ነግህ በጊዜ ጸሎት አእዋፍ ሳይወነጭፍ
ከማለዳ ሰማይ ፀሐይ ሳትነጥፍ
ይሰማል አርጋኖን ከጉም ሽፋኗ ስር
አቋቋም ዝማሬ ነፍስን የሚያሸብር
ከሌሊት ወጋገን ከአናብርት ልቆ
ከአርያም ብሔር መድረሻውን አውቆ
የማኅሌት ክምር ኅሊና የሚሠውር
እንደ መላእክቱ በምስጋና መስከር
ይታየኛል ሕይወት ነፍስ የሚያለመልም
ከጉልላቷ ስር መቀነተ ማርያም
ፀሐይዋ ክርስቶስ በደም አንጿታል
እንደ ወይን ያማርሽ ሽቱሽ ይወደዳል
መልካሟ ርግቤ ሆይ ነይ ወደኔ ይላታል
ዛፎቿ ሐዋርያት ከላይ ተንዠርግገው
አጥሮቿ ቅዱሳን ዙሪያዋን ከልለው
በመቁጠሪያ ድርድር በብህትውና ውርስ
ይታያል ከመቅደስ የትሕትና ልብስ
በሰማዕታቷ ደም ቀይ ምንጣፍ ተነጥፋ
የዲያቢሎስ ስራይ ተን ሆኖ ሲጠፋ
ይታየኛል ጠጠር ከደጀ ሰላሟ ከስር የሚርመሰመስ
የመጉደፌን ድርሳን ምስጢር ተገልጦለት ውስጥ ዕንባዬን ሲያብስ
እማ ሐመረ ኖኅ የአብርሀም ድንኳን
የአዳም በአቱ የደሙ ቃል ኪዳን
ውቢቷ ሙሽራ ሐውልተ ያዕቆብ
ቤተ-ኤል ሰላም መዋቢያ አሸንክታብ

🍀🍀🍀🍀🍀🍀🍀🍀🍀🍀🍀🍀

     ✍️የሺወርቅ ቢተው
       ፍቅርተ ሥላሴ
ቤተ-ኤል