ኸረ አልሆንልኝም አለ መንፈሴ አልገዛም አለ

የጭንቅ አማላጅቱ አንድ ብትዪኝ ምን አለ

ጸሎት ምህላ አቃተኝ መንፈሴ ከንስሐ ሸፈተ

መንጸፈ ደይን ወደቅኩኝ ነፍሴ በኀጥያት ሸተተ

እምቢ አለኝ ጾም ጸሎት አምቢኝ አለኝ ንስሐ

ስጋ መንፈሴ ኮብልሎ እየዋኘ ከአለም ውሃ

ኸረ አንድ በይኝ እመቤቴ ወለላይቱ ተማለጂኝ

ጨርሶ ዓለም ሳይነጥቀኝ ከወደቅኩበት አንሺኝ

ነጭ ነጠላ አጣፍቼ ከቤተ መቅደስ ስመጣ

መጽሐፍ ቅዱስ ዘርግቼ ለስብከት መድረክ ስወጣ

ልብሰ ተክህኖ ለብሼ ንፍቅ ገባሬ ሰናይ ስሆን

ጥቅስ በቃሌ ስደረድር ለዜማ ቅኔ ስቀኝ

አካሌ እዚህ ሆኖ መንፈሴ እየሸፈተ

ነፍሴን በኃጥያት ገንዞ ስጋዬ ነፍሴን ጎተተ

ኸረ አንድ በይኝ እመብርሐን ወለላይቱ ተማለጂኝ

ጨርሶ ዓለም ሳይነጥቀኝ ከወደቅኩበት አንሺኝ

ማለዳ ኪዳን አድርሼ ቅዳሴ ጸሎት ጨርሼ

ከቤተክርስትያን ወጥቼ ወደ ስጋ ገበያ ተመልሼ

በኃጥያት ባህር ስዋኝ የግፍ ዳንኪራ ስረግጥ እውላለሁ

የልጅነት ጸጋዬን አውጥቼ ብኩርናዬን እሸጣለሁ

እዚህ መልአክ መስዬ ላዬ በቅድስና በርቶ

ውጪ ከክፋት ከፍቼ ኃጥያት በጽድቄ ተተክቶ፤

በሐሜት የሰው ስጋ ስበላ በወንድሜ ሸር ስሸርብ

ስዋሽ ስቀጥፍ ውዬ ስሰርቅ ሳሽሟጥጥ ስሳደብ

ነጠላ ስለብስ ግን ወደ ቤተ-እግዚአብሔር ስገባ

ሰአሊ ለነ ቅድስት ስል ያለ ንሰሐ እንባ፤

የመውደቂያዬ ጉድጓዱ ጥልቀቱ ወሰን ዳርቻ የለውም

እዝነ ሕሊናዬ ለዓለም እንጂ ለጽድቅ ቦታ የለውም፡፡

መሐረነ ክርስቶስ እንዳልል ተዘከረነ ፈጣሪዬ

ኃጥያት በደሌ አፈነኝ በሐፍረት ነደደ ሕሊናዬ

ምን ብዬ ልጥራው ጌታዬን ተዘከረኒ ብዬ

ሰለኔ መገረፉን የመስቀል ፍቀሩን አቃልዬ

እንዴት ማረኝ ልበለው ስለስጋ ጣዕም ተቃጥዬ፡፡

ምን ብዬ ልጥራው ጌታዬን  ???

ዐይኔን ወደ ጸፍጸፈ ሰማይ ወደ ስላሴ መንበር

አንስቼ ማየት አቃተኝ ማረኝ ብዬ ለመናገር፡፡

ለሰው ጻድቅ መስዬ የኃጥያት ጎተራ ሆኛለሁ

እነዴት አባቴ ቀና ብዬ መንበረ ጸባኦትን አያለሁ፡፡

እባክሽን እናቴ ወለላይቱ ተማለጂኝ

እንደ ቃና ዘገሊላ ባዶ ማድጋዬን ሙዪልኝ

ከፊቱ እንዳላፍር ከዐማኑኤል ጋር አስታርቂኝ

ለተጠማ ውሻ እንዳዘንሽ ለመጻተኛው እዘኚልኝ፡፡

አንቺ የትሁታን ትሁት ርሕርይተ ልብ እናቴ

ከልጅሽ ከኢየሱስ አማልጂኝ እዘኚ ለእኔም እመቤቴ

አንቺ ውዳሴሽ የነፍስ ስንቅ ስምሽ ከማር የጣፈጠ

በላሔ ሰብ በእፍኝ ውሃ በምልጃሽ ከሞት ያመለጠ

አንቺ መላዕክት የሚጎበኙሽ የካህናት አለቆች ምስጋናቸው

በመወሰን የማይወሰን እሳተ መለኮትን የቻልሽ

አንቺ ከገነት በተሰደደ ጊዜ ለአዳም ተስፋ የሆንሽው

ዛሬም ለእኔ ተስፋ ሁኚኝ ለነፍሴ ስለ ነፍሴ ተዋሺው

እንጂ እኔማ አልቻልኩም የልቤ ንጽህና ጠፍቷል

ለጸሎት እንኳ ስቆም ልቤ ለሁለት ተከፍሏል

ኸረ አልሆንልኝም አለ መንፈሴ አልገዛም አለ

የጭንቅ አማላጅቱ አንድ ብትዪኛ ምን አለ

እምቢ አለኝ ጾም ጸሎት አምቢኝ አለኝ ንስሐ

ስጋ መንፈሴ ኮብልሎ እየዋኘ ከአለም ውሃ

የልቤን መወላወል የነፍሴን ድካም አበርቺኝ

በአማላጅነትሽ ስር ነኝ እና ከልጅሽ አስታርቂኝ

ለሰው ዐይን ባይገለጥም የሰራሁት ኃጥያት

አምላክን አሳዝኖታል የምኖርበት ሕይወት

ይኸው. . .

የምናገረው አይሰምርም የወረወርኩት አይመታም

ስጋዬ አልተቀደሰም ገበታዬ በረከት የለውም

ዕውቀት ምርምር አይዘልቀኝ ሕሊናዬ ፍሬ አቋጥር

ዝርው ሆኖብኝ ቀርቶ የነፍስ የስጋዬ ምስጢር

ይኸው . . .

የማወራው ለሰው አይጥም ፍቅር ከእኔ ርቋል

መቆም መቀመጤ አያምር ሰው በስራዬ ይማረራል

የኃጥያት ምንዳዬ ይኸው

የኃጥያት ደሞዜ ይኸው . . .ስቃዬ ውስጤን በልቶታል

ለአንድነት የተናገርኩት ዛሬም ጉባሔ ይበትናል

እናም አዛኚቱ ታረቂኝ ከልጅሽ ከዐማኑኤል አማልጂኝ

ከሰው የሸሸግኩት ኃጥያት ጨርሶ በልቶ ሳይውጠኝ

የበላሔ ሰብ እመቤት እባክሽን ተማለጂኝ

አንቺ ሕይወቴን ዳብሺው ነፍሴ እረፍት እንድታገኝ

ኸረ አልሆንልኝም አለ መንፈሴ አልገዛም አለ

የጭንቅ አማላጅቱ አንድ ብትዪኝ ምን አለ ???

የደ/ገ/ዐማኑኤል/ካ/እግዚአብሔር/ም/ሰ/ት/ቤት ስነጽሁፍና ተውኔት ክፍል

ከሌላ ምንጭ የተገኘ