አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመውሰድ ቃሉ ለተጻፈበት ዓለማ ወይም ለሚያስተላልፈው መልእክት ሳይሆን እነርሱ ለሚፈልጉት የተቃርኖ አስተያየት የሚጠቀሙ ሰዎች ለዚሁ አካሔድ ከሚጠቀሙባቸው ሐሳቦች መካከል አንዱ የጌታችንን ማዳን ከቅዱሳን አዳኝነት ጋር የሚቀናቀን ወይም የሚጻረር አድርገው ማቅረባቸው ነው፡፡

*** የዚህ ሐሳብ አቅራቢዎች የጌታን አዳኝነት የሚገልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን መሠረት አድርገው ይነሡና መዳን በጌታ ከሆነ ቅዱሳን አያድኑም ማለት ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የጌታን አዳኝነት ከቅዱሳን አዳኝነት ጋር እንደ ተቀናቃኝ ማሰባቸው ስሕተት ነው፡፡ የቅዱሳን አዳኝነት የጌታን አዳኝነት ይበልጥ የሚያረጋግጥ እንጂ የሚቃወም እንዳልሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠውን ልብ ቢሉ ከዚህ ስሕተት ይድኑ ነበር፡፡

~~በመጀመሪያ ደረጃ የቅዱሳን አዳኝነት እራሳቸው ቅዱሳኑ የፈጠሩትና በገዛ ኃይላቸው የሚፈጽሙት ሳይሆን ከአምላክ የተቀበሉት ነው፡፡ ስለዚህ እነርሱ ቢያድኑም በእነርሱ ውስጥ ይህን የማዳን ሥራ የሚሠራው እርሱ አምላካቸው ነው፡፡

~~እንኳን በነፍስ ስለሚሆነው መዳን ቀርቶ ከሥጋዊ ሕማሞች እንኳ ለማዳን ቅዱሳን የሚጠሩት የአምላክን ስም ሲሆን ስለ ድንቅ ሥራውም እንዲመሰገን የሚፈልጉት የአምላካቸው ስም ነው፡፡

~~~ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራን እግሩ የሰለለችበትን ሰው በፈወሱ ጊዜ ሕዝቡ በመደነቅ አማልክት ናቸው በማለት ሊሰዉላቸው ሲነሡ እንዴት እንደተቃወሙ ታሪኩ እንዲህ ይነግረናል “ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፤ እንዲህም አሉ፦ እናንተ ሰዎች ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን።” (ሐዋ.14፡14-15)

~~~ታድያ ሐዋርያት ምድራዊ ፈውስ እንኳ ቢሆን ሥራው የአምላክ እንደሆነ እንዲታወቅ ካደረጉ ለሰማያዊው ድኅነትማ እንዴት እነርሱ ራሳቸው አደረጉት ሊባል ይችላል? ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን የሚደረገውን ማዳን “የጸጋ” ብላ ስትጠራ የጌታችንን ደግሞ “የባሕርይ” ብላ ትለየዋለች፡፡ ይህም የክርስቶስ አዳኝነት ከማንም ያልተቀበለውና ማንም የማይወስድበት መሆኑን የሚገልጥ ሲሆን የቅዱሳን አዳኝነት ደግሞ ከጌታ የተቀበሉት መሆኑን የሚገልጥ ነው፡፡

~~~በሌላም በኩል የቅዱሳን አዳኝነት የክርስቶስን የማዳን ሥራ ይበልጥ የሚያጸና እንጂ የሚቃወም አይደለም፡፡ ይኸውም ከክርስቶስ የማዳን ሥራ በፊት በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሰዎች ሌሎችን ሊያድኑ ቀርቶ እራሳቸውም በገዛ ጽድቃቸው መዳን አልቻሉም ነበር፡፡

~~~በሐዲስ ኪዳን ግን የመዳን መንገዱ በጌታችን የማዳን ሥራ በመከፈቱ ምክንያት ጻድቃን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ማዳን ለመቻል በቁ፡፡ ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን የቅዱሳን ማዳን የክርስቶስን ማዳን የሚቀናቀን ወይም የሚቃወም ሳይሆን ይበልጥ የሚያጸና፣ ይበልጥ የሚያረጋግጥልን ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ የተገለጠ ነው፡፡ ማስረጃዎቹን ከዚህ በታች እንመለከት፡፡

~~~“ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” (ማቴ.10፡ 41-42)

~~~ይህ የጌታችን ቃል ነው፡፡ ቃሉ ነብያትንና ጻድቃንን በመቀበል ስለሚገኝ ዋጋ የሚናገር ነው፡፡ ለመዳን ጌታን መቀበል ብቻ በቂ ስለሆነ ጻድቃን አያስፈልጉም ለሚሉ ሰዎች ይህ የጌታችን ቃል ዱብ ዕዳ እንደሚሆንባቸው አያጠራጥርም፡፡

~~~ቃሉ ይበልጥ ይግረማችሁ ብሎ “በደቀ መዝሙር ስም ቀዝቃዛ ውኃ ብቻ የሚያጠጣ” ዘላለማዊ ዋጋን እንደሚቀበል ይነግረናል፡፡ “ብቻ” የምትለዋ ቃል እንዴት ትደንቃለች? ውኃ ብቻ ዘላለማዊ ዋጋ የምታሰጥ ከሆነ፣ ጻድቃንን መቀበል የእነርሱን ዋጋ የሚያጎናጽፍ ከሆነ ከዚያ የሚልቅ መታሰቢያን ለቅዱሳን ማድረግማ የቱን ያህል የላቀ ዋጋ በሰማይ ያሰጠን ይሆን?

~~~መጽሐፍ ቅዱስ የእኛ የሰው ልጆች መዳን ከቅዱሳን መላእክት ጋር ያለውን ግንኙነት ይነግረናል፡፡ ጌታችን በወንጌል የአንድ ኀጥእ በንስሐ ወደ መዳን መንገድ መመለስ በሰማይ መላእክት ዘንድ የሚፈጥረውን ደስታ ሲገልጥ እንዲህ ብሎናል፡፡

*** “እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።” (ሉቃ.15፡7)

~~~ታድያ ቅዱሳን መላእክት የሰዎች መዳን የሚያሳስባቸውና ወደመዳን ሲያመሩ ደስ የሚሰኙ ከሆኑ ሰዎች እንዲድኑላቸውና ደስታቸው ፍጻሜ እንዲያገኝ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ መኖሩ የማይቀር ነው፡፡

~~~ይህም እውነት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይነግረናል፡፡ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብ.1፡14)

*** ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱሳን መላእክት ለመዳናችን የሚኖራቸውን ሚና ግልጥ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ጌታችን ማን እንደሆነ ሲገልጥ እርሱ የመላእክት አምላካቸው መሆኑን ከገለጠ በኋላ የእርሱን ሚና ከመላእክት ሚና እንድንለይ ያስተምረናል፤ በመጨረሻም እንድንድን የሚሹ መላእክት መዳናችንን እስክንወርስ ድረስ በተልእኳቸው እንደሚራዱን ይነግረናል፡፡

~~~ታድያ ሐዋርያው ይህን ስለነገረን የክርስቶስ የማዳን ሥራ በመላእክት ተተክቷል ልንል ነውን? እንደዚያ እንዳንል ሐሳቡ ግልጥ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ የጌታ አዳኝነት በማንም የማይተካ ሲሆን የቅዱሳን ጻድቃንና የቅዱሳን መላእክቱ ደግሞ ከክርስቶስ የተቀበሉት እርሱ አስቀድሞ የመዳናችንን በር ከመክፈቱ የተነሣ የተገኘ ስለሆነ የሚደጋገፍ እንጂ የሚቀዋወም አይደለም፡፡

(ምንጭ፡- ዕቅበተ እምነት በእንተ ነገረ ድኅነት፣ 2011)

መዳን በጌታ ስለሆነ ቅዱሳን አያድኑምን?