👉ጸሎት የምንጸልይባቸው የየራሳችን ምክንያቶች አሉን። እጅግ ብዙ። ጥሩ የትምህርት ውጤት፣ ጤና፣ የተሳካ ሥራ፣ መልካም ትዳር፣ ከህይወት ፈተና መራቅ፣ መልካም ቤተሰብ፣ ልጅ፣ ለንስሓ እና ቅዱስ ቍርባን መብቃት ወዘተ… የሰው ልጅ በዘመናት ለአምላኩ ከጸለያቸው ጸሎቶች መካከል ይገኙበታል። አዳም ከጸጋ ከተራቆተ በኋላ ከገጠመው የሕሊና ሕመም (የቀደመውን ደስታ እና ሰላም ማጣት) የተነሣ መንግሥተ ሰማያትን ይለምን ነበር። ሰው ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር አገብሮት መጸለዩ እንዳለ ሆኖ ትልቁ የጸሎት መነሻ ግን ማጣት ነው። የቀደመ ሰላም፣ ፍቅር፣ ትዳር፣ ልጅ፣ ጤና፣ የተስተካከለ ሕይወት በማጣት እግዚአብሔር ደጅ ለጸሎት የቆምነው እልፍ ነን።
👉አዳም መንግሥተ ሰማያትን፣ የቀደመ ክብሩን፣ የቀደመ ሰላሙን፣ የቀደመ ጤንነቱን አጥቶ ፤ ለንስሓ እና ለጸሎት እንደቆመ ማለት ነው። ጸሎቱ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ተሰማለት። ለመልሱ ተግባራዊነት ደግሞ 5500 ዘመንን ቆየ። እንደቆይታው ግን የማይፈጸም ይመስል ነበር። እግዚአብሔር መልሱን ለመስጠት 5500 ዘመን መቆየቱ የራሱ ምክንያት አለው! ልክ የእኛን ጸሎት መልስ ለመስጠት እንደሚዘገየው ማለት ነው። ብዙዎቻችን ከመዘግየቱ የተነሣ ተስፋ ከማጣት ጀምሮ እግዚአብሔርን እስከመካድ እንደርሳለን። ለአዳም 5500 ዘመን እንደቆየበት ምክንያት ለኛም ጥያቄ መዘግየት ምክንያቶች ምንድናቸው ሚለውን ለማሰብ ለአዕምሯችን ዕድል አንሰጠውም። ይልቁን የመልሱን መዘግየት እንደ መቅረት አድርገን እንገነዘባለን። ለረጅም ጊዜ ደጁ ተመላልሰን የጸለይነው ጸሎት መልስ አልባ መስሎ ይሰማናል።
👉እግዚአብሔር እኛ በፈልገነው ወቅት መልሱን ስላልሰጠን ተስፋ እንቆርጣለን። እግዚአብሔር ጨርሶ የተወን ያክል ይሰማናል።የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ ይህን ነገር ሲገልጥ “እንደማይሰጥ ይዘገያል” ይለዋል እግዚአብሔርን። እውነት ነው እግዚአብሔር መስጠቱ ለማይቀር ይዘገያል። የሚዘገይበትም የራሱ ምክንያቶች አሉት። እኛም ለመረዳት መሞከር ያለብን እነዚያን ምክንያቶች እንጂ መዘግየቱን እንደመቅረት መረዳት የለብንም። @ማኅበረ ቅዱሳን ሕዝብ ግንኙነት

“እንደማይሰጥ ይዘገያል” ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት