በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሃይማኖት” ማለት አምነ፣ አመነ ከሚል የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን መዝገበ ቃላታዊ ትርጓሜውም “ማመን፣ መታመን” ማለት ነው፡፡ በምሥጢራዊው ትርጕሙ ግን “ሃይማኖት” ማለት ፍጥረትን ኹሉ ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣ አንድ እግዚአብሔር እንዳለ፣ ለሚታየውም ለማይታየውም ፍጥረት ሠራዒውና መጋቢው ርሱ ብቻ እንደኾነ፣ ልዩ ሦስትነት እንዳለው፣ በዚኽ አለ በዚኽ የለም የማይባል ምሉዕ በኵለሄ እንደኾነ፣ … ማመን መታመን ማለት ነው፡፡
“ማመን” ማለትም ይኾንልኛል ይደረግልኛል ብሎ መቀበል፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ተስፋ ማድረግ፤ አለመጠራጠር ማለት ሲኾን፤ “መታመን” ማለት ደግሞ ያመኑትን እውነት በሰው ፊት በአንደበት መመስከርና በተግባራዊ ሕይወት መግለጥ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይኽን በተመለከተ፡- “ይኽም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ኾነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ብሎ አስተምሯል /ሮሜ.10፡8-10/፡፡ ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ፡- “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትኹ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል” በማለት ከኹሉ አስቀድሞ እምነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳና፤ ቀጥሎም “ማንም ግን በዚኽ መሠረት ላይ በወርቅ ቢኾን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤” በማለት ምግባር ትሩፋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል /1ኛ ቆሮ.3፡10፣12/።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት 9ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “እምነት መሠረት ናት፤ ሌሎች ግን ሕንፃና ግንብ ናቸው” በማለት ምግባርና ትሩፋት ከመሥራት በፊት እምነት እንደሚቀድም አስተምሯል /ቍ.80-81/፡፡
ስለዚኽ “ትምህርተ ሃይማኖት” ስንል ስለዚኹ ስለምናምነው አምላክ የምንማማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው ማለት ነው፡፡ “ስለምናምነው አምላክ የምንማማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው” ሲባል ግን በፍልስፍናና በዚኽ ዓለም እንደምናደርገው በምርምርና በሙከራ እንደርስበታለን ለማለት ሳይኾን እግዚአብሔር ራሱ በተለያየ መንገድ የገለጠውንና እንድናውቀው የፈቀደውን ብቻ እንማማራለን ለማለት ነው፡፡ በዚኹ ዙርያ ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔር ስንማማር በስፋት እንመለስበታለን፡፡
በፍልስፍናው ዓለም ፍልስፍናን ለመማር የራሱ የኾነ ቅድመ ኹኔታ (Axiom) እንዳለ ኹሉ በትምህርተ ሃይማኖትም ስለ ፈጣሪ ለማወቅ “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል” ተብሎ እንደተጻፈ አስቀድሞ እምነት ያስፈልጋል /ዕብ.11፡6/፡፡ እምነት ማለትም ለመለኮታዊው መገለጥ የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡ በትምህርተ ሃይማኖት የመዠመሪያው ቅድመ ኹኔታ ይኽ እምነት ነው፡፡ እምነት ሳይኖረን ትምህርተ ሃይማኖትን መማር አይቻለንም፤ ትምህርተ ሃይማኖት የአዕምሮ ጨዋታ አይደለምና፡፡ ትምህርተ ሃይማኖትን ስናጠና ኹል ጊዜ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ እምነት ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ስጦታ ቢኾንም ፈቃዳችንን ይጠይቃል፡፡ ይኽ አካሔድም በቤተ ክርስቲያን ቋንቋ “ፍኖተ አሚን” ይባላል፡፡
ቀጥሎ የሚመጣው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንኾንኽ አምነናል፤ ዐውቀናልም” እንዳለው ዕውቀት ነው /ዮሐ.6፡69/፡፡ ኾኖም አኹንም ጥንቃቄ ያስፈልገናል፡፡ ይኸውም ይኽ ስለ ፈጣሪ የምናውቀው እውነት መጨረሻ የለውም፡፡ ለምን? እግዚአብሔር ወሰን የለውምና /ኤር.23፡23/፡፡ ተጠንቶ የሚያልቀው ውስንነት ስላለው አካል (ፍጡር) ብቻ ነው፤ ያውም አብዛኛው አያልቅም፡፡ ስለኾነም ስለ እግዚአብሔር የምንማረው ኹሉ በጥቂት ቃላት ብቻ ታጥሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ይኽ አነጋገር በኦሬንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አነጋገር “Apophatism – አፖፋቲዝም” ይባላል፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. “አንድም ፣ አንድምታ” እያልን የምናውቀው ነው፡፡
“ታድያ መማራችን ምን ፋይዳ አለው?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡
1ኛ) የተገለጠውን እውነት ለመረዳት ይጠቅማል፤
2ኛ) የቀደመችውን አንዲቷን መንገድ መያዝ ስለሚያስፈልግ እውነትን ከሐሰት ለመለየት ይረዳናል፤
ምንም እንኳን ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ቢኾንም፥ ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሰዎች ፈልገው የማያገኙት ቢኾንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስና በሥነ ፍጥረት የተገለጠውን ግልጽ ትምህርት መማርን ግን አያወግዝም፡፡ ኹል ጊዜ እውነትን ለማወቅ ከመጠየቅ ዕረፍት የሌለው የሰው ልጅ አዕምሮንም በአመክንዮ (By Reason) ማስረዳትን እንዲኹ አያወግዝም፡፡ ይልቁንም አመክንዮን በትክክለኛው መንገድ እንድንጠቀምበት ያግዛል እንጂ፡፡
ምንም እንኳን አዳምና ሔዋን ከበደሉ በኋላ ከሃይማኖት መንገድ ቢወጡም እግዚአብሔር አዳምን ጠርቶ “ወዴት ነኽ?” ባለው ጊዜ መልሶታል፡፡ ከአቤል ዠምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ላይ በነበሩ ደጋግ ሰዎችም ቀጠለች፡፡ አቤልን ከቃየል፣ ኖኅን ከሰብአ ትካት፣ አብርሃምን ከሰብአ ዑር፣ ሙሴን ከሰብአ ግብጽ፣ ነቢያትን ከሐሰትና ከክሕደት የለየቻቸውም ይኽቺ ርትዕት ሃይማኖት ናት /ዕብ.11/፡፡ በመጨረሻ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጉልቶና አብራርቶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣት /ዮሐ.17፡8/፡፡ ከእኛም ዘንድ ደረሰች /ይሁዳ ቁ.3/፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የምታስተምረውም ይኽንኑን ነው፡፡ መዳን ከዚኽች እምነት ውጪ ኾኖ እንደማይገኝ፣ በቤቷ ብንመጣ በሕይወታችን ሰላምን እንደምናገኝ፣ በሚመጣውም ዓለም ከዚኽ የበለጠ ሰላምና ዕረፍት እንደሚጠብቀን ለኹላችንም ማስተማሯ ስለዚኹ ነው፡፡

ሃይማኖት ያላቸው ፍጥረታት
ሃይማኖት ያላቸው ፍጥረታት ኹለት ሲኾኑ፥ እነርሱም መላዕክትና ሰዎች ናቸው፡፡ አጋንንትም ቢኾኑ ምድባቸው ከመላዕክት ወገን ስለኾነ ሃይማኖት እንዳላቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል /ያዕ.፪፡፲፱/፡፡ የአጋንንት ችግራቸው ከምግባር የተለየ ሃይማኖት ስላላቸው ነው፡፡
አንዲት ሃይማኖት
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ ሃይማኖት” እንዳለ /ኤፌ.4፡5/ በዓለመ መላዕክት የነበረች፣ በሕገ ልቡና በሕገ ኦሪት የቀጠለች፣ በዘመነ ሐዲስም ያለች ሃይማኖት አንዲት ነች፡፡ ይኽቺ ሃይማኖት ተነጻጻሪ፣ ተፎካካሪ፣ እኩያ እኅት ወይም ወንድም፣ መንትያ ቅጥያ፣ ልዋጭ አማራጭ፣ ተቀዳሚ ተከታይ የላትም፡፡ ሃይማኖት አንድ የኾነችበት ምክንያትም እግዚአብሔር አንድ ስለኾነ ነው፡፡ ከዚኽች ሃይማኖት ውጪም ድኅነት የለም፡፡
የሃይማኖት አስፈላጊነት
የሰው ልጅ የተፈጠረው የእግዚአብሔርን ክብር ወርሶ፣ ስሙንም ቀድሶ በዘለዓለማዊ ሕይወት ለመኖር ነው፡፡ በመኾኑም ሰው ያለ ሃይማኖት ልኑር ቢል በፍጹም አይችልም፡፡ የታሪክ ድርሳናትም ሰው ያለ ሃይማኖት የነበረበትን ዘመን አልጻፉልንም፡፡ ምናልባት በፍጡራን ወይም በኅሊናው በፈጠረውና ጭራሽ ህልውና በሌለው ምናብ ተይዞ የሚያመልከውን አምላክ በትክክል ላያውቀው ይችል እንደኾነ እንጂ ሰው ያለ ሃይማኖት መኖር አይችልም፡፡ ሃይማኖት የለኝም ብሎ የሚያስበው ሰው እንኳን “ሃይማኖት የለኝም” የሚለው አመለካከቱ ለርሱ ሃይማኖቱ ነው፡፡ ሰው ያለ ሃይማኖት መኖር እንደማይችል የበለጠ የሚታወቀው ደግሞ አስቸጋሪ ኹናቴ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ በዚያ የጭንቅ ሰዓት ሰው ረዳት ይፈልጋል፡፡
ከላይ በገለጥናት አንዲት ሃይማኖት ስንኖር እጅግ ብዙ ጥቅሞችን እናገኛለን፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያኽልም፡-
· በሕግ በአምልኮት ለሚሹት ሰዎች እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ዋጋ እንዳለ ዐውቀን በሃይማኖት ስንቀርብ እግዚአብሔርን ደስ እናሰኛለን /ዕብ.11፡6/፤
· ምንም ዓይነት መከራ ቢገጥመንም እግዚአብሔር ያስችለኛል ብለን መንፈሰ ጠንካራ በመኾን ፈቃደ ሥጋን አንድም ፈቃደ ሰይጣንን እናሸንፋለን፤ በሃይማኖት /ፊልጵ.4፡13፣ 1ኛ ዮሐ.5፡4-5/፤
· ባለመኖሩ አይታይ የነበረው ዓለም ካለ መኖር ወደ መኖር መጥቶ እንደታየ የምናውቀው በሃይማኖት ነው፡፡ በዚኽም የእነዚኽን ፍጥረታት አስገኚ እግዚአብሔርን እናውቅበታለን፤ በሃይማኖት /ዕብ.11፡3/፤
· ሰው ቢሰጥ ኃላፊውንና ጠፊውን ነው፤ እግዚአብሔር ግን ዘለዓለማዊውን ይሰጣል፡፡ ሰው ቢሰጥ ግዙፉን ነው፤ እግዚአብሔር ግን ረቂቁን ነው፡፡ ሰው ቢሰጥ ማፍጀት፣ መሰልቸት፣ መጸጸት፣ መሰቀቅ አለበት፤ እግዚአብሔር ሲሰጥ ግን ይኽ ኹሉ የለበትም፡፡ በመኾኑም በሃይማኖት ወደርሱ ስንቀርብ እውነተኛ ሰላምን እናገኛለን /ዮሐ.14፡27/፤
· በየትኛውም ዓይነት ሥፍራና ኹናቴ ብንኾንም በሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብ ከኾነ ከሚቃጣብን መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ እንድናለን /ዳን.6፡10-28/፤
· አብን ወላዲ፣ ወልድን ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ብለን ስናምን ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ እናገኝባታለን፤ ሃይማኖት /ዮሐ.3፡18/፤
· እና የመሳሰሉት፡፡
ኦርቶዶክስ እና ተዋሕዶ የሚሉ ስሞችን የምንጠቀምበት ምክንያት
ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የጽርዕ (የግሪክ) ቋንቋ (ኦርቶ= የቀና፣ የተስተካከለ ፥ ዶክሳ= እምነት፣ አመለካከት) ሲኾን ትርጓሜውም ቀጥተኛ እምነት ማለት ነው፡፡ ይኽ ስም ለክርስትና እምነት የተሰጠው በ325 ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ነው፡፡ ሠለስቱ ምዕት ለክርስትና ሃይማኖት ይኽን ስያሜ ሲሰጡት አርዮስ “ወልድ ፍጡር በመለኮቱ” ብሎ ሲነሣ ከክርስቶስ የተቀበሏት ሃይማኖት እንዲኽ ዓይነት እንግዳ ትምህርት እንደሌላት ገልጠው ሃይማኖታቸው ርትዕት፣ የቀናች መኾኗንና ከአርዮስ ትምህርት የተለየች መኾኗን ለመግለጥ ነው፡፡
ተዋሕዶ ማለት ከግእዝ የተወረሰ ቃል ሲኾን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ለምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት መጠሪያ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ትርጓሜውም ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ከኹለት አካል አንድ አካል፥ ከኹለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ እንደ ነፍስና ሥጋ አንድ መኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይኽ ስም ለኦርቶዶክስ ክርስትና የተሰጠው በ431 ዓ.ም. በጉባኤ ኤፌሶን ነው፡፡ ቅዱሳን አበው ይኽን ገላጭ ቃል ሲጠቀሙ ሥጋን ከመለኮት ነጥሎ አካልንና ባሕርይን ከፋፍሎ የሰበከ ንስጥሮስንና ተከታዮቹን ሲያወግዙ ነው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ ተዋሕዶ የሚለው አገላለጽ ሥጋን ከመለኮት ጋር ቀላቅሎና አጣፍጦ የተወገዘውን የአውጣኪን ትምህርት ያርቃል፡፡
የኦርቶክስ ተዋሕዶን እምነት የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያናት 6 ሲኾኑ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ እስክንድርያ፣ የሕንድ ማላንካራ፣ ሶርያ እና አርመን ናቸው፡፡
ተወዳጆች ሆይ! እኛም በዚኽች አቤልን ከቃየል፣ ኖኅን ከሰብአ ትካት፣ አብርሃምን ከሰብአ ዑር፣ ሙሴን ከሰብአ ግብጽ፣ ነቢያትን ከሐሰትና ከክሕደት፣ ሐዋርያትን ከሰብአ ዓለም የለየቻቸውም ተነጻጻሪ፣ ተፎካካሪ፣ እኩያ እኅት ወይም ወንድም፣ መንትያ ቅጥያ፣ ልዋጭ አማራጭ፣ ተቀዳሚ ተከታይ የሌላት አንዲት ሃይማኖት ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ከዚኽች ሃይማኖት መውጣት ከሕይወት መውጣት ነውና፡፡ ከዚኽች ሃይማኖት መውጣት ሲባል ግን እምነቷን መካድ ብቻ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በልቡናቸው እግዚአብሔርን እንደሚያውቁት አድርገው እናምናለን ይላሉ፡፡ በሥራቸው ግን ይክዱታል” እንዳለ /ቲቶ.1፡16/ በተግባራዊ ምልልሳችንም በዚኽች ሃይማኖት ጸንተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚኽም የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡

…ተመስጦ…
ቸርና ሰው ወዳጅ የኾንከው እግዚአብሔር ሆይ! ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣኸን አንተ ነኽ፡፡ ምን እንደሚያስፈልገን ዐውቀኅ የሚጠቅመንን ብቻ የምትሰጠን አንተ ነኽ፡፡ ይኽም የምታደርገው ስለ ፍቅርኅ እንጂ ከእኛ መልካም ነገር አግኝተኅ አይደለም፡፡ ቅዱስ ሆይ! እንኪያስ እኛም ፍቅርኅ ይገባን ዘንድ ልቡናችንን በብርሃንኅ አብራልን፡፡ አምነንና ታምነን እንጸና ዘንድ ርዳን፡፡ በፍኖተ አዕምሮ ሳይኾን በፍኖተ አሚን ተጕዘን “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ዠምሮ የተዘጋጀላችኁን መንግሥት ውረሱ” ብለኅ በቀኝ ከምታቆማቸው ቅዱሳን ጋር እንቈጠር ዘንድ ቸርነትኅ ትርዳን፡፡ አሜን፤ ይኹንልን፤ ይደረግልን፡፡
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፡ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ)
ይድረስ ለሯጩ ወንድሜ
በአምሃ ገብርኤል
ከዓምደ ሃይማኖት /ሰ/ት/ቤት

የትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ