ሰው መሆንም ቀረ

አለምና ሐሰት ጋብቻ መስርተው

ውሸት የሚሉትን ቀጣፊ ልጅ ወልደው

ሲኖሩ… ሲኖሩ… ሲኖሩ… ተዋደው

ፍቅራቸው ሲደራ

ተጎራበቱና ከዲያቢሎስ ጋራ

ያው የጥንቱ ውሸት እረቀቅ አለና

የልጅ ልጅ አፈራ በእባብ ልቦና

እባብም ተማርካ በውዳሴ ከንቱ

አዳም እንቢ ቢላት ነግራ ለሴቲቱ

ቀንጥሰው ጎረሷት እፀ በለሲቷን

ሊበልጡ እግዚአብሔርን

አልሆነም ነገሩ አልሰመረም ምክሩ

የተገላቢጦሽ ዞረ አዳምም አፈረ

እንኳን እግዜር ሊኮን ሰው መሆንም ቀረ።

 

ምንጭ ሐመር 8 ዓመት ቁጥር 1 1992 ዓ.ም

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

በየዓመቱ መጋቢት 5 የምናከብረው በዓል አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያረፉበት በዓል ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋም በትምህርቷም ኹሉ እኒኽን ታላቅና ቅዱስ አባት ታነሣለች፤ ታወድሳለች፤ ተጋድሎአቸውንም ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡

ሀገራቸው ንሒሳ (ግብጽ) ሲኾን አባታቸው ስምዖን እናታቸውም አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዓመታት ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ እኛ አንድ ነገርን ለምነን በእኛ አቈጣጠር ካልተመለሰልን ስንት ቀን እንታገሥ ይኾን? ዛሬ በልጅ ምክንያት የፈረሱ ትዳሮች ስንት ናቸው? ለመኾኑ እግዚአብሔርን ስንለምነው እንደምን ባለ ልቡና ነው? ጥያቄአችን ፈጥኖ ላይመለስ ይችላል፡፡ ያልተመለሰው ለምንድነው ብለን ግን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “የምንለምነውን የማናገኘው በእምነት ስለማንለምን ነው፤ በእምነት ብንለምንም ፈጥነን ተስፋ ስለምንቆርጥ ነው” ይላል፡፡ ሰውን ብንለምነው እንደዘበዘብነው፣ እንደ ጨቀጨቅነው አድርጎ ሊቈጥረው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲኽ አይደለም፡፡ “ለምኑ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” ያለን ርሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ የሚያስፈልገን ከኾነ ያለ ጥርጥር ይሰጠናል፡፡ መቼ? ዛሬ ሊኾን ይችላል፤ ነገ ሊኾን ይችላል፤ ወይም እንደ ስምዖንና እንደ አቅሌስያ የዛሬ 30 ዓመት ሊኾን ይችላል፡፡ ጭራሽኑ ላይሰጠንም ይችላል፡፡ አልሰጠንም ማለት ግን ጸሎታችን ምላሽ አላገኘም ማለት አይደለም፡፡ የለመንነው እኛን የሚጎዳን ስለኾነ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሲሰጥ ስለ ፍቅሩ፤ ሲነሳም ስለ ፍቅሩ ነውና፡፡

(more…)

‹‹ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!››

ዘወትር ከአባታችን ሆይ ቀጥሎ በምናደርሰው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› በተሰኘው የጸሎት ክፍል ውስጥ ‹‹በሐሳብሽ ድንግል ነሽ በሥጋሽም ድንግል ነሽ›› የሚል የምስጋናና የምስክርነት ቃል ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በመልክዓ ማርያም ውስጥም ‹‹ሰላም ለሕሊናኪ ሐልዮ ሠናያት ልማዱ ወገቢረ ምሕረት መፍቅዱ›› ማለትም ‹‹ምሕረት ማድረግ ለሚወድ መልካም መልካሙን ማሰብ ልማዱ ለሆነ ሕሊናሽ ሰላም እላለሁ!›› የሚል የምስጋና ቃል አለ፡፡ የተአምረ ማርያም መቅድም ደግሞ የድንግል ማርያምን ሕሊና ከመላእክት ሕሊና ጋር ያስተያይና በልጦ ሲያገኘው በመደነቅ እንዲህ እያለ ያመሰግናል፡፡ ‹‹ሥጋዊ ነገር ከማሰብ መጠበቅ ከአዳም ልጆች ለማን ተሰጠው? ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ለመላእክት እንኳን አልተቻላቸውም፡፡ በቀደመው ወራት ያልተሰጣቸውን ሽተው በድለው ከሰማይ ወደ ምድር ወርደዋልና፡፡›› ከዚህም ጋር አያይዞ ‹‹የእመቤታችን ማርያም አሳብ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› ይህም አሳብዋ ንጹሕና መልካም ብቻ መሆኑን ያስረዳናል፡: እኛ ክርስቲያኖች ‹‹እግዚአብሔርን እንድንመስል›› ታዘናል፡፡ (1ጢሞ4.7-8፤ 1ቆሮ11.1) ይህም በመልክ አይደለም፡፡ በሥራና በአመለካከት እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን በአመለካከት መምሰል የማይቻል ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔርን ምሰሉ አንባልም ነበር፡፡ በመልክ ስለመምሰል የሚናገር ቢሆን ኖሮ ደግሞ መልክን የሚፈጥረው ፈጣሪ ስለሆን ‹‹ምሰሉ›› አንባልም ነበር፡፡ የሚደንቅ ነው! እኛ ፈጣሪን በአሳብና በአመለካከት እንድንመስለው ታዘዝን፡፡ ድንግል ማርያም ግን መስላ ስለተገኘች ‹‹አሳብዋ እንደ አምላክ አሳብ ነው፡፡›› የሚል ምስክርነት ተሰጠላት፡፡ ቀደም ሲል ስለ ድንግል ማርያም ፍጹም የሕሊና ድንግልናና በጎነት ከአዋልድ መጻሕፍት ያስቀደምኩት ሆን ብዬ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚደግፈው ማሳየት ያስፈልጋልና እነሆ!

(more…)

መንፈሳዊነት ምንድነው ?

ለመሆኑ መንፈሳዊነት ምንድን ነው፡፡ ረዥምቀሚስ መልበስ ነው? ፀጉርን በአሮጌ ሻሽ መሸፈን ነው? ገላን ያለመታጠብ ነው? አንገትን መድፋት ብቻ ነው? ቀስ ብሎ መናገር ነው? ኋላ ቀርነት ነው? አይመስለኝም፡፡ ቴሌቭዥን አለማየት፣ኢሜይል አለመጠቀም ነው? ከጸሎት መጻሕፍት በቀር ሌላ ነገር አለማንበብ ነው? መንፈሳዊነትኮ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው፡፡ ራስን ማሸነፍ ነው፡፡ አእምሮን እና ልቡናን ቀና እና ሰላማዊ ማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ የውስጡ መንፈሳዊነት አይደለም እንዴ ወደላይ መገለጥ ያለበት፡፡ ስለ ሐዋርያት ስንናገርኮ የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ቅድስና ለልብሳቸው፣ የልብሳቸው ቅድስና ደግሞ ለጥላቸው ተረፈ ነው የምንለው፡፡ መንፈሳዊነቱ ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ ወደ ውስጥ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ «መንፈሳዊነት» ከ «መንፈሳይነት» ጋር እየተመሳሰለ የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ነው ይህችን ቃል ያመጣት፡፡ ከሁለት ቃላት «መንፈሳዊ» እና «መሳይ» ከሚሉ ቃላት ቆራርጦ «መንፈሳይ» የሚል ቃል ፈጠረ፡፡ ትርጉሙም «መንፈሳዊ መሳይ» ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈሳውያን ይመስላሉ እንጂ አይደሉም፡፡

አባ ኤፍሬም ሶርያዊ ባስልዮስን ለማየት በሄደ ጊዜ ስለ ክብረ ወንጌል ሲል ከላዩ የወርቅ ልብስ ለብሶ ፣ የወርቅ ወንበር ዘርግቶ፣ የወርቅ ጫማ ተጫምቶ በጉባኤው ላይ ባየው ጊዜ «ደገኛ መምህር የተባለው ባስልዮስ ይኼ ነውን?» ብሎ ነበር፡፡ በኋላ ግን ተአምራቱን አይቶ አድንቆታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የውጭ ገጽታ ውስጥን ሊገልጥም ላይገልጥም ይችላልና፡፡ ልክ ነው ክርስቲያናዊ አነጋገር፣ አለባበስ፣ አረማመድ፣ ገጽታ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት መንፈሳዊነት ጅልነት፣ ከርፋፋነት፣ ኋላ ቀርነት ወይንም ደግሞ፣ ንጽሕናን አለመጠበቅ ማለት ግን አይደለም፡፡ በመንፈሳዊነታቸው የሚደነቁት የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ባስልዮስ ዘቂሳርያ በዘመኑ በነበረው የግሪክ ፍልስፍና እና ዕውቀት የበለጸጉ ነገር ግን ዕውቀታቸውን እናሥልጣኔያቸውን በወንጌል የቃኙ ነበሩ፡፡

ብዙዎቻችን ከውስጥ ለሚመነጩ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ታዛዥነትን፣ ትኅትናን፣ አርቆ ማሰብን፣ ኀዘኔታን፣ ፍቅርን፣ ትጋትን ለመሰሉ ነገሮች ትኩረት አንሰጥም፡፡ ከዚያ ይልቅ ተዋንያን ሊያደርጉት የሚችሉትን የውጭ ገጽታን ብቻ በማየት መመዘን እንመርጣለን። እውነተኛው መንፈሳዊነት ግን ከመንፈሳይነት መለየት አለበት፡፡ መንፈሳይ ሰዎች የራሳቸው መለያ ባሕርያት አሏቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከውስጣዊ መንፈሳዊነት ይልቅ ለውጫዊ ነገሮች ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ማንነታቸውን ለመሸፈን ሲሉ ሕግ ከሚፈቅደው በላይ ለውጫዊ ገጽታ ይጨነቃሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ የፀጉር አያያዝ የራስዋ ባህል አላት፡፡ እነርሱ ግን ፀጉር መታጠብን ኃጢአት ያደርጉታል፡፡ ክርስቲያኖች የሚለብሱት ልብስ ራሳቸውን የማያጋልጥ እንዲሆን ትመክራለች፡፡ እነርሱ ግን ልብስ ሁሉ መሬት ካልጠረገ ይላሉ፡፡ ያደፈ በመልበስ፣ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ይመስል እጅግ ቀሰስ ብለው በመናገር፣ ሰው መሆናቸውን ረስተው ምንም ነገር እንደማይበሉ እና እንደማይጠጡ በማሳመን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በመልበስ፣ ሰንሰለት በመታጠቅ፣ ትልልቅ መቁጠርያ እጃቸው ላይ በመጠቅለል፡፡ ይበልጥ መንፈሳዊ ሆነው መታየት ይፈልጋሉ፡፡

ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው በዱርዬ እና በሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ያለውን ያህል ፈሪሃ እግዚአብሔር በአገልጋዮች ዘንድ የለም ይል ነበር፡፡

አንዳንዶች በአገልግሎት እየበረቱ ሲሄዱ ከመንፈሳዊነት ወደ መንፈሳይነት ስለሚለወጡ፡፡ጋሽ ግርማ ከበደ ከሚያስተምረው ነገር የማልረሳው ቃል አለ፡፡ «ሰው የሚጠላውን ኃጢአት ደጋግሞ ይሠራዋል» ይላል፡፡ ለምንድን ነው ደጋግሞ ይሠራዋል ያለው? እኔ እንደ ተረዳሁት መጀመርያውኑ ይህ ሰው ውስጡ ያላመነበትን እና ሊያደርገው የማይፈልገውን ነገር ነው ለማስመሰል ሲል እያወራ ያለው፡፡ ስለዚህም በውስጡ ያንን የጠላውን ነገር ላለማድረግ መንፈሳዊ ተጋድሎ ስለማያደርግ ደጋግሞ ሲሠራው ይገኛል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች መንፈሳያን ስለ አንድ

ሰው መንፈሳዊነት ደጋግመው በጥላቻ ወይንም በንቀት፣ ወይንም ደግሞ በመመጻደቅ የሚያወሩ ከሆነ ያንጊዜ አንዳች ነገር ተረዱ፡፡ ሳያስቡት እየተናገሩ ያሉት ስለ ራሳቸው ነው፡፡ መንፈሳውያን ሰዎች ስለሌሎች ውድቀት ሲያነሡ ከርኅራኄ እና ከኀዘኔታ ጋር ነው፡፡ የደስታ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ እንደ ጀብዱም አይቆጥሩትም፡፡ ለዚህም ነው በቅዳሴ አትናቴዎስ ሊቁ ስለ አዳምና ሔዋን አንሥቶ «እኛስ እናንተን ልንወቅሳችሁ አንችልም» በማለት የተናገረው፡፡ መንፈሳውያን ይነበባሉ፤መንፈሳያን ግን ይታያሉ፡፡ መንፈሳውያን ይቀመሳሉ፣ መንፈሳያን ግን ይላሳሉ፡፡ መንፈሳውያን ያዳምጣሉ፤ መንፈሳያን ግን ይለፈልፋ፡፡ መንፈሳውያን ያስተውላሉ፤ መንፈሳያን ግን ይቸኩላሉ፤ መንፈሳውያን ያጠግባሉ፣

መንፈሳያን ግን ያቁለጨልጫሉ፡፡ መንፈሳውያን ይመዝናሉ፤ መንፈሳያን ግን ያፍሳሉ፡፡ መንፈሳውያን ያርማሉ፤ መንፈሳያን ግን ይተቻሉ፡፡ መንፈሳውያን ጠላቶቻቸውን አንድ ሺ ዕድል ይሰጣሉ፤ መንፈሳያን ግን ወዳጆቻቸውን ጠላቶቻቸው ለማድረግ አንድ ሺ በር ይከፍታሉ፡፡ መንፈሳውያን ይጾማሉ፣ መንፈሳያን ይራባሉ፤ መንፈሳውያን ይጸልያሉ፣ መንፈሳያን ግን ይናገራሉ/ያነባሉ፡፡ መንፈሳውያን ሱባኤ ይይዛሉ፣ መንፈሳያን ግን ስለ ሱባኤያቸው ያወራሉ፡፡ መንፈሳውያን ይሰጣሉ፣ መንፈሳያን ግን ሲሰጡ ያሳያሉ፡፡ መንፈሳውያን ቃለ እግዚአብሔርን ያስተምራሉ፣ መንፈሳያን ግን በራሳቸው ቃላት ይጠበባሉ፤ መንፈሳውያን ወደ ውስጥ፣ መንፈሳያን ወደ ውጭ ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን የነገን፣ መንፈሳያን የዛሬን ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን ምክንያቱን፣ መንፈሳያን ድርጊቱን ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን ራሳቸውን፣ መንፈሳያን ሌላውን ያያሉ፡፡

መንፈሳውያን ከመፍረዳቸው በፊት ይመክራሉ፤ መንፈሳያን ከፈረዱ በኋላ ይመክራሉ፡፡ መንፈሳውያን ዘጠኝ ጊዜ ለክተው አንድ ጊዜ ይሰፋሉ፣ መንፈሳያን ግን ዘጠኝ ጊዜ ሰፍተው አንድ ጊዜ ይለካሉ፡፡ መንፈሳውያን ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፣ መንፈሳያን ከተናገሩ በኋላ ያስባሉ፡፡ መንፈሳውያን ይወስናሉ፣ መንፈሳያን አስተያየት ያበዛሉ፡፡ መንፈሳውያን ሰው እንዳይሞት በችግሩ ጊዜ ይረዳሉ፣ መንፈሳያን ግን ሰው ሲሞት የልቅሶ ትርኢት ያሳያሉ፡፡ መንፈሳውያን ስለ ሌሎች በጎ መናገርን ያዘወትራሉ፣ መንፈሳያን ስለ ራሳቸው በጎ መናገርን ይፈልጋሉ፡፡ መንፈሳያን ነጭ እና ጥቁር ብቻ ያያሉ፣ መንፈሳውያን ግን ግራጫንም ጨምረው ይመለከታሉ፡፡ መንፈሳዊ ሰው አንድ ሰው ነው፡፡ መንፈሳይ ሰው ግን ሁለት ሰው ነው፡፡ ውጩ ሌላ ውስጡ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ገና ያልተሸነፈ፣ እንዲያውም እየገነገነ እና እየገነተረ የሚሄድ ክፉ ጠባይ አለባቸው፡፡ አይጋደሉትም፡፡ አይጸየፉትም፡፡ ሊያሸንፉት አይፈልጉም፡፡ አይቃወሙትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ጥሩ ተዋናይ በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በአረማመድ፣ በመቅለስለስ፣ በመሸፋፈን እና ለሰው መስለው በመታየት ሊገልጡት የሚፈልጉት ሌላ ማንነት ደግሞ አላቸው፡፡ ይህ የውስጥ ማንነት አንድ ቀን ያሸንፍና እንደ ዴማስ ያስኮበልላቸዋል፡፡ ያን ጊዜ በሰው ይፈርዱ የነበሩትን ነገር ሁሉ አብዝተው ያደርጉታል። ወጣ ወጣ እና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ የተባለው ይደርስባቸዋል፡፡ አንዳንዴ መንፈሳይነት ሕይወት ሳይሆን በሽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያውም የአእምሮ መዛባት/ mental disorder/፡፡ በሁለት ማንነቶች መካከል እየተምታቱ መኖር፡፡ መንፈሳዊ ሰው ኃጢአት ቢሠራ እንኳን ንስሐ ይገባበታል፡፡ ያርመዋል፡፡ ይጋደልበታል፡፡ ኃጢአቱን በመሸፈን እና በማስመሰል ሳይሆን በመጋደል እና በማስወገድ ያምናል፡፡ መንፈሳይ ሰው ግን ሌሎች እንዳያዩት እንጂ እግዚአብሔር እንዳያየው አይጨነቅም፡፡ አሁን እኛ እስኪ ራሳችንን እንየው መንፈሳዊ ነን ወይስ መንፈሳይ?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዘጋጅ፡ ኃይለ ገብርኤል

ጸሐፊ፡- ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ታላቁ አባት አባ አቡነ ሙሴ ጸሊም

አቡነ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ተጋድሎአቸውን የፈጸሙት ግን በግብፅ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ እንደ አብርሃም በየዋህ ልቡና ሆነው ስነ ፍጥረትን በመመራመር እግዚአብሔር አምላካቸውን ያገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወላጆቻቸው ፀሐይ ያመልኩ ስለነበር ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃጢአት በሠሩ ቁጥር ‹‹ተው አምላካችን ፀሐይ ይጣላሃል›› ይሏቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ባደጉ ጊዜ ቀማኛ ዘራፊ ሆኑ፡፡ እየዘረፉ ብዙ ይመገቡ ስለነበር ከትልቅነታቸውና ኃይለኛነታቸው የተነሳ ‹‹በገ ፈጅ›› እየተባሉም ይጠሩ ነበር፡፡
ብዙ ወርቅ ከባለ ሀብቶች ሰብስባ ለነዳያንና ለቤተክርስቲያን ልትሰጥ ትሄድ የነበረችን አንዲት ክርስቲስቲያን ሴት ልጅ ሙሴና ግብረ አበሮቻቸው ለወርቁ ሲሉ እርሷንም ማርከው ወሰዷት፡፡ ማታ ላይ ስለ ውበቷ ሲያወሩ እርሷ ግን ‹‹ስምህ ማን ነው?›› ስትላቸው ‹‹ሙሴ ነኝ›› ቢሏት ‹‹ይሄ ስምኮ እጅግ የተባረከ ስም ነው….›› ብላ ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴና ስለ ክርስቶስ አስረዳቻቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በወላጆቻቸው ስለ ፀሐይ አምላክነት ሲነገራቸው ያደጉትን ነገር መመርመር ጀመሩ፡፡ ‹‹ፀሐይ አምላክ ከሆነ እስከዛሬ ድረስ ሽፍታና ዘራፊ ሆኜ ሰው ስገድልና ይህን ሁሉ ኃጢአት ስሠራ እንዴት ፀሐይ ሳታቃጥለኝ ቀረች? ደግሞም ፀሐይ ጠዋት ወጥታ ማታ ትጠልቃለች ይህችስ እንዴት አስገኚ ልትሆን ትችላለች ለራሷ አስገኚ አላት እንጂ…›› በማለት ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ እሳትን፣ ነፋስን በየተራ አምላክ መሆናቸውን አለመሆናቸውን በሚገባ ከፈተኑና ከመረመሩ በኋላ ‹‹የፀሐይ የጨረቃ የሁሉ አስገኚ አምላክ ተናገረኝ›› ብለው ሲጸልዩ ከሰማይ ድምፅ መጥቶላቸው ወደ ገዳም ሄደው ከአባቶች ትምህርተ ሃይማኖትን እንዲማሩ ተነገራቸውና ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደው መምህር ኤስድሮስ ሁሉንም ነገር አስተምረው ለማዕረገ ምንኩስና አበቋቸው፡፡
መጀመሪያ ወደ ገዳሙ ሲሄዱም ይዘርፉበትና ይቀሙበት የነበረውን ስለታም መሣርያ እንደያዙ ስለነበር ያዩአቸው መነኮሳት ሁሉ ‹‹ሊገድለን መጣ›› ነበር ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ለመነኮሳቱ ሁሉ የሚላላኩ ሆኑ፡፡ ትንሹም ትልቁም ‹‹ሙሴ ይህን አድርግልኝ›› ይሉታል እርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፡፡ ራሱን በትሕትና ዝቅ በማድረግ በተጋድሎ እየኖረ ተአምራትን ማድረግ ጀመረ፡፡ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንብ ነበር፤ ለቅድስና ደረጃ ከበቁም በኋላ 40 ዓመት ሙሉ ከሰው ሳይገናኙ ብቻቸውን ዘግተው ከኖሩ በኋላ ለ500 መነኮሳት አበምኔት ሆነው ተሾሙ፡፡ ቀን ወንጌል ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት እየተነሱ ከበረሃ ሄደው ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዱላቸው ነበር፡፡ አገልግሎታቸው የታይታ እንዳይሆንባቸው አረጋውያን መነኮሳት መተኛታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የግብፅ በረሃን አቋርጠው ከሩቅ ሥፍራ ሄደው ውኃ እየቀዱ መነኮሳቱ ሳያዩአቸው በየደጃፋቸው ላይ ያስቀምጡላቸው ነበር፡፡
ብዙ መነኮሳትም ወደ አቡነ ሙሴ እየመጡ የሕይወትን ትምህርት ይማሩ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባ ሙሴም ‹‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት›› አሉት፡፡ ‹‹ሌላ አይጠበቅበትምን?›› ሲል ያ ወንድም ጠየቃቸው፡፡ ‹‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ኃላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልንጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብፅን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም›› ብለው መለሱለት፡፡ ያም ወንድም ‹‹ምን ማለት ነው?›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሀሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው…›› ብለው መከሩት፡፡

በዕድሜአቸው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ለመቀበል ከመነኮሳት ደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር ወደ አባ መቃርስ ሄዱ፡፡ አባ መቃርስም ‹‹ልጆቼ ከናንተ መካከል በሰማዕትነት የሚሞት›› አለ ብለው ትንቢት ሲናገሩ ሙሴ ጸሊምም ‹‹አባቴ ያ ሰው እኔ ነኝ፣ ‹ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ› የሚል ቃል አለ፡፡ ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር›› አላቸው፡፡ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ዘርፈው መነኮሳቱን ሊገድሉ ሲመጡ ደቀመዛሙርቶቻቸው ‹‹ሸሽተን እናምልጥ›› ሲሏቸው አቡነ ሙሴ ግን ‹‹በጎልማሳነቴ ጊዜ ደም አፍስሼያለሁና አሁን የእኔም ደም ሊፈስ ይገባል›› በማለት ራሳቸውን ለመሰየፍ አዘጋጅተው ጠበቋቸውና በርበሮች ሰኔ 24 ቀን አንገታቸውን በሰይፍ ቆርጠዋቸዋል፡፡ ፈርተውና ሸሽተው የነበሩት ደቀመዛሙርቶቻቸውም ተመልሰው አብረዋቸው ተሰይፈዋል፡፡
የአባታችን የሙሴ ጸሊም ቅዱስ ሥጋቸው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፡፡ ግብፆች አቡነ ሙሴ ጸሊምን በእጅጉ ያከብሯቸዋል፡፡ በስማቸው ጽላት ቀርጸው ቤተክርስቲያን ሠርተው ሥዕላቸውን አሠርተው ገድላቸውን ጽፈው በስንክሳራቸው መዝግበው የዕረፍታቸውን መታሰቢያ በደማቅ ሁኔታ ነው የሚያከብሩት፡፡ የአቡነ ሙሴ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሥራህን ሥራ፤ ሌሎችን እርዳ፤ የሚጠቅም ሰውም ኹን! በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

 

ሌሎች ሰዎችን ከማያድን ክርስቲያን በላይ የከፋ ምንም የለም፡፡ አንተ ሰው! ድኻ ነኝ የምትለኝ ለምንድን ነው? ኹለት ዲናር የጣለችዋ ሴት ትፋረድባሃለች፡፡ ከምናምንቴ ቤተ ሰብ እንደ ተወለድክ የምትነግረኝስ ለምንድን ነው? ሐዋርያትም ምናምንቴዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ታላላቅ መኾን ተችሏቸዋል፡፡ አለመማርህን ሰበብ አድርገህ አትንገረኝ፤ ሐዋርያትም ያልተማሩ ነበሩና፡፡

ባሪያ ብትኾንም እንኳ፣ ስደተኛ ብትኾንም እንኳ ሥራህን መሥራት ይቻልሃል፤ ሌሎችን መርዳት ይቻልሃል፤ ሰዎችን ማዳን ይቻልሃል፥ አናሲሞስም እንደ አንተ ዓይነት ሰው ነበርና (ፊልሞ.1፡10-11)፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ምን ወዳለ ማዕረግ ከፍ እንዳደረገውና ምን ብሎ እንደ ጠራው አድምጥ፡- “በእስራቴ ስለ ወለድሁት፡፡”

ወዳጄ ሆይ! እኔ እንኳን ሕመምተኛ ነኝ ብለህ አትንገረኝ፤ ጢሞቴዎስም እንደ አንተ ዘወትር ይታመም ነበር፡፡

ፍሬ የማያፈሩ ዛፎች እንደ ምን ብርቱዎችና ተወዳጆች፣ ግዙፋንና ሐመልማላውያን እንደዚሁም ረጃጅም እንደ ኾኑ አላየህምን? የፍራፍሬ ቦታ ቢኖረን ግን ፍሬ የሚያፈሩት ሮማንንና ወይራን እንተክላለን እንጂ እነዚህ ፍሬ የማይሰጡንን ዛፎች አንተክልም፡፡ ምክንያቱም እንዲሁ ለዓይን ማረፊያ ለማየት ካልኾነ በስተቀር ሌላ ጥቅም የላቸውምና፡፡

የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚመለከቱ፣ ሌሎች ሰዎችንም የማይረዱ ክርስቲያኖችም እንደ እነዚህ ዛፎች ናቸው፡፡ እንዲያውም ከእነዚህ ዛፎችም የባሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የሚቆረጡት ለእሳተ ገሃነም ነው፡፡ ዛፎቹ ግን ቢያንስ ቢያንስ ጠረጴዛም ወንበርም ለመሥራት ይጠቅማሉ፡፡ ለቤት መሥሪያ ይጠቅማሉ፡፡ አጥር ቅጥር ኾነው ያገለግላሉ፡፡

እነዚያ አምስቱ ደናግል እንደዚህ ነበሩ (ማቴ.25፡1)፡፡ ርግጥ ነው ንጽህናቸውን የጠበቁ ነበሩ፡፡ ለሚያያቸው ኹሉ ግሩም የኾነ ጠባይ የነበራቸው ነበሩ፡፡ ሥርዓት ያላቸው ነበሩ፡፡ ይህ ኹሉ ግን ምንም አልጠቀማቸውም፡፡ ወደ እሳተ ገሃነም ከመጣ’ል አልታደጋቸውም፤ ዘይት የተባለው ምጽዋት አልነበራቸው’ማ! ክርስቶስን በነዳያን አማካኝነት የማይመግቡትም ዕጣ ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው ይኸው ነው – የሰነፎቹ ደናግል ዕጣ!

አንተ ሰው ልብ ብለህ አስተውል! እነዚህ ደናግል በግል ኃጢአታቸው አልተነቀፉም፡፡ በዝሙት ወይም በሐሰት ምስክርነት አልተወቀሱም፡፡ በፍጹም! ይልቁንም የተነቀፉትና የተወቀሱት ሌሎች ሰዎችን ባለመጥቀማቸው ነው፡፡

እንደዚህ ከኾነ ታዲያ ሰዎች ክርስቲያን ተብለው ሊጠሩ የሚችሉት በምን መመዘኛ ነው? እኮ በምን መስፈርት? አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ! በሊጥ ውስጥ የተጨመረ እርሾ ሊጡን እንዲቦካ ካላደረገው እንዲሁ እርሾ ተብሎ መጠራት ብቻውን ምን ይረባዋል? ዳግመኛም ወደ እርሱ የቀረቡትን ሰዎች መዓዛው ካልሸተታቸውና ቤቱን ካላወደው በቀር ከርቤ በከርቤነቱ ምን በቁዔት አለው?

ሌሎች ሰዎችን መርዳት አይቻለኝም ብለህ አትንገረኝ፡፡ እንዲያውም ልንገርህ፤ አንተም ስማኝ፡- አንተ በእውነት ክርስቲያን ከኾንክ ሌሎች ሰዎችን አለመርዳት የማይቻል ነው፡፡ ዕጣን መዓዛ እንዲኖረው፣ እርሾም ሊጥን እንዲያቦካ ተፈጥሮው እንደ ኾነ ኹሉ፥ አንድ ክርስቲያንም በስም ክርስቲያን ከመባል አልፎ በእውነት ያለ ሐሰት ክርስቲያን ከኾነ ሌሎች ሰዎችን መርዳት መቻሉ፣ ሌሎችን የሚጠቅም ሥራ መሥራቱ ክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ነው፡፡

ስለዚህ አይኾንልኝም፤ አይቻለኝም በማለት እግዚአብሔርን አታማርር፡፡ ፀሐይ ብርሃኗን በእኔ ላይ ማብራት አይቻላትም ካልክ ፀሐይን እየሰደብካት ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ አንድ ክርስቲያንም ሌሎች ሰዎችን ሊጠቅማቸው አይችልም የምትል ከኾነ እግዚአብሔር እየሰደብክ [ሎቱ ስብሐትና] ሐሰተኛም እያደረግኸው ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን ሌሎች ሰዎችን ካለመርዳትና ካለመጥቀም ይልቅ ፀሐይ ሙቀትና ብርሃን ባትሰጥ ይቀላል፡፡ እንደዚህ ከሚኾን ብርሃን ወደ ጨለማ መቀየር ይቀላል፡፡

እናስ? እና’ማ አይቻለኝም አትበለኝ፡፡ የማይቻለው መርዳት አለመቻል ነውና፡፡ አይኾንልኝም እያልክ በከንቱ እግዚአብሔርን አታማርር፡፡

ሕይወታችንን በአግባቡና በሥርዓቱ የምንመራ ከኾነ እነዚህን ነገሮች ኹሉ በቀላሉ ማድረግ ይቻለናል፤ እነዚህ ነገሮች ሊደረጉ ግድ ነው፡፡ በመቅረዝ ላይ የተቀመጠ ሻማ ብርሃኑን መደበቅ እንደማይቻለው ኹሉ ክርስቲያንም የእውነት ክርስቲያን ከኾነ ብርሃኑም መሸሸግ አይቻለውም፡፡ ስለዚህ እውነተኞች ክርስቲያኖች ከኾንን ሌሎች ሰዎችን መርዳት መጥቀምም ችላ አንበል፡፡

ምንጭ፡ (መቅረዝ ዘተዋሕዶ)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መንፈሳዊ ዕድገት በቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ

አንድ አገልጋይ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እየተጠቀመ መሆኑ የሚታወቀው የአገልግሎት ዘመኑ እየጨመረ ሲሄድ ትኅትናው እየጨመረ ከመጣ ነው፡፡ የአገልግሎት ብርታትና ጥንካሬ በዕውቀት መጨመር ወይም በታዋቂነት ብዛት ብቻ አይለካም፡፡ ብዙ ቦታዎችን በማዳረስና ብዙ ነገሮችንም በመሥራት ብቻ አይመዘንም፡፡ ከኢየሩሳሌም ያልወጣው ቅዱስ ያዕቆብ ነው ከሐዋርያት መካከል የመጀመሪያውን አክሊል የተቀዳጀው(የሐዋ12)፡፡ ከፊት በመምጣት ወይም ከኋላ በመነሣትም አይታወቅም፡፡ መጀመሪያ ከተጠሩት ወገን የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስና በመጨረሻ የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ በአንድ ቀን ነው የሰማዕትነት አክሊል የተቀበሉት፡፡ ሊቁ አውግስጢኖስ ‹ኢየሱስ ክርስቶስ አልፋና ዖሜጋ ስለሆነ. ነው ይላል፡፡

የአገልጋይ ብቃት በዋናነት የሚለካው በትኁት ሰብእና ነው፡፡ ይበልጥ ባገለገለ ቁጥር ይበልጥ ክርስቶስን ያውቃል፡፡ ይበልጥም ክርስቶስን ባወቀ ቁጥር ይበልጥ ራሱን ያውቃል፡፡ ይበልጥ ራሱን ባወቀ ቁጥርም ይበልጥ ድካሙን ይረዳል፤ ይበልጥ ድካሙን በተረዳ ቁጥርም ይበልጥ ትኁት ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀመው ራሳቸውን የሚያውቁ አገልጋዮችን በማፍራት እንጂ ብዙ ነገር የሚያውቁ አገልጋዮችን በማፍራት አይደለም፡፡ ዕውቀት የሚጠቅመው ራስን በማወቅ ውስጥ ከተቀመጠ ነው፡፡ ያለበለዚያ ዕውቀት ያስታብያል(1ኛቆሮ. 8÷1)፡፡

 

እግዚአብሔርን አሟልቶ ማወቅ አይቻልም፡፡ ትምህርቶች ሁሉ የሚጠቅሙን እግዚአብሔርን ለማወቅ አይደለም፡፡ ስለ እግዚአብሔር ለማወቅ እንጂ፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅ የሚቻለው ከእግዚአብሔር ጋር በመኖር ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ማወቃችን የሚጠቅመን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ነው፡፡ የተጠቀመ ሰው ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ አልፎ እግዚአብሔርን ወደማወቅ ይሸጋገራል፡፡ አገልጋይን ስለ እግዚአብሔር ከማወቅ እግዚአብሔርን ወደማወቅ የሚያሸጋግረው ትኁት ሰብእና ነው፡፡

ይህ ትኁት ሰብእና የሚገኘውም ራስን በማወቅ ነው፡፡ ሰው ራሱን ካላወቀ እግዚአብሔርን አያውቅም፡፡ በቀኝ በኩል የተሰቀለው ሽፍታ ክርስቶስን ማወቅ የቻለው መጀመሪያ ራሱን ስላወቀ ነው፡፡ የራሱን በደልና ኃጢአት፣ የተፈረደበትም ትክክል መሆኑን ተረዳ፡፡ ስለዚህም ከጎኑ የተሰቀለውን፣ አይሁድ ወንበዴ ነው ብለው የሰቀሉትን ክርስቶስን ንጹሕ ነው ብሎ ለመመስከር፣ ‹በመንግሥትህ አስበኝ› ብሎ ለመለመን አልከበደውም፡፡ ራስህን በምእመናን ካየኸው ታላቅ ነህ፤ ራስህን በክርስቶስ ካየኸው ግን ትንሽ ነህ፡፡

ከቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት የምንማረው ይኼንን ነው፡፡ ይበልጥ ባገለገለ ቁጥር ይበልጥ ትኁት ይሆን ነበር፡፡ ይበልጥ በተገለጠለትም ቁጥር ይበልጥ ስለ ራሱ ማንነት ይገነዘብ ነበር፡፡ የአገልግሎቱ ዘመናት በጨመሩ ቁጥር የቅዱስ ጳውሎስም ትኅትና በዚያው ልክ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያዋን መልእክቱን ለገላትያ ሰዎች በ48 ዓ.ም. አካባቢ ሲጽፍላቸው ራሱን የጠራው ‹የክርስቶስ ባሪያ› ብሎ ነው፡፡ ያ እስከ ሦስተኛው ሰማይ የተነጠቀ፣ በፍኖተ ደማስቆ በድንቅ ሁኔታ የተጠራ፣ ከእናቱ ማኅጸን የተመረጠ(ገላ.1÷15) ሐዋርያ ራሱን ‹ባሪያ› ይለዋል፡፡ በ49/50 ዓ.ም. መጀመሪያ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ ደግሞ ‹ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ› ሲል ነው ራሱን የገለጠው (ሮሜ.1÷1)፡፡ ይህ ጊዜ ብዙ ታዋቂነት ያገኘበትና የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉዞውን ያደረገበት ወቅት ነው፡፡

በዚሁ ዓመት መጨረሻ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ ይበልጥ ትኅትናው ጨመረ፡፡ ራሱንም ‹ጭንጋፍ የምሆን …እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ … ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ› ሲል ገለጠው፡፡ ይህንን ያለው በልብሱ ቅዳጅ ተአምራትን ካደረገ(የሐዋ. 19÷11)፣ አጋንንት ከተገዙለትና ጉባኤው ከሰፋለት በኋላ ነው፡፡ በዓመቱ በ50 ዓ.ም. በተላከችው ሁለተኛዋ የቆሮንቶስ መልእክቱም ሰማያዊውን መገለጥ ከነገረን በኋላ ስለ ራሱ የሚሰማውን ሲነግረን ‹ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ› ይላል (2ኛቆሮ. 12÷7)፡፡ ራሱንም እንደ ኢትዮጵያ የአብነት መምህራን ከተማሪዎቹ እንደ አንዱ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በ54 ዓ.ም. በላከው መልእክቱ እንደ ቀድሞው ራሱን ‹የክርስቶስ ባሪያ› ብሎ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ ታዋቂው፣ ጸጋው የበዛለት፣ እስከ ሦስተኛው ሰማይ የተነጠቀው የሚለውን አልተጠቀመም፡፡ ያገኘውን ነገር የሚገልጥልን መንገር አስፈላጊ የሚሆንበት ግዳጅ ሲመጣ ነው፤ ያንንም ራስን ከመውቀስ ጋር ነው፡፡

ከዓመት በኋላ በ55 ዓ.ም. ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ ላይ የቅዱስ ጳውሎስ ትኅትና ይበልጥ ጨመረ፡፡ ያፈራ ወይን፣ ያዘለዘለም ገብስ ከፍሬው ብዛት ወደ መሬት ጎንበስ ይላል፡፡ ፍሬ የሞላው አገልጋይም ትኅትናው ይጨምራል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲሁ ነው፡፡ ይህ ወቅት በሮም የታሠረበት ወቅት ነው፡፡ እርሱ ግን በፍሬው ብዛት ጎንበስ አለ፡፡ ስለ ራሱም እንዲህ አለን ‹ከዘላለም የተሠወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለእኔ ተሰጠ› (ኤፌ. 3÷9)፡፡ እየበቃ ሲሄድ እያነሰ መጣ፡፡ ከፍ እያለ ሲሄድ ዝቅ እያለ መጣ፡፡

በሮም እሥር ላይ እያለ ከጻፋቸው መልእክቶች አንዷ በሆነችው የ55 ዓ.ም. የፊልጵስዩስ መልእክቱ ላይ ራሱን አሁንም ‹የክርስቶስ ባሪያ› ብሎ መጥራቱን አላቆመም(ፊልጵ.1÷1)፡፡ ለብዙ ዘመናት ማገልገሉ፣ ተአምራትን ማድረጉ፣ አያሌ ምእመናንን ማፍራቱ፣ ወደ ሰማያትም መነጠቁ ከዚህ ትኅትናው አላወረደውም፡፡ ይህ ዘመን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ትልቅ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ቢሆን እንኳን ‹በክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ የተያዝኩ ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናሉ፤ እኔ ገና እንዳልያዝኩ እቆጥራለሁ› ሲል ገና ጀማሪ ነኝ ይለናል(ፊልጵ.3÷13)፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ በ58 ዓ.ም. በተጻፈው የፊልሞና መልእክቱ ላይም ራሱን ‹የክርስቶስ ባሪያ› እያለ ይጠራዋል፡፡ መንፈሳዊ ዕድገትና ትኅትና አብረው ይሄዳሉና፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ የጻፋቸው ሁለት መልእክቶች ናቸው፡፡ በ58 ዓ.ም አካባቢ የመጀመሪያዋን፣ በ60 ዓ.ም አካባቢ ደግሞ ሁለተኛዋን መልእክት ለልጁ ለጢሞቴዎስ ልኮለታል፡፡ ይህም ለሁለት ዓመታት በሮም ከታሠረበት እሥር ቤት በወጣ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የሕይወቱ ዘመን ፍጻሜ ላይ ለመሥዋዕትነት እየተዘጋጀ ነው፡፡የኔሮን ጭካኔ ጨምሯል፤ በዚያ ዘመን የአውሮፓ ምዕራባዊ ጫፍ እስከሆነው ስፔን ድረስ ሄዶ በማስተማር ሩጫውን ፈጽሟል፤ የድል አክሊል ተዘጋጅቶለታል፡፡ ትኅትናው ግን ይበልጥ ጨምሯል፡፡ ስለራሱ ሲነግረንም ‹ከኃጢአተኞች ዋናው እኔ ነኝ› ይላል(1ኛጢሞ.1÷15)፡፡ ኃጢአቱ እንደተሠረየለት ያምናል፡፡ በደለኛነቱን ግን አይረሳውም፡፡ በደለኛነትን መርሳት ከትዕቢት ያደርሳልና፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለስብከተ ወንጌል ከመሠማራታቸው በፊት በአንድ ከባድ ፈተና ተፈትነው ነበር፡፡ በዚህ ፈተና ለምን እንደተፈተኑ ቅዱስ ሚካኤልን ሲጠይቁት ‹በኃጢአተኞች ላይ እንዳትፈርድባቸው ሲባል ነው› አላቸው፡፡

እውነተኛ የወንጌል አገልጋይ በመንፈሳዊ ሕይወት ማደጉን በአንድ ዋና መለኪያ ማየት ይቻላል፡፡ ይበልጥ ሲያገለግል ይበልጥ ትኁት ይሆናል፡፡

 

ጸሐፊ፡ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ብሒለ አበው

 • “በየጊዜው ለንስሐ መራኹ” (ቅዱስ እንጦንስ)
 • “ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ንስሐ የለም፡፡”
 • “ቁጡ ብስጩ አትሁን ቁጣ ነፍስ ወደማጥፋት ይደርሳል፡፡” /ቅዱስ እንድርያስ/
 • “ቂም በቀል የሌለህ ሁን ቂም በቀል በሌላቸው ሰዎች መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉና” /ቅዱስ ታዴዎስ/
 • “ከኃይልና ከጩኸት ይልቅ ይቅርታና ትህትና ጠንካራ ናቸው፡፡”
 • “ኃጢአት መደበቅ በራሱ ኃጢአት ነው፡፡”
 • “እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በተፈጥሮ ያልሰጠውን ማንም ሊሠጠው አይችልም፡፡”
 • “በራሱ ለራሱ አመኔታ ከሌለው ከሰው ቁምነገር መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡”
 • “የዲያቢሎስ አንዱ መንገድ ሰውን በፀጋው ማኩራራት ነው፡፡”
 • “የዶሮ እርግማን ጭልፊቷን አያስጨንቃትም፡፡”

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!

ምንጭ፡ – አትሮንስ መጽሐፍ

መንፈሳዊ አባባሎች

 • “የወጡ ማጣፈጫ ቅቤ ነው፡፡ የሃይማኖት ማጣፈጫ ግን ምግባር ነው፡፡”
 • “ክርስትና እያዘኑ የሚደሰቱበት ሃይማኖት ነው”፡፡
 • “ለአጢያት ንስሐ መግባት ሕይወት ነው፤ አለመግባት ግን ሞት ነው”፡፡
 • “መንፈሳዊ መካሪ ርካሽ ሳይሆን ውድ ነው”፡፡
 • “መጽሐፍ ቅዱስ ምግብ ነውና ይመገቡት”::
 • “መጽሐፍ ቅዱስ ያብሩት ብርሃን ነውና”፡፡
 • “ለጠቢብ ሰው ምላስ ጤና ናት”፡፡
 • “የጠቢብ ሰው ከንፈር እውቀትን ትዘራለች”፡፡
 • “የጻድቃን በደል በአንደበታቸው ነው፤ የኃጥአን በደል ግን በመላ ሰውነታቸው ነው”፡፡
 • “ሰው ለሚለው ነገር እንቢ ማለት በሽታ ነው”፡፡
 • “በሰው ንግግር መቀለድ ቂላቂልነት ነው፡፡”
 • “መነሳቱን የሚያውቅ ሰው መውደቁን እያቀደ ነው፡፡”
 • “መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት መዝገብ ቃል ነው፡፡”
 • “ፆም ራስን ሠውነትን የሚያሳይ መስታወት ነው፡፡”
 • “ፆም የነፍስ ቁስል ትፈውሳለች፡፡”

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!

ምንጭ፡ – አትሮንስ መጽሐፍ

ይህን ያውቁ ኖሯል

 • የቅዱስ መርቆርዮስ ፈረስ ጌታው ከሞተ በኋላ 7 ዓመት በጌታው ተተክቶ አስተምህሮ በጥር 25 ቀን ተገደለ፡፡
 • የገላውድዮስ ፈረስ ከአፉ እሳት እየወጣ አሳውያኖችን ያቃትላቸው ነበር፡፡
 • የአቡነ አካለ ክርስቶስ መቋሚያ ቤተመቅደስ ሳይታጥን የቀረ እንደሆነ መቋሚያዋ ካለችበት ትሰወራለች፡፡
 • የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ገዳም በቅሎዎች ተጭነው የ9 ሰዓት መንገድ በርሃ ወርደው ሰው ሳይከተላቸው መንገደኛ ውሃ ቀድቶ ሲጭናቸው ውሃውን ይዘው ለገዳሙ ያስረክባሉ ዛሬም እየተደረገ ነው፡፡
 • አቡነ ገሪማ ምራቃቸውን ተፍተው ወደ ጸበልነት የተለወጠች ዛሬም በዋሽነቷ ትታወቃለች፡፡
 • ቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጽ 23 ዓመት ፈጀበት በጠቅላላው የሰራቸው አብያተ ክርስቲያናት 210 ናቸው፡፡
 • የመጀመሪያው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበት ቦታ በሰሜን ጎንደር ዳሽን ጣና ደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ ገዳም ይባላል፡፡ እርሱንም የሚጠብቀው አውሬ ነው፡፡
 • የአቡነ ዘርዓብሩክ ዘጎጃም የተባለው ማየ ጠበል ድርሳኑ ሲደገም ባዶ ጠርሙስ ይቀመጣል፡፡ ድርሳኑ ተደግሞ ሲያበቃ ማሰሮው ጠርሙሶቹ ይሞላሉ፡፡ ያስደንቃል የጸበሉም ስም ረዳኤ ሕይወተ ዘማይ ጸሎት ይባላል፡፡
 • ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የእስላም መስጊድ እንዲሰራ ያደረገው ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ ይባላል፡፡ ይህም ከግብጽ የመጣው ጳጳስ የፈቀደው በሀገሩ እስላም መንግስት አድልቶ ስለነበር የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰቃይቶ አባረረው፡፡
 • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ5 እንጀራ በ2 ዓሣ ከሕጻናቱ በስተቀር 5ሺህ ሰው አበርክቶ 12 መሶብ ተርፎ የተነሣበት ዕለት በጥር 28 ቀን ነው፡፡
 • አጼ ይኩኖ አምላክና አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሠሩዋቸው አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 510 ሲሆኑ 160ው ታላላቅ ገዳማት ናቸው፡፡
 • ጌታችን 99ኙን ነገደ መላእክት ትቶ አንዱን የጠፋው አዳምን ሊፈልግ እንደመጣ የሚያትተው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሉቃስ ወንጌል 15፡13 ነው፡፡
 • ንጉስ ቆስጠንጢንዮስ በሰኔ 12 ቀን በ312 ዓ.ም በአዋጅ የጣዖታትን ቤት ዘግቶ ቤተክርስቲን እንድትከፈት አደረገ፡፡
 • በመጽሐፈ ኩፋሌ እንደተጠቀሰው የኖኅ ሚስት አምዛይ የሎጥ ሚስት ሚልካ የአብርሃም እናት ዲና ይባላሉ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

ከቤተ መጻሕፍት