(በዲ/ን ሕሊና በለጠ)
በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለው ጊዜ ዘመነ ጽጌ/ ወርኃ ጽጌ ይባላል፡፡
የተዘሩ አዝርዕት በቅለው፣ የተተከሉ አትክልት ጸድቀው፣ አብበውና አፍርተው የሚታዩበት የጽጌ፣ የልምላሜ ጊዜ ነው፡፡ “አሠርጎኮ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ በሥነ ጽጌያት ግብረ እደዊከ አዳም እግዚኦ” እያልን ጌታን የምናመሰግንበት ጊዜ ነው- ጌታ ኮከብን ለሰማይ ውበት ጽጌን ለምድር ጌጥና ሽልማት አድርጎ ሰጥቷልና፡፡ ከዚህ የተነሣ ኮከብ ሰማይን ጽጌ ምድርን ያስጌጣሉ፡፡ ኮከብ ሰማይን አበባ ምድርን በባሕሪያቸው እንደሚያስውቡት ሁሉ እራሳቸውንና ገንዘባቸውን የተወደደና ያማረ መሥዋዕት አድርገው ለአምላካቸው የሚሰጡ ምእመናን ገድል እንዲሁ ለቤተክርስቲያን የመወደድ ጌጥን ይሰጣታል፡፡
በዚኽ በዘመነ ጽጌ የሚታሰበው ሌላው ዐቢይ መንፈሳዊ ጉዳይ የእመቤታችን ጌታን ይዛ መሰደድ ነው፡፡ በመኾኑም አባታችን አባ ጽጌ ድንግል የደረሰውና መልካም መዐዛ ባላቸው አበቦችና ፍሬዎች ጌታንና እመቤታችንን እየመሰለ የሚያመሰግነው ማኅሌተ ጽጌ የተሰኘው ድርሰት በዚህ ወቅት በሰፊው አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡
ካህናትና ምእመናን እመቤታችን ጌታን ይዛ በስደት መንከራተቷን ለማሰብ ሌሊቱን በቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ የሚያድሩበት ለኦርቶዶክሳዊያን የተዋሕዶ ልጆች ተናፋቂ የኾነ ወቅት ነው፡፡
ለመሆኑ ጌታ ስለምን ተሰደደ?


ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰደዱትን የሚያስጠልል፣ የተራቡትን የሚያበላ፣ የተጠሙትን የሚያጠጣ፣ ከሰማይ ላይ መናን ለእስራኤል ያወረደ፣ በበረሀ ድንቅ ተዐምራትን ያደረገ፣ ኤልያስን ከኤልዛቤል፣ ዳዊትን ከሳኦል፣ ሙሴን ከዳታንና አቤሮን፤ እስራኤልን ከፈርኦን የጠበቀ ሁሉን ቻይ ሆኖ ሳለ ስለ ምን ተሰደደ?
አምላካችን በወላዲተ አምላክ በውድ እናቱ ድንግል ማርያም ታቅፎ ስለ አራት ነገሮች ተሰደደ፡፡
1ኛ. አዳም ከገነት ወደዚህ ዓለም ተሰድዶ መጥቶ ነበርና የጌታም መወለድ አዳምን ከነልጆቹ ለማዳን ነውና በዚህ ምክንያት ጌታ ተሰደደ፡፡ ጌታ ከመወለዱ ከ5500 ዓመት በፊት አዳም ትእዛዝን ተላልፎ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ ብሎት ነበርና በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ የአዳምን ስደት ተሰደደለት፡፡
2ኛ. እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ (ማለትም ፈጣን ደመና በተባለች እናቱ ጀርባ ታዝሎ) ወደ ግብፅ ይመጣል፤ ልጄን ከግብፅ(ወደ ግብፅ ጠራሁት) ተብሎ በነቢዩ ኢሳይያስና በነቢዩ ሆሴዕ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታ ተሰደደ፡፡(ኢሳ.19፡1-2፤ ሆሴ.11፡2)፤ ልጄን ወደ ግብፅ ጠራሁት ማለቱ መሰደዱን፣ ከግብፅ ጠራሁት ማለቱ ደግሞ መመለሱን ያሳያል፡፡
ቅዱስ ያሬድም “ደመና ቀሊል ዘይቤ ኢሳይያስ ይእቲኬ ማርያም ድንግል እንተ ፆረቶ በከርሣ ለወልደ እግዚአብሔር” ማለትም “ኢሳይያስ ፈጣን ደመና ያላት የአብ የባሕሪዩ ልጅ የሆነ ወልድን በማኅፀኗ የተሸከመች ድንግል ማርያም ናት” በማለት መዋሥዕት በተባለው ድርሰቱ ተርጉሞታል፡፡ እመቤታችንንም የኢሳይያስ ደመና ያሰኛት ይሄ ነው፡፡
3ኛ. ሦስተኛው ጌታችን የተሰደደበት ምክንያት፤ ጌታ ባይሰደድ ሕፃናቱ ሲገደሉ እሱ ከሞት ቢተርፍ ኖሮ ትስብእቱ(የጌታ ሰው መሆን) ምትሐት ነው ብለው በተሰናከሉ ነበርና፣ የሞቱ ጊዜም ገና አልደረሰም ነበርና፣ ጌታም በተሰደደበት ቦታ ያሉ ሰዎች የጌታንና የእናቱን በረከት ያገኛሉና ነው፡፡
4ኛ. ጌታ የተሰደደበት የመጨረሻው ምክንያት ስደትን ለጻድቃን፣ ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠትና አብነት ለመሆን ነው፡

ዘመነ ጽጌና የጌታ መሰደድ ምክንያት