በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን

አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው:: ጻድቁ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ኣካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ:: የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው::

+ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው:: ወላጆቻቸው ዘሚካኤል ሲሏቸው በበርሃ ገብረ አምላክ ተብለዋል:: በኢትዮዽያ ደግሞ አረጋዊ ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ::

+በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል:: ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር 7 ያህል የቤተ መንግስት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል::

+”የት ልሒድ” ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮዽያን አሳያቸው:: ተመልሰውም ለ8 ባልንጀሮቻቸው “ሃገርስ ባሳየሁዋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር” ብለው ከ8ቱ ጋር ወደ ኢትዮዽያ መጡ::

+በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ:: ወደ ሃገራችን የመጡ በ470ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል:: በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ: ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል::

+ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል:: በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት:: የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ 60 ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል::

+እንደ ወጡም “ሃሌ ሉያ ለአብ: ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ” ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል:: በዚህም ቦታዋ “ደብረ ሃሌ ሉያ” ተብላለች:: ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በኋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው 6ሺ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል::

+ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም “አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮዽያ-የኢትዮዽያ መነኮሳት አባት” ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል::

+ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ:: በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሐረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግስት እድና ሁናለች::

+ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው በዚህ ቀን በገዳሙ በስተምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል:: ጌታም 15 ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል::

+” ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ “+

✞✞✞ በዘመነ ሐዋርያት በዚህ ስም የሚጠሩ አባቶች 2 ነበሩ:: አንደኛው ከ12ቱ ሐዋርያት ሲቆጠር ዛሬ የምናከብረው ደግሞ ከ72ቱ አርድእት ይቆጠራል:: ቅዱስ ፊልዾስ ያደገው የኖረውም በቂሣርያ አካባቢ ሲሆን ባለ ትዳር የልጆች አባት ነው::

+ጌታ ሲጠራው እንኩዋ 4 ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት:: ከጌታ ሕማማት በፊት ተልኮ አስተምሯል:: ከበዓለ ሃምሳ በኋላም 7ቱ ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: (ሐዋ. 6) በቅዱስ እስጢፋኖስ መሪነትም 8ሺውን ማሕበር አገልግሏል::

+ቅዱስ እስጢፋኖስ ተገድሎ 8ሺው ማሕበር ሲበተንም ቅዱስ ፊልዾስ 4ቱን ልጆቹን አስከትሎ ወደ ሰማርያ ወርዷል:: በዚያም መሠሪ ስምዖንን ጨምሮ የሃገሪቱን ሰዎች አሳምኖ አጥምቁዋል::

+መቼም ቢሆን እኛ ኢትዮዽያውያን የማንዘነጋው ግን ጃንደረባውን ባኮስን ማጥመቁን እና ለሃገራችን የወንጌልን ብርሃን መላኩን ነው:: ጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ ከጉዞ መልስ ትንቢተ ኢሳይያስን (ኢሳ. 53) ሲያነብ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቀርቦ ምሥጢረ ሥጋዌን አስረድቶታል::

+ሠረገላውም ቁሞለት ቅዱስ ባኮስን አጥምቆት ተነጥቆ ሔዷል:: (ሐዋ. 8:26) ቅዱስ ፊልዾስ በቀሪ ዘመኑ ከተባረኩ 4 ደናግል ልጆቹ ጋር ሲሰብክ ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::

+” ሙሽራው ቅዱስ ሙሴ “+

✞✞✞ የዚህ ቅዱስ ወጣት ታሪክ ደስ የሚልም: የሚገርምም ነው:: በሮም ከተማ በምጽዋት: በጾምና በጸሎት ከተቃኙ ሃብታሞች (መስፍንያኖስና አግልያስ) ተወልዶ: በሥርዓቱ አድጐ: መጻሕፍትን ተምሮ በተክሊል አጋቡት::

+በሠርጉ ማግስት ሙሽሪትን ቢያያት በጣም ታምራለች:: “ይህ ሁሉ ውበትና ምቾት ከንቱ አይደለምን!” ብሎ በሌሊት ጠፍቶ: ነዳያንን መስሎ ከሮም ሃገረ ሮሆ (ሶርያ አካባቢ) ሔደ::

+በዚያም በፍጹም ምናኔ: በ7 ቀን አንዲት ማዕድ እየበላ: በረንዳ ላይ እየተኛና እየለመነ ለዓመታት ኖረ:: ሁሌም ቀን የለመነውን ማታ ለነዳያን አካፍሎ እርሱ ሲጸልይ ያድር ነበር:: በአካባቢው ክብሩ ሲገለጽበትም የሐዋርያውን የቅዱስ ዻውሎስን በረከት ፍለጋ ወደ ጠርሴስ ሔደ::

+ነገር ግን ጥቅል ነፋስ መርከቧን ገፍቶ ሮም አደረሳት:: ቅዱስ ሙሴም “የአምላክ ፈቃድ ነው” ብሎ በወላጆቹ ደጅ ተኝቶ ለ12 ዓመታት ተጋደለ:: ወላጆቹ ፈልገው ስላጡት በበራቸው የወደቀው ነዳይ እርሱ ይሆናል ብለው አልጠረጠሩም::

+ከብዙ ተጋድሎም በኋላም ዜና ሕይወቱን ጽፎ በዚህች ቀን: በዕለተ እሑድ ዐርፏል:: ጌታችንም “መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ ካልተጠራጠረ እምረዋለሁ” ብሎታል::

በዚያም ሕዝቡ: ካህናቱና ሊቀ ዻዻሳቱን ጌታ አዟቸው አግኝተውታል:: ወላጆቹ ማንነቱን በለዩ ጊዜም ታላቅ ለቅሶን አልቅሰዋል:: ሥጋውም ብዙ ተአምራትን አድርጉዋል::

+” ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ “+

✞✞✞ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ በሃገራቸው ልሳን ‘አብደል መሲሕ’ ይባላል:: ለቅዱስ ሙሴና ለሌሎችም ሙሽርነትን ትቶ መመነንን ያስተማረ እርሱ ነው:: አባቱ ታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሲሆን እናቱ መርኬዛ ትባላለች:: የጻድቃን ትውልድ የተባረከ ነውና (መዝ. 111:1) ታላቁ አቡነ ኪሮስ አጐቱ ናቸው::

+ስለዚህ ቅዱስ ምን እነግራቹሃለሁ! ሙሉ ታሪኩ ከቅዱስ ሙሴ ጋር ተመሳሳይ ነውና:: ልዩነቱ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ በገዛ ፍቃዱ አካሉ በመቁሰሉ ምክንያት ሰዎች ሊለዩት አልቻሉም ነበር::

+በአርማንያ: በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ደጅ ለ15 ዓመታት ሲጋደል ወደ ወላጆቹ ሃገር ቁስጥንጥንያ ተመልሶ ለ15 ዓመታት ተፈትኗል:: ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆንም የአባቱ ባሮች በጥፊ ይመቱት: ጽሕሙን (ጺሙን) ይነጩት: ቆሻሻ ይደፉበት: ሽንታቸውንም ይሸኑበት ነበር::

+ለእርሱ ወዳጆቹ ውሾች ነበሩ:: በአባቱ ደጅ ለ15 ዓመታት መከራን ከተቀበለ በኋላ “ጌታ ሆይ! የአባቴ አገልጋዮች በእኔ ላይ ያደረጉትን ሁሉ በደል አድርገለህ አትቁጠርባቸው” አለ:: በዚህች ቀን ሲያርፍም ጌታችን 7ቱን ሊቃነ መላእክት ከነ ሠራዊታቸው አስከትሎ ወርዶ በክብር አሳርጐታል:: አጠቃላይ የገድል ዓመታቱም 30 ናቸው::

አምላከ ቅዱሳን ለእነርሱ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

+ጥቅምት 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.አቡነ ዘሚካኤል (አረጋዊ)

2.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

3.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ

4.ቅዱስ ሙሴ መርዓዊ

5.ቅድስት እድና (የአረጋዊ እናት)

6.አባ ማትያስ (የአረጋዊ ረድዕ)

++”+ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም:: +”+ (ማቴ. 10:41)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

ምንጭ፡ Tewahedo ተዋህዶ  የፌስቡክ ገጽ

✞✞✞ ጥቅምት 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞