አስተርእዮተ ሥሉስ ቅዱስ በቤተ አብርሃም

ቅድስት ሥላሴ

ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት የገባበትና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት ነው። ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው።


አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ዅሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ
ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡ አስቦም
አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አልመጣ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አብርሃምም ማዕደ
እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን
ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴው (በሦስትነቱ) ከአብርሃም ቤት ገብቷል
(ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፬፥፴፪)፡፡


በኦሪት ዘፍጥረት ፲፰፥፩-፲፱ ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር
በሦስት ሰዎች አምሳል በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው
ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን
አትለፈኝ?›› ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች
ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ
መጥታችኋልና›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እንዳልህ አድርግ›› ብለውታል፡፡


የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን ‹‹ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ›› ሲላቸው
‹‹ደክሞናልና አዝለህ አስገባን›› አሉት፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ (በአምላካዊ
ጥበብ) ከቤቱ ገቡ፡፡ አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ሔደና ‹‹ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ›› አላት፤ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ አብርሃምም ወይፈን አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡ ወይፈኑም ተነሥቶ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፤›› ብሎ እግዚአብሔርን አመስገኗል፡፡
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ
እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም
ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች
ግዳጅ ትቷት ነበርና ‹‹‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› እንዲሉ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?›› ብላ በማሰቧና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና
አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡ ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡


በዚህ ትምህርት ብዙ ምሥጢራት ይገኛሉ፤ ጥቂቶቹን በመጠኑ ለማስታወስ ያህል፦ ‹‹… ሦስት ሰዎች … ሊቀበላቸው … ወደ እነርሱ …›› የሚሉትና ሌሎችም በብዙ ቍጥር የተገለጹ ተመሳሳይ ሐረጋት የእግዚአብሔርን ሦስትነት፤ ‹‹… በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ? …›› የሚለው ዐረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ያመለክታል፡፡ ሣራ ዳቦ ያዘጋጀችበት ሦስቱ መሥፈሪያ የሦስትነቱ፤ ዳቦው አንድ መኾኑ ደግሞ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡

ሥላሴ አብርሃም ያዘጋጀውን እንስሳ ተመገቡ ተብሎ መነገሩም በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ነው እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ አይስማማቸውም (አይነገርላቸውም)፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ሥላሴ ምግብ በሉ (እግዚአብሔር ምግብ በላ) ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡ መብላት፣ መጠጣትን የመሰሉ የሥጋ ተግባራት የመለኮት ባሕርያት አይደሉምና፡፡ ከዚህ በተለየ ምሥጢር ሥላሴ ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› ብለው ከጠየቁበት ኃይለ ቃል መካከል ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› የሚለውን እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› (ሉቃ. ፩፥፴፯) ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ መናገሩ የእግዚአብሔር ቃል በዘመን ብዛት የማይለወጥ ሕያውና እውነተኛ መኾኑን ያጠይቃል።
እግዚአብሔር አብርሃምን ‹‹ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል መጠየቁም ያለችበት ጠፍቶበት ሳይኾን የሚነግራት ታላቅ
የምሥራች እንዳለ ለማጠየቅ ነው፡፡ ሰውን ያለበትን ጠይቆ፣ ጠርቶ፣ አቅርቦ አስደሳች ዜና መንገር የተለመደ ነውና፡፡
ይኸውም ‹‹አዳም ወዴት ነህ?›› ከሚለው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው (ዘፍ. ፫፥፱)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አዳምን ‹‹ወዴት ነህ?›› ሲል የጠየቀው ያለበትን ዐላውቅ ብሎ ሳይኾን ቃል በቃል ሊያነጋግረው፣ ‹‹ከልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚለውን የድኅነት ቃል ኪዳን ሊሰጠው ፈቅዶ ነበር፡፡ እንደ አዳም ዅሉ ለሣራም ለጊዜው ይስሐቅን እንደምትወልድ፤ ለፍጻሜው ደግሞ ከአብርሃም ዘር ከምትኾን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ እንደሚገለጥና ዓለሙን እንደሚያድነው ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል ጠይቆታል፡፡ ከዚያም የይስሐቅን መወለድ አብሥሯቸዋል፡፡ ይኸውም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም እግዚአብሔር
ከአብርሃም የልጅ ልጅ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደ (በአካለ ሥጋ ወደ ምድር እንደ መጣ)፤ በዚህ ጊዜም በሣራ የተመሰለች ወንጌል በይስሐቅ የሚመሰሉ ምእመናንን እንዳስገኘች ማለትም ሐዲስ ኪዳን
ተመሥርታ ብዙ ክርስቲያኖችን እንዳፈራች የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡


የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደ ተረጐሙልን የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ ‹‹ተናግዶቱ (ተአንግዶቱ)
ለአብርሃም፤ ለአብርሃም የሃይማኖቱን (የእንግዳ ተቀባይነቱን) ዋጋ የምታሰጪው አንቺ ነሽ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ፡፡
በአብርሃም ድንኳን አላፊ አግዳሚው ይመግብበት፣ ያርፍበት እንደ ነበረ ዅሉ በእመቤታችንም አማላጅነትም
መንገደኞች ማረፍያ፤ እንግዶች መጠለያ፤ ስደተኞች ተስፋ ያገኛሉና፡፡ ከዅሉም በላይ የነፈስ የሥጋ መድኀኒት፤
የዘለዓለም ማረፍያ፤ እውነተኛ መብልና መጠጥ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እርሷ ናትና በአብርሃም ድንኳን
ትመሰላለች፡፡ ቀትር በኾነ ጊዜ ማለትም በስድስት ሰዓት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደ ገቡ
ዅሉ፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዓመት ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዓመት እግዚአብሔር አብ ለአጽንዖ፤
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመልበስ በእመቤታችን ቅድስት
ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡ ‹‹በስድስተኛው ወር ቅዱስ ገብርኤል
ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተላከ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. ፩፥፳፮)፡፡ በዚህ ቃለ ወንጌል ‹‹ስድስተኛው
ወር›› የሚለው ሐረግ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን ቅዱስ ገብርኤል ወደ
እመቤታችን ለብሥራት መላኩን ያመለክታል፡፡
በአብርሃም ቤት (በድንኳኑ) ውስጥ ወይፈኑ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› ብሎ
እንዳመሰገነ ዅሉ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች ‹‹ስብሐት
ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን፤ ሰላምም
በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ›› እያሉ እግዚአብሔርን በአንድነት አመስግነዋል (ሉቃ. ፪፥፲፬)፡፡


እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የይስሐቅን መወለድ እና በሥጋ ማርያም መገለጡን ከነገረው በኋላ ተመልሶ ሔዷል፡
፡ ‹‹ሄዷል›› ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት በሰው አምሳል ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ዅሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ
ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡
ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ተገኝቶ የይስሐቅን መወለድና
የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የተናገረበት ዕለት ከመኾኑ ሌላ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ዅሉ
በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱ፤ ይህንን
ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም
እግዚአብሔር በኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው፤ አብርሃምም በአማላጅነት በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የተማጸነው በዚሁ ዕለት ነው፡፡


ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ዘወትር ስለ ሰው ልጅ ድኅነት እንደሚጸልዩ እና እንደሚያማልዱ፤ እንደ አብርሃም
ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ተግባራቸው አድርገው በሚኖሩ
ሰዎች ቤት እግዚአብሔር እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤት ወደ ሰው ቤት ሲገባም የተዘጋ ማኅፀን እንደሚከፍትና ቤቱን በበረከት እንደሚሞላ፤ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየታየ አምላክነቱን ለዘመናት እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከታሪኩ እንማራለን፡


በአጠቃላይ ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት የመገለጥ ትምህርት በአንድ ወቅት ብቻ የተፈጸመና ‹‹ነበር›› እየተባለ
የሚነገር ያለፈ ታሪክ ሳይኾን፣ ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ቃል ነው፡፡ ይህንም እግዚአብሔር
ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ለዘመናት በሚያደርገው ድንቅ ሥራና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡

ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመለየት በተጨማሪ ለተቸገሩ በመራራት፣ በደግነት፣ በቀና አስተሳሰብ ከተጓዝን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ እርሱ ያደረበት ሰውነት ይባረካል፤ ይቀደሳልና፡፡ ደግሞም ልጅ ለሌለን ልጅ፤ ዘመድ ላጣን ዘመድ በመስጠት ዘራችንንም ይባርክልናል፡፡ በጥቅሉ የልባችንን መሻት ዐውቆ የምንሻውን መልካም ነገር ዅሉ ይፈጽምልናል፡፡ ይህ ዅሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ እኛም በርትዕት የተዋሕዶ ሃይማኖት እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባርም እንትጋ፡፡

አዘጋጅ- የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል እግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ትምህርት ቤት።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ

ይህም ቅዱስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል። ይኸውም ልሳነ ዕረፍት፣ የክርስቶስ አንደበት፤ የዕውቀት አዘቅት፤ የቤተ ክርስቲያን መብራት፤ እንደ ስሙም ትርጓሜ መሪ አመስጋኝ ወደብ ጸጥታ ነው።


ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ በክርስቶስ ያመኑትን የሚያሳድድ ነበር፤ እርሱም ከብንያም ወገን የፈሪሳዊ ልጅ ነው። ወላጆቹም ሳውል ብለው ስም አወጡለት ትርጓሜውም ስጦታ ማለት ነው። ቁመቱ ቀጥ ያለ መልኩ ያማረ ፊቱ ብሩህ ቅላቱ እንደ ሮማን ቅርፍት ደርበብ ያለ ዐይኑም የተኳለ የሚመስል አፍንጫው ቀጥ ያለ ሸንጎበታም ጉንጩ እንደ ጽጌ ረዳ ነበር።


እርሱም ሕገ ኦሪትን አዋቂ ነበረ። ለሕጉም ቀናተኛ ሆኖ ምእመናን አሳዳጅ ነበረ። ወደ ሊቀ ካህናቱም ሔዶ መንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንና ሴቶችን እንደ ታሠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይመልሳቸው ዘንድ ለደማስቆ ከተማና ለምኵራቦች የፈቃድ ደብዳቤ ለመነ። ሲሔድም ወደ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ ድንገት ከሰማይ መብረቅ ብልጭ አለበት በምድር ላይም ወደቀ ወዲያውም “ሳውል ሳውል ለምን” ታሳድደኛለህ የሚለውን ቃል ሰማ።


ሳውልም “አቤቱ አንተ ማነህ” አለው “አንተ የምሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ በሾለው ብረት ላይ ብትረግጥ አንተን ይጎዳሃል” አለው። እየተንቀጠቀጠም አደነቀ “አቤቱ ምን እንዳደርግ ትሻለህ” አለው ጌታም “ተነሥና ወደ ከተማ ግባ ልታደርግ የሚገባህን ከዚያ ይነግሩሃል” አለው። ከርሱ ጋራ ቁመው የነበሩ ሰዎችም ንግግሩን ይሰሙ ነበር ነገር ግን የሚያዩት አልነበረም።


ሳውልም ከምድር ተነሣ ዐይኖቹንም ተገልጠው ሳሉ አያይም ነበር እየመሩም ወደ ደማስቆ አስገቡት በዚያም ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ሰነበተ። በዚያም በደማስቆ ከደቀ መዛሙርት ወገን ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ጌታም በራዕይ ተገለጠለትና ሐናንያ ብሎ ጠራው እርሱም “አቤቱ ጌታዬ እነሆኝ” አለ። ጌታም “ተነሥና ቀጥተኛ ወደምትባለው መንገድ ሒድ በይሁዳ ቤትም ጠርሴስ ከሚባል አገር የመጣ ሳውል የሚባል ሰው ፈልግ እርሱ አሁን ይጸልያልና” አለው።


ሐናንያ ግን መልሶ እንዲህ አለ “አቤቱ ስለዚያ ሰው በኢየሩሳሌም በቅዱሳኖችህ ላይ የሚደርገውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ ወደዚህም ከካህናቱ አለቃ አስፈቅዶ የመጣ ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ሊያሥር ነው”። ጌታችንም “ተነሥና ሒድ በአሕዛብና በነገሥታት በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና። እኔም ስለ ስሜ መከራ ይቀበል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ”።


ያን ጊዜም ሐናንያ ሔደ ወደ ቤትም ገባ “ወንድሜ ሳውል በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ታይ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ ይሞላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። ያን ጊዜም ዐይኖቹም ተገለጡ። ወዲያውም አየ ተነሥቶም ተጠመቀ እህልም በልቶ በረታ። ከደቀ መዛሙርትም ጋር በደማስቆ ጥቂት ቀን ሰነበተ። በዚያው ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰበከ አስተማረም። የሰሙትም ሁሉ አደነቁ እንዲህም አሉ “በኢየሩሳሌም ይህም ስም የሚጠሩትን ሁሉ ያሳድድ የነበረ ይህ አልነበረምን ወደዚህስ የመጣው እያሠረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊወስዳቸው አይደለምን” አሉ።


አጽናኝ መንፈስ ቅዱስም አደረበት እውነተኛንም ሃይማኖት ግልጽ አድርጎ አስተማረ። ለኦሪት ሕግ የሚቀና እንደ ነበረ እንዲሁ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠራት ሕግ ወንጌል ዕጽፍ ድርብ ቅንዓትን የሚቀና ሆነ። ከዚህም በኋላ በአገሮች ሁሉ ዞሮ ሰበከ በጌታችንም ስም ሰበከ። ድንቆችንና ተአምራትንም አደረገ። ቁጥር የሌላቸው ብዙዎች አሕዛብንም አሳመናቸው ነገር ግን ብዙ ጊዜ በመገረፍ በመደብደብና በመታሠር ብዙ መከራ ደረሰበት መከራውንም ሁሉ ታግሶ በሁሉ ቦታ አስተማረ።


በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደተጻፈ የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ ሲጾሙና ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ “እኔ እነርሱን ለመረጥሁለት ሥራ ሳውልና በርናባስ ለዩልኝ” አላቸው። ከዚህም በኋላ ጾመውና ጸልየው እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሙአቸው ከመንፈስ ቅዱስም ተሹመው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ።


በደሴቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፋ ወደ ምትባል አገር ደረሱ። በዚያም ሐሰተኛ ነቢይ የሆነ ስሙ በርያሱስ የሚባል አንድ ሥራየኛ አይሁዳዊ ሰው አገኙ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባል ብልህ ሰው ከሆነ አገረ ገዥ ዘንድ የነበረ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ወዶ በርናባስንና ሳውልን ጠራቸው። የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበርና ኤልማስ የሚሉት ያ ሴረኛ ሰው ይከራከራቸው ነበር ገዥውንም ማመንን ሊከለክለው ወዶ ነበር።


ጳውሎስ በተባለው ሳውል ላይም መንፈስ ቅዱስ መላበት። አተኵሮም ተመለከተው “ኃጢአትንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ የሰይጣን ልጅ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ እያመጣመምኽ ተው ብትባል እምቢ አልኽ እነሆ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ተቃጥታለች ትታወራለህ እስከ እድሜ ልክህም ፀሐይን አታይም” አለው። ወዲያውኑም ታወረ ጨለማም ዋጠው የሚመራውንም ፈለገ አገረ ገዥውም የሆነውን አይቶ ደነገጠ በጌታችንም አመነ።


ከዚህ በኋላ ሒደው ወደ ሊቆኦንያ ከዚያም ወደ ልስጥራንና ደርቤን ከተማ ወደ አውራጃውም ሁሉ ገብተው አስተማሩ። በልስጥራን ከተማም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እግሩ ልምሾ የሆነ አንድ ሰው ነበረ ተቀምጦ ይኖር ነበረ እንጂ ልምሾ ከሆነ ጀምሮ ቁሞ አልሔደም። ቅዱስ ጳውሎስንም ሲያስተምር አደመጠው ጳውሎስ ተመልክቶ ሃይማኖት እንዳለው እንደሚድንም ተረዳ። ድምፁንም ከፍ አድርጎ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ቀጥ ብለህ ቁም እልሀለሁ” አለው ወዲያውኑ ተነሥቶ ሔደ። አሕዛብም ቅዱስ ጳውሎስ ያደረውን አይተው በጌታችን አመኑ…።
ከዚህም በኋላ ከሐዋርያ ፊሊጶስ ጋር ወደ ሁለት አገሮች በአንድነት ሔዱ ከዚያም በጌታችን ስም ሰበኩ የአገሩም አለቆች ያዟቸው እጆቻቸውንና እግሮቻቸው አሰሯቸው በአንገቶቻቸውም የብረት ሰንሰለቶችን አስገቡ እራሳቸውንም የሸፋን የብር ቆብን ሰሩላቸው ዳግመኛም በእጅና በእጅ በጣቶችም ምሳሌ ሰሩ በእጆቻቸውና በክንዶቻቸው እያንዳንዱን የብረት እጅ ጨመሩ። ከብረቶችም ጋር ቸነከሯቸው።


ሁለተኛም እስከ አንገት የሚደርስ በትከሻ አምሳል ሰሩ በፊትና በኋላም ቸነከሯቸው ደግሞም መላ አካላቸውን የሚከብና ከአካላቸው ምንም እንዳይታይ የሚሸፍን የብረት ሰሌዳ ሰሩ ከወገቦቻቸው ጋራ ቸነከሯቸው ችንካሮችም ተረከዛቸውን ነድለው ወደ ጭኖቻቸው እስከሚደርሱና እስከሚያቆስሏቸው ድረስ የብረት ጫማ ሰርተው እግሮቻቸውን ቸነከሩ። ደግሞ በመሸፈኛ አምሳል የብረት ሰናፊል ሠሩ ቀማሚዎችም መጡ አንድ መክሊት የሚመዝን እርሳስንም አመጡ ታላቅ የብረት ጋንንም ሰባት ልጥር የሰሊጥ ቅባት አመጡ። ስቡንና አደሮ ማሩን የእሳቱን ኃይል አብዝቶ የሚያነደውን ቅመሙን ከሙጫውና ከድኙ ጋር ቀላቀሉት ከዋርካና ከቁልቋል ከቅንጭብም ደም ሰባት ልጥር አንድ ወይን ሐረግንና ቅባት ያለቸውን እንጨቶች ሁሉ አመጡ።

በጋን ውስጥ ያበሰሉትንና ያሟሙትን ልዩ ልዩ ቅመምን አምጥተው ከሥጋቸው እስሚጣበቅ በቅዱሳን ሐዋርያት ሥጋ ላይ ባሉት ሠሌዳዎች ውስጥ ጨመሩት። ከእግራቸው እስከ ራሳቸው ከፍ ከፍ እስከሚል ድረስ በእሳት ያቀለጡትን ያንን እርሳስ ጨመሩት። ርዝመቱ ዐሥራ አምስት ክንድ በሆነ ወፍራም የጥድ ምሰሶ ላይም አቆማቸውና ከበታቻቸው ፍሬ በሌለው በወይን ሐረግና በተልባ እሳቱን አቀጣጥለው አነደዱ። የእሳቱም ነበልባልም ከሥጋቸው በላይ ከፍ ከፍ አለ ሐዋርያትን ግን ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር።
ከመኳንቱም በአንዱ ልብ ርኅራኄ አሳደረና እንዲፈቷቸው አዝዞ ፈቷቸው። በፈቷቸውና ሠሌዳው ከሥጋቸው ላይ ባስወገዱ ጊዜ ቆዳቸው ተገፈፈና ከብረቱ ሠሌዳዎች ጋር ወጣ። ብዙ ደምም ከሥጋቸው ፈሰሰ።


ሰይጣንም በከተማው ሰዎች ልብ አደረና ሐዋርያትን ወደ እሳት ውስጥ መለሷቸው ያን ጊዜ ጌታችን ወርዶ የእሳቱ ነበልባል አጠፋው። ዝናብን የተሞላች ብርሕት ደመና መጥታ ቅዱሳን ሐዋርያት ከበበቻቸው በዚያም አገር አንድ ጊዜ በደንጊያ በመወገር አንድ ጊዜም በፍላጻ በመንደፍ ብዙ ተሰቃዩ። ከዚህም በኋላ ሙታንን በአነሱ ጊዜ የከተማው ሰዎች ሁሉ አመኑ አጠመቋቸው። ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው ካህናትንም ሾሙላቸው በቀናች ሃይማኖት እስኪጸኑ አስተማሯቸው። ከዚያም ወጥተው ጌታችን ወደ አዘዛቸው ወደ ሌላ አገር ሔዱ።


ክብር ይግባውና ጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጳውሎስ ተገለጠለትና “የመረጥኩህ ጳውሎስ ሆይ ስላም ላንተ ይሁን። መታሰቢያህን የሚደርገውን፣ በስምህ ቤተ ክርስቲያን የሚሰራውንና የሚጸልየውን፣ ስለትንና መባንም የሚሰጠውን፣ በመታሰቢያህም ቀን ለድኆች የሚመጸውተውን ሁሉ ከአንተ ጋር በመንግሥተ ሰማያት አኖራቸዋለሁ” አለው። “በስምህ የታነጹትም አብያተ ቤተ ክርስቲያናት መላእክቶቼን እንዲጠብቋቸው አደርጋቸዋለሁ” ቡዙ ቃል ኪዳንም ሰጠው። በመለኮታዊ አፉ አፉን ሳመውና ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ።


ከዚህም በኋላ እልዋሪቆን ወደ ምትባል ታላቅ አገር እስከሚደርስ በብዙ አገሮች ውስጥ ተመላለሰ በዚያም የብርሃን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻለት አረጋጋችው ረዳችውም የአገሩን ሰዎች እንዲያጠምቃቸውና እንዲያስተምራቸው አዘዘችው።
ከዚህም በኋላ ወደ ሮሜ ከተማ ገብቶ በውስጧ ሰበከ በስብከቱም ብዙዎች ሰዎች አምነው የክርስትናን ጥምቀትን አጠመቃቸው። በመጻፍትነት የታወቁ ዐሥራ አራት መልክቶችን ጻፈ የመጀመሪያ መልክቱም ለሮሜ የተጻፈችው ናት።


መልካም ሩጫውን ከፈጸመ በኋላ ንጉሥ ኔሮን ይዞ ጽኑ ሥቃይ አሰቃየው። ራሱንም በሠይፍ እንዲቆርጡት ለሠያፊ ሰጠው ከሠያፊውም ጋር አልፎ ሲሄድ ከንጉሥ ኔሮን ዘመዶች ወገን የሆነች አንዲት ብላቴና አገኘችው እርሷም ክብር ይግባውና በጌታችን ያመነች ነበረች ስለእርሱ አለቀሰች። እርሱ ግን “መጎናጸፍያሽ ስጭኝ እኔም ዛሬ እመልስልሻለሁ” አላት። እርሷም መጎናጸፍያዋን ሰጠችውና ራስ ወደሚቆርጡበት ቦታ ሔደ። ለሠያፊው ራሱ በዘነበለለት ጊዜ በመጎናጸፍያዋ ፊቱን ሸፈነ ሠያፊው የቅዱስ ጳውሎስ ራስ ሐምሌ 5 ቀን ቆርጦ በዚያች ብላቴና መጎናጸፍያ እንደተሸፈነ ጣለው።


ሠያፊው ጳውሎስን እንደገደለው ለንጉሥ ሊነግረው በተመለሰ ጊዜ ያቺ ብላቴና አገኘችው “ያ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ አለ” አለችው። ራስ በሚቆርጥበት ቦታ ወድቋል ራሱም በመጎናጸፍያሽ ተሸፍኗል” አላት። እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት “ዋሽተሃል እነሆ ጴጥሮስና ጳውሎስ በእኔ ዘንድ አልፈው ሔዱ እነርሱም የመንግሥት ልብስን ለብሰዋል በራሳቸውም ላይ በእንቊ የተጌጡ አይንን የሚበዘብዙ አክሊላትን አድርገዋል። መጎናጸፍያዬን ሰጡኝ። እርሷም እነኋት ተመልከታት” ብላ ለዛያ ሠያፊ አሳየችው። ከእርሱ ጋር ለነበሩትም አሳየቻቸው። አይተውም አደነቁ ስለዚህም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።


ለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተአምራቶች ቁጥር የሌላቸው እጅግ የበዙ ናቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በቅዱስ ጳውሎስ በጸሎት ይማረን ።

ዐምደ ሃይማኖት ቅዱስ ቄርሎስ

ቅዱስ ቄርሎስ


አባ ቄርሎስ፦ ይህም አባት ለእስክንድርያ (ለግብጽ) ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ አራተኛ ነው። ይህም ቅዱስ የእናቱ ወንድም በሆነው በአባ ቴዎፍሎስ ዘንድ አደገ፤ ጥቂት ከፍ ባለ ጊዜም ወደ አስቄጥስ ወደ መቃርስ ገዳም ላከው በዚያም አምላካውያን የሆኑ መጻሕፍትን ተማረ እግዚአብሔርም መጽሐፍትን አንድ ጊዜ አንብቦ እስከሚያጸናው ድረስ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጠው።


ከዚህም በኋላ ደግሞ ያስተምረው ዘንድ ለአባ ሰራብዮን ሰጠው ከእርሱም ዘንድ ያለውን ትምህርትን በፈጸመ ጊዜ ወደ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ መለሰው። እርሱም እጅግ ደስ ተሰኘበት እግዚአብሔርንም አመሰገነው። ከዚህም በኋላ ሁል ጊዜ መጻሕፍትን እንዲያነብና ሕዝቡን እንዲያስተምር ለሊቀ ጵጵስና ሥራ ውስጥ ሾመው። ከትምህርቱም ጣዕም የተነሣ ዝም ይል ዘንድ ማንም አይወድም ነበር።


አባ ቴዎፍሎስ ካረፈ በኋላ በእስክንድርያ ከተማ ላይ ይህን አባ ቄርሎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም በትምህርቱ ቤተ ክርስቲያን በራች። ይኸው አባት ቄርሎስ የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ንስጥሮስ በካደ ጊዜ በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ማኅበርን በኤፌሶን ከተማ ሰበሰበ። ይህ አባት ቄርሎስን መረጠው ሊቀ ጉባኤ አደረጉት ንስጥሮስንም ተከራከረው ስህተቱንም ገለጠለት ከስህተቱም ባልተመለሰ ጊዜ አውግዘው ከመንበረ ሲመት አሳደዱት።


ይህም አባት ቄርሎስ አሥራ ሁለት አንቀጾችን ደረሰ። በውስጣቸውም የቀናች ሃይማኖትን ገለጠ። ከዚህም በኋላ ግን ብዙዎች ድርሳናትን ተግሳጻትንና መልእክቶችን ደረሰ። እነዚህም በሁሉ ቦታ በምእመናን እጆች ይገኛሉ።


ቅዱስ ቄርሎስ እግዚአብሔር ቃል ከትስብእቱ ጋራ ከተዋሐደ በኋላ በሥራ ሁሉ በምንም በምን የማይለያይ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ እንደሆነ አስረዳ። ቄርሎስም ሃይማኖታቸው ከቀና ከሦስት መቶ አሥራ ስምንት አባቶች ሃይማኖት ወጥተው ክርስቶስን ወደ ሁለት የሚከፍሉት መናፍቃንን ሁሉንም አውግዞ ለያቸው።


ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ መልካም የሆነው ሥራውም ፈጽሞ ሐምሌ 3 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ቄርሎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላዓለሙ አሜን።


“ሰላም ለቄርሎስ ወልደ አንበሳ ጽኑዕ፤ ነባቢ ምስጢረ ሥላሴ ቅድስት፤ ዘተናገረ ላዕለ መለኮት”።


ትርጉም፦ በመለኮት ላይ የተናገረ፤ የቅድስት ሥላሴን ምስጢርን ተናጋሪ፤ ብርቱ (ጠንካራ) ለኾነ ለአንበሳው ልጅ ለቄርሎስ ሰላምታ ይገባል።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

የነቢይ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት፦

ሃሌ ሉያ “ሰምዑ አዝማዲሃ ወሰብአ ቤታ። እስመ አዕበየ እግዚአብሔር ሣህሎ ላዕሌሃ። ወተፈሥሁ ፍሥሃ ፈድፋደ። ወፈቀዱ ይስምይዎ በስመ አቡሁ ዘካርያስ። ወትቤ እሙ ዮሐንስሃ ይሰመይ”። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።


የነቢይ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ልደት፦ ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው። ይህም በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው።


በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች። ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለርስዋ ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን “አይሆንም ዮሐንስ ይባል” አለች። “ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም” አሏት።


አባቱንም ጠቅሰው “ማን ሊባል ትወዳለህ” አሉት። እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ “ዮሐንስ ይባል” ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም የልዑል ነቢይ እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።


ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሔዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት እንዲገድሉትም ጭፍሮችን ላከ ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋራ እንዲሔዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።


ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና “ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት” አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው። ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት። ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሀ ውስጥ ኖረ።


“የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ የዐዋጅ ነጋሪ ድምጽ እነሆ” ብሎ ኢያሳያስ የተናገረለት ይህ ነው። ሚልክያስም ስለርሱ እንዲህ አለ “በፊትህ ጎዳናዬን አስተካክሎ የሚጠርግ መልአክተኛዬን እኔ እሰዳለሁ”።ራሱ መድኃኒታችንም ስርሱ ሲናገር “ሴቶች ከወለዷቸው መጥምቁ ዮሐንስን የሚበልጠው የለም” ብሏል። ይህ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ልጅ በአጠመቀውና የማትዳሠሥ ራሱን በዳሠሠው ጊዜ “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” የሚል የአብን ቃል ሰምቷልና። ዳግመኛም ክብር ይግባውና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሲቀመጥም አይቷልና።

እኛንም መድኃኒታችን እንዲምረንና ይቅር እንዲለን በአማላጅነቱ እያመን መታሰቢያውን እናድርግ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱም እኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አባ ሙሴ ጸሊም

ሙሴ ጸሊም

ሰዎች ከገድሉ የተነሣ ይህን ቅዱስ ያደንቁታል እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ በሥራውም ኃይለኛ ነበር ይበላና ይጠጣ፣ ይቀማና ያመነዝር ነበር ይገድልም ነበር ማንም ሊቋቋመው አይችልም ነበር። አንድ በግ በአንድ ጊዜ ጨርሶ እንደሚበላና አንድ ፊቀን ወይን ጠጅ እንደ ሚጠጣ ስለ እርሱ ተነግሮአል። እርሱም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበር ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ “ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ” ይል ነበር ደግሞም በልቡ “የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ” ይል ነበር።


ከዚህም በኋላ በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው። ያን ጊዜም ተነሣ ሰይፉንም ታጥቆ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው። አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም “እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ” አለው። አባ ኤስድሮስም ወደ አባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው። እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲለህም አለው “ታግሠህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ።”


ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኰሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ። ሰይጣንም ቀድሞ ሲሠራው በነበረ በመብሉና በመጠጡ መዝሙቱም ይዋጋው ነበረ እርሱም በራሱ ላይ የሚደርስበትን ሁሉ ለአባ ኤስድሮስ ይነግረው ነበር እርሱም አጽናንቶ ሊሠራው የሚገባውን ያስተምረው ነበር።


ከገድሉ ብዛትም የተነሣ አረጋውያን መነኰሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውኃ መቅጃዎችን ወስዶ ውኃ መልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር። ውኃው ከእርሱ ሩቅ ነበረና እንዲም እያደረገ በመጋደል በብዙ ዘመናት ኖረ። ሰይጣንም በእርሱ ቀንቶ በእግሩ ውስጥ አስጨናቂ የሆነ አመታትን መታው ተኝቶም እየተጨነቀ ብዙ ቀን ታመመ።
ከዚህም በኋላ የመታውና የሚፈታተነው ሰይጣን እንደሆነ ዐውቆ ሥጋው በእሳት ተለብልቦ እንደ ደረቀ ዕንጨት እስኪሆን ድረስ ተጋድሎውንና አገልግሎቱን አበዛ። እግዚአብሔርም ትዕግሥቱን አይቶ ከደዌው ፈወሰው የሰይጣንንም ጦር ከእርሱ አራቀለት የመንፈስም ጸጋ አደረበት ወደርሱም አምስት መቶ ወንድሞች መነኰሳት ተሰበሰቡ በእነርሱም ላይ አበ ምኔት ሆነ።


ከዚህም በኋላ ቅስና ሊሾሙት መረጡት በቤተ መቅደስም ሊቀ ጳጳሳቱ ዘንድ በአቆሙት ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱም አልፈቀደም ነበር አረጋውያኑንም “ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት ከዚህ አውጡት” አላቸው እርሱም “መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ” በማለት ራሱን እየገሠጸ ወጣ ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ሊቀ ጳጳሳቱ ጠራውና እጁን በላዩ ጭኖ ቅስና ሾመው እንዲህም አለው “ሙሴ ሆይ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ”።


በአንዲትም ዕለት ቅዱሳን አረጋውያን ወደርሱ መጡ በእርሱም ዘንድ ውኃ አልነበረም እርሱም ከበዓቱ ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ይል ነበር ከዚህም በኋላም ብዙ ዝናም ዘንሞ ጒድጓዶችን ሁሉ ሞላ። አረጋውያንም ለምን ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ትል ነበር ብለው ጠየቁት እርሱም “እግዚአብሔርን ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ እለው ነበር ።በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን” አላቸው።


በአንዲት ዕለት አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ ሔደ አባ መቃርስም የሰማዕትነት አክሊል ያለው ከእናንተ ውስጥ አንዱን እነሆ አያለሁ” አላቸው አባ ሙሴም “አባቴ ሆይ ምናልባት እኔ እሆናለሁ በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው የሚል ጽሑፍ አለና” ብሎ መለሰ።


ከዚህም በኋላ የበርበር ሰዎች መጡ አባ ሙሴም ከእርሱ ጋራ ያሉትን መነኰሳት “እነሆ የበርበር ሰዎች ደረሱ መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ” አላቸው እነርሱም “አባታችን አንተስ አትሸሽምን” አሉት እርሱም “በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል ስለ ሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ያቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ” አላቸው። ወዲያውኑም የበርበር ሰዎች ገብተው በሰይፍ ገደሉት መሸሽ ስለ አልፈለጉ ከእርሱ ጋር ሰባት መነኰሳትም ተገደሉ አንዱ ግን ከምንጣፍ ውስጥ ተሠወረ የእግዚአብሔርንም መላአክ አየ በእጁም አክሊል ነበር እርሱም ቆሞ ይጠብቅ ነበር። ይህንንም በአየ ጊዜ ከተሠወረበት ወጣ የበርበር ሰዎችም ገደሉት የሰማዕታትንም አክሊል ተቀበለ።


ወንድሞች ሆይ ከሀዲና ነፍሰ ገዳይ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ለውጣ ደግ አባት መምህርና የሚያጽናና ለመነኰሳትም ሥርዓትን የሠራ ካህን እንዳደረገችው በሁሉም አብያተ ክርስቲያን ስሙ እንዲጠራ እንዳደረገችው የንስሐን ኃይሏን ተመልከቱ።


ሥጋው በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ ለዘላለም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ይታያሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የሰኔ 24 ስንክሳር።


“ሰላም ዕብል ለሙሴ ጸሊም። እንተ ነበረ ዕጉሠ ውስጤ ገዳም። ሶበ ተዘከረ ኵሎ እከያቲሁ ዘቅድም እትቀተል ይቤ በመጥባሕተ በርበር ዮም። ዘእንበለ ደም ኢይነጽሕ ደም”። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 24።


የዋሃት ያለው ሰው እንዴት ያለ ነው?


የዋሃት ወይም ደግነት ጌታ ከእርሱ እንማረው ዘንድ የጠየቀን እጅግ ጠቃሚ ምግባር ነው፡፡<<ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፡፡ማቴ 11-29 ብሏልና፡፡ ከእርሱ ስብከትን መምህርነትን፣አገልግሎትን፣ፍቅርን፣ ምህረትን፣ጥበብን እና ሌሎች ምግባራትን እና ፍጹምነትን ሁሉ እንድንማር ጠይቆናል ፍጹምነትን እና ምግባር ሁሉ ይወክላል ነገር ግን በየውሃት እና ቸርነት ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ይህንን ለሚማሩትም <<ለነፍሳችሁ እረፍት ታገኛላችሁ>> ብሏቸዋል፡፡


አባቶች ሐዋርያት በንግግራቸው ውስጥ ስለየዋህነት በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <<ወንድሞች ሆይ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየዋሃት መንፈስ አቅኑት አንተ ደግሞ እንዳትፈትን ራስህን ጠብቅ፡፡ገላ 6÷1 አለ፡፡

የዋህ ሰው መልካም ጠባይ ያለው እና ሰላማዊ ሰው ነው፡፡እርሱ ሁል ጊዜ የተረጋጋ ነው፡፡ጠባዩ የረጋ ነው ንግግሮቹ ስሜቶቹ እና እንቅስቃሴዎቹም ሰላማዊ ናቸው፡፡ውጪያዊ ገጽታው ብቻ ሳይሆን እሱነቱም እርጋታ የተሞላበት ነው፡፡ልቡና ስሜቶቹ የረጉ ናቸው፡፡ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች እና ንግግሮች የረጋ ነው፡፡ዳግመኛም<<ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር፡፡ዘኁ 12÷3 የየዋህ ሰው ድምጽ ሁልጊዜ የዋህ ነው፡፡ ድምጹ ፈጽሞ ከፍተኛና ኃይለኛ አይደለም፡፡ንግግሮቹ ጎጂም አስቸጋሪም አይደሉም የረጋ እና አነስተኛ ድምጽ የሚመስል ነው፡፡ይህም የየዋሁ ጌታችንን ድምጽ የሚመስል ነው፡፡ እግዚአብሔር ነብዩ ኤልያስን ከአጭበርባሪዋ ከንግስት ኤልዛቤል ሲሸሽ ባገኘው ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ነፈሰ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፡፡ ከነፋሱም በኋላ በምድር መናወጥ ሆነ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም፡፡ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፡፡ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምጽ ሆነ ድምጹም<< ኤልያስ ሆይ በዚህ ምን ታደርጋለህ?>> የሚል የእግዚአብሔር ድምጽ ነበር፡፡ 1ኛ ነገ 19÷1-13


የዋህ በስሜቱ ኃይልና ቁጣ የለበትም፡፡ እርሱ የረጋ እና ተቃውሞ የማያስነሳ ወይም የማይቀሰቅስ ነው፡፡ፍጹም ንዴት አያገኘውም፡፡በስሜትም በስሜታዊነትም አይነሳሳም ነገሮቻችንም አይጋፈጥም ስሜቶቹ ሁል ጊዜ ሰላማዊ ናቸው የፊት ገጽታዎቹም መልካም ባህሪይ እና ደስታ የተላበሱ ናቸው፡፡ማንም ቢያስከፋውም በትዕግስት በጽናት ይጋፈጣል፡፡


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስቃዩና ወደ ስቅለት በተጓዘበት መንገድ <<ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቶቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ>> እንዴት እንደነበረ ተመልከት፡፡የዋህ ሰው ራሱን እንደታዛቢ አድርጎ በሌሎች ላይ አያስቀምጥም ራሱን እንደ ዳኛ በሌሎች ዘንድ ጣልቃ እንደሚገባ አድርጎ አያስቀምጥም፡፡ሌሎች ለመታዘብ እና በሥራቸው ላይ ለመፍረድ ለራሱ ሥልጣን አይሰጥም፡፡ማንንም አይኮንንም፡፡ ይፈርድ ዘንድ ከተገደደ ፍርዱ የጭካኔ አይሆንም፡፡

አቡነ ሺኖዳ የመንፈስ ፍሬዎች ገጽ 96

የምስጋና ሕይወት

ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል


የምስጋና ሕይወት የሚኖር ሰው የተደረገለትን ሥራ እና የተፈጸመለትን መልካም ነገር ሁሉ የማይረሳ ለዚህም ምስጋናውን በደስታ የሚገልጽ አዋቂ ሰው ነው፡፡ለእግዚአብሔር እና ለሰዎች የሚያቀርበው ምስጋና በልቡ ጽላት ላይ ተጽፎ የተቀመጠ በመሆኑ ምስጋና ከአንደበቱ ፈጽሞ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ኢየሱስ ክርስቶስ ካነጻቸው ከአስሩ ለምጻሞች መካከል አንዱን ባርኮታል፡፡ከእነርሱ አንዱ እነደተፈወሰ ባየ ጊዜ ‹‹በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ›› ኢየሱስም መልሶ ‹‹አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት ሄዱ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔር ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም››አለ፡፡ሉቃ 17-15-18 ስለዚህ ለተደረገልን ነገር ምስጋና ስታቀርብ እግዚአብሔርን እያከበርህ ለአንተ የሰጠህን ፍቅሩን እና ትሕትናውንም እየገለጽህ መሆንህን ተረዳ፡፡እግዚአብሔር በማንም በኩል አንድ መልካም ነገር ካደረገልህ ከእግዚአብሔር በተጨማሪ ያንን መልካም ነገር እንድትቀበል ምክንያት ለሆነህ ሰውም ምስጋና ስጥ፡፡


ብዙ ሰዎች በየዕለቱ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ በታላላቅ ክብረ በዓላት ላይ እና በሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ጊዜያት ላይ ብቻ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሰጣሉ፡፡ነገር ግን ‹‹ሁል ጊዜ ስለሁሉ አመስግኑ›› ኤፌ 5-20 ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ስናቀርብ ጊዜና ወቅት ጠብቀን በተለየ ጊዜ ሳይሆን‹‹ሁልጊዜ›› መሆን አለበት፡፡ምስጋናውም ደግሞ የማይቋረጥ እስከሆነ ድረስ መላ የሕይወት ዘመንን ያጠቃልላል፡፡‹‹ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ››1 ተሰ 5፤16-18 ተብሎ ተገልጧል፡፡


ይህ ትምህርት የምስጋና ጸሎት ጸሎቶችን እንደሚመራ ያስረዳል፡፡የሰርክ እና የነግህ ጸሎቶችን ጨምሮ ሁሉም የቤተክርስትያን ሥርዓቶችና አገልግሎቶች የሚጀምሩት በምስጋና ጸሎት ነው፡፡እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በማለዳ በቀትር እና በማታ እናመሰግነዋለን፡፡ በማንኛውም ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡ስለዚህ እግዚአብሔርን ስለሁሉም ነገር ጭምር ማመስገን ያስፈልጋል፡፡ምክንያቱም ሐዋርያው‹‹እግዚአብሔር ለሚወዱት እንደሀሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡››ሮሜ 8-28 አንዳለ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ በጎ ነገር ያደርግልናል፡፡

ምንጭ – አቡነ ሺኖዳ፥ የምስጋና ሕይወት ገጽ 5

ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት

ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት

እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ለሰማይ ጭፍራ ለተባለ ለቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን መርዩጥ በተባለ አገር ለከበረችበት ለቅዳሴ ቤቱ በዓል (ሰኔ 15) በሰላም አደረሰን።


የቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት፦ ከዚህ አስቀድሞ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ተሠውሮ ይኖር ነበር ጌታችንም ሊገልጠው በወደደ ጊዜ ምክንያት አደረገ ይኸውም እንዲህ ነው ቅዱስ ሚናስ ሥጋው ተደፍኖ በሚኖርበት ኮረብታ አቅራቢያ በጎችን የሚያረባ አንድ ሰው በጎቹን እየጠበቀ ይኖር ነበር። ከዚያ እረኛ በጎች ውስጥ ደዌ ያለበት አንዱ በግ በዚያ በኮረብታው አጠገብ ባለ የጒድጓድ ውኃ ተጠምቆ ወዲያውኑ ከደዌው ዳነ እረኛውም አይቶ አደነቀ ሌሎችንም ደዌ ያለባቸውን አመጣ በዚያ ውኃም በታጠቡ ጊዜ ሁሉም ዳኑ።


ከዚህም በኋላ ይህ በቦታው ሁሉ ታወቀ ደዌ ያለባቸውም ሁሉ እየመጡ አፈሩን ከውኃው ጋራ አንድ አድርገው ለውሰው በመቀባት ወዲያውኑ ይድኑ ነበሩ ምክንያቱን ግን አላወቁም። በዚያ ውኃና በአፈሩ በሽተኞችን እንደሚያድን የዚያ በግ ጠባቂ ወሬው በሮሙ ንጉሥ ዘንድ ተሰማ ለንሡም የቊስል ደዌ የታመመች ልጅ ነበረችው ወደ በግ ጠባቂውም ላካት እርሱም በጎቹን እንደ አዳናቸው አዳናት። እርሷም በተፈወሰች ጊዜ ከዚያ ቦታ ፈውስ የሚደረግበትን ምክንያት ታውቅ ዘንድ ወደደች።


ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚናስ በሕልም ተገለጸላትና ” ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተደፍኖ ስለሚኖር እነሆ አስቆፍረሽ ታወጪው ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል” አላት። ከእንቅልፍም በነቃች ጊዜ ቅዱስ ሚናስ እንዳዘዛት አደረገች የከበረ ሥጋውንም አወጣች በዚያም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠራችለት ንጉሡም በዚያ ቦታ ከተማ እንዲሠሩ መኳንንቱንና ሹሞቹን አዘዛቸው ታላቅ ከተማም ተሠራች ስሟም መርዩጥ ተባለች።

እግዚአብሔር ከቅዱስ ሚናስ ሥጋ ቊጥር የሌላቸው ድንቆችንና ተአምራትን ገለጠ። ሊቀ ጳጳሳቱም ከኤጲስቆጶሳቱ መጥቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዛሬዋ ሰኔ 15 ዕለት አከበራት በዚያቺም ቦታ የሚሠሩ የድንቆችና የተአምሮች ወሬ በቦታው ሁሉ ተሰማ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚናስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፦ የሰኔ15 ስንክሳር።


“ሰላም ለቅዳሴ ቤትከ እንተ ተሐንፀት በመርዩጥ። በትእዛዝ ንጉሥ ሥሉጥ። ሚናስ ዘአንቃሕከ በድነ ሐራውያ እምጸጥ። አስተዋጺኦሙ ዕደው ዘበበ፪ቱ ቂራጥ። መባአ ለከ ዘነሥኡ በሤጥ”። አርከ ሥሉስ(አርኬ) የሰኔ 15።


“ሰላም ለሚናስ ኅሩይ ዘክርስቶስ ሐራይ ጽድቀ ዘአብደረ እምነ ንዋይ፤ አምሳለ ወርኅ ወከመ ፀሓይ ብሩህ”። ትርጉም፦ የክርስቶስ ምርጥ ጭፍራ ከገንዘብ ይልቅ ጽድቅን የመረጠ እንደ ምሳሌው እንደጨረቃ ለደመቀና እንደ ፀሓይም ብሩህ ለኾነ ለሚናስ ሰላምታ ይገባል።

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

እግዚአብሔርን መፍራት


ብልህ ሰው መንገዱን ከመነሻው ይጀምራል ይህም እግዚአብሔርን ከመፍራት ነው፡፡ ይህ ፍርሀት ደግሞ በሂደት ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ይመራዋል፡፡ አንድ ሰው ኃጢአትን እስካደረገ ወይም የኃጢአት ምኞት በልቡ እስካለ ድረስ በውስጡ ፈሪሀ እግዚአብሔር አይኖርም፡፡ስለዚህ ሰው እግዚአብሔርን ከመፍራት መጀመር ይገባዋል ኃጢአትን የማድረግ ፍላጎት በውስጡ ቢኖር እንኳን ንስሐ ገብቶ ከኃጢአቱ መራቅ አለበት፡፡ብዙ ይፍጨረጨራል ትዕዛዛቱን ለመፈፀም እራሱን እስከማስገደድ ይደርሳል፡፡ጸሎትን፣ቃሉን ማንበብና ማሰላሰልን እንዲሁም ውዳሴን የመሳሰሉትን የፀጋ መንገዶች ይከተላል፡፡


የመንፈሳዊ መንገድ ጀማሪ ገና ከኃጢአት ነፃነትን አልተቀዳጀም ስለዚህ እራሱን ከኃጢአት ያርቃል፡፡ይህን የሚያደርገው የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳያሳዝንና እንዳያስቆጣ የቅጣቱም ተካፋይ እንዳይሆን ነው፡፡ትዕዛዙንም በፈጸመ ቁጥር በእነርሱ መደሰት እና መውደድ ይጀምራል፡፡ብዙ ሽልማት እንዳገኘ ሰው ሀሴት ያደርጋል፡፡ መልካም ማድረግን ይወዳል፡፡ ቀምሶ ወደ ወደዳቸው ንፅህና ቅድስናና መንፈሳዊነት የመራውን ትዕዛዝም ያፈቅራል፡፡እግዚአብሔርን በመፍራት ሳንኖር ፍቅሩን ልናገኝ እንችላለን ብለን ማሰብ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ፈሪሀ እግዚአብሔር ብቻ ነው ልብን አንጽቶ የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ እንዲሆን ሊያበቃው የሚችለው፡፡መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በልባችን የእግዚአብሔር ፍቅሩ ያፈሳል፡፡በዚህ መንገድ ነው እንግዲህ ሰው ከፈሪሀ እግዚአብሔር ወደ ፍቅሩ መሸጋገር የሚችለው፡፡
ይህ ሽግግር ግን በአንዴ የሚሆን አይደለም፡፡ ከብዙ ትግልና የፀጋ ተግባር በኋላ የሚደርስበትን ሊሆን ይችላል፡፡እንዲህ ባለ ትግልና ጥረት ውስጥ ነው ቁርጠኝነቱንና ልፋቱን ለእግዚአብሔር የሚያረጋግጠው፡፡ እግዚአብሔርም ውሳኔውን ሲያይ ፍቅሩን በልቡ ከማፍሰስም አልፎ ኃጢአት በውስጡ ከፈጠረው ግጭት ያጽናናዋል፡፡ ከመውደቅ ፍርሃትም ያበረታዋል፡፡


ሰው እግዚአብሔርን እወዳለው እያለ ከፍቅሩ በጣም ሊርቅ ይችላል፡፡<<ትዕዛዙን በእርሱ ዘንድ ያለች የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ>> ዮሐ 14-21 ብሎ ይናገራል፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔርን እወዳለው እያሉ ትዕዛዙን መተላለፍ የሚቻል አይደለም፡፡ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ << የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈፅሟል፡፡>> 1ዮሐ 2÷4-5፡፡ ስለዚህ ከሁሉ አሰቀድመን ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ የሚገፋፋንን ፈሪሀ እግዚአብሔር ልንይዝ ይገባል፡፡


ኃጢአት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው የፍቅርም ሆነ የፍርሀት ደረጃ ላይ አልደረሰም ገና መንፈሳዊውን ጉዞ አልጀመረም፡፡ እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ እስከኖረ ድረስ አይወደውም አይፈራውምም ከብርሃን ርቆ ገና በጨለማ ነው ያለው፡፡

✍አቡነ ሺኖዳ እግዚአብሔርን መፍራት ገፅ 82

አንዳንድ ነገሮች ስለ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት

ቅዱስ ላሊበላ ዓሥሩንም ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በጣም በሚያስገርም ሁኔታ በውስጥና በውጭ ያሉት ብዙ ቅርጾች ነገረ ድኅነትን በምሳሌ እንዲወክሉ አድርጎ ነው ያነጻቸው፡፡ የክርስቶስን መከራና በእርሱም የተገኘውን ፍጹም ዘላለማዊ ድኅነት በእያንዳንዱ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዴት አድርጎ በምሳሌ እንዳስቀመጠው እጅግ አስገራሚ ነው፡፡


በላስታ ቅዱስ ላሊበላና አካባቢው የሚገኙ ሌሎች አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፡-

ከአሥሩ የቅዱስ ላሊበላ አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ የቅዱስ ነአኵቶለአብና የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም አሸተን ማርያም በዋናነት ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጐበኛቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ በላሊበላና አካባቢው ግን እጅግ ጥንታዊና አስደናቂ የሆኑ በጣም በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ሣርዝና ሚካኤል፣ ብልባላ ቂርቆስ፣ ብልባላ ጊዮርጊስ፣ አርባዕቱ እንስሳ፣ ትርኩዛ ኪዳነምሕረት፣ ገነተ ማርያም፣ ቀንቀኒት ሚካኤል እነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ እንዲሁም ዋልድቢት ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም፣ አቡነ ዮሴፍ ገዳም፣ ገብረ ክርስቶስ ዋሻ ቤተክርስቲያን፣ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን፣ ቀደሊት ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እመኪና መድኃኔዓለምና እመኪና ልደታ፣ ማውሬ እስጢፋኖስ፣ የቅዱስ ገብረ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ማይ ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ተከዜ ኪዳነምሕረትና መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ ከ485-536 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት የታነጹ ናቸው፡፡ ሌሎቹንና በሰሜን ላስታ ያሉትን ደግሞ እነ ላሊበላና ይምርሃነ ክርስቶስ አንጸዋቸዋል፡፡

ቅዱስ ላሊበላ እኛ ከምናውቃቸው ከድንቅ ሥነ ሕንፃዎቹ ሥራ በተጨማሪ ከሺህ ዓመታት በፊት በሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙትና በመሳሰሉት ሁሉ እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከሺህ ዓመታት በፊት አዳራሾችን፣ ፎቆችን፣ የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያዎችን፣ የእንግዳ መቀበያዎችን፣ የሕፃናት ማሳደጊያዎችን፣ የሕሙማን መፈወሻዎችን፣ የሕንፃ መሳሪያዎችን፣ የትምህርት ማዕከሎችን፣ የመደጎሻ ቦታዎችን ያቋቋመ መሆኑን የብራና ገድሉ እንደሚናገር የደብሩ አባቶች ይገልጣሉ፡፡ ወደፊት ተርጎመው እንሚያቀርቡልን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ በተጨማሪ የግእዝ ቋንቋን በጽሑፍ አበልፅጎ ያቆየ ባለውለታ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ሌሎችንም በርካታ ቤተ መቅደሶች ሠርቷል፤ ከሀገራቸንም አልፎ በሱማሌ ሞቃዲሾ ላይ መቅደሰ ማርያም የተባለች ቤተክርስቲያን ሠርቷል፡፡ ክርስትናን ከግብፅ ምድር ጨርሰው ለማጥፋት ተንባላት በተነሡ ጊዜ ዓባይን ሊያግድባቸው ሲነሣ በብዙ ምልጃና ልመና ስለማራቸው በሀገሪቱ ውስጥ ክርስትና እስካሁን እንዲቆይ የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ላሊበላ ነቢይም ሆኖ፣ ሐዋርያም፣ ጻዲቅም፣ ሰማዕትም ሆኖ ጥበብ መንፈሳዊንና ጥበብ ሥጋዊን ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ንግሥናንና ክህነትን፣ ቅድስናንና ንጽሕናን በሚገባ አስተባብሮ በማያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅንነት ሲያገለግል ኖሮ ሰኔ 12 ቀን 1197 ዓ.ም ከፈጣሪው ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብሎ በዝማሬ መላእክት፣ በመዝሙረ ዳዊት ቅድስት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ሰማያዊ ክብርን ወርሷል፡፡ ክቡር ሥጋውም ራሱ ባነጸው ቤተ ሚካኤል መቅደስ ሥር በክብር ዐርፏል፡፡

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለቅዱስ ላሊበላ የገባለት ልዩ ቃልኪዳን፡-ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት በዙፋኑ ፊት የሰጠው ቃልኪዳን፡- ‹‹ዛሬ በዚህች ቀን ከአንተ ጋር እነሆ ኪዳኔን አጸናሁ፡፡ በጸሎትህ ኃይል ታምኖ በውስጣቸው የሚያመሰግን ትሠራቸው ዘንድ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የደረሰ ሁሉ አንተን አስቦ ‹አቤቱ ፈጽመህ ይቅር በለኝ› የሚለኝ፣ ‹ይህን የሚያስደንቅ ሥራ በእጁ ስለገለጥክለት ስለ ባሪያህ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ብለህ ይቅር በለኝ› እያለ የሚጸልየውን በዚያ ጊዜ እኔ ጸሎቱን እሰማዋለሁ፡፡ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የሠራውን ኃጢአት ሁሉ አስተሠርይለታለሁ፤ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንደ እንደተወለደባት ቀን የነፃ አደርገዋለሁ፡፡ የዕዳ ደብዳቤውንም በእጅህ ትቀደው ዘንድ ለአንተ እሠጥሃለሁ፤ ዕድሜውንም በምድር ላይ አረዝምለታለሁ፤ ቤቱንና ንብረቱን ሁሉ እባርክለታለሁ፤ በተንኮል የሚከራከረው ቢኖር ድል እንዳይነሣው አሠለጥነዋለሁ፤ እግሮቹ እየተመላለሰ ወደ ቤተክርስቲያን የገሠገሠ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በኤዶም ገነት ውስጥ እንዲመላለስ አደርገዋለሁ፤ መባዕ የሚያገባ ሁሉ ጥቂትም ቢሆን ብዙም ቢሆን በእጅህ ከምሠራው ከቤተ መቅደሴ የሚያመጣውን መባዕ ሁሉ ቀኝ እጄን ዘርግቼ ከእጁ ፈጽሜ እቀበለዋለሁ፡፡ ከዕጣንም ወገን በየአይነቱ ያገባ ቢኖር እንደሰው ልማድ ሥጋዬን እንደቀባበት እንደ ኒቆዲሞስ ሽቱ እቀበለዋለሁ፣ በቢታንያ እንደቀባችኝ እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መዓዛውን አሸትለታለሁ፤ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ የመንግሥቴ ወንጌል በተሰበከበት ስሟን ይጠሩ ዘንድ እንዳዘዝኩ ሁሉ ትጉሃን በሚሆኑ በሰማያውያን መላእክት ከተሞች ስሙን ይጠሩት ዘንድ አዛለሁ፡፡ ለመብራት የሚሆን ዘይት ቢያገባ በይቅርታዬ ዘይትነት ራሱን አወዛዋለሁ፡ ሰውነቱ ለዘለዓለሙ አይሻክርም፣ ከፊቱም የብርሃን መብራት አይጠፋም፡፡ ወደ ሠርግ ቤት ከሚገቡ መብራታቸው ካልጠፋባቸው ከልባሞች ደናግል ጋር በመጣሁ ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል፡፡››

በኢየሩሳሌም ሳለ ጌታችን የስቅለቱን መከራ በራእይ ካሳየው በኋላ የሰጠው ቃልኪዳን፡- ‹‹ለሌሎቹ ጻድቃን ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ወቅት በፍጹም ልቡናቸው እንደሚገባ ያገለገሉኝን ዋጋቸውን ሰጠኋቸው፣ ለአንተ ግን በሞት የምትለይበት ጊዜ ሳይደርስ በሕይወትህ ሳለህ ኪዳንን ሰጠሁህ፡፡ ማደሪያህ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ይሆናል፡፡ አቀማመጥህ በቀኜ ነው፣ ደቀ መዛሙርቴን በ12 ወንበር ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ እንዳልኳቸው አንተም ወንበርህ ከወንበራቸው አያንስም፤ ብርሃንህ ከብርሃናቸው፣ ክብርህ ከክብራቸው አያንስም፤ ኪዳንህም ከሰጠኋቸው ኪዳን አያንስም፤ ርስትህ ዕድል ፈንታህ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ የሰጠሁህን ቃልኪዳንና ገድልህን የሚያቃልል ሁሉ ዕድል ፈንታው ከአንተ ጋር አይሁን፣ ርስት ጉልቱም ከአንተ ርስት ጉልት አይገኝም፤ የጸናሁልህን ቃልኪዳን የማያምን ያ ሰው እኔን ክርስቶስን እግዚአብሔር አይደለም እሩቅ ብእሲ ነው እንጂ እንደሚለኝ ሰው ይሁን፡፡ መጽሐፍህን ሰምቶ የተቀበለ ሁሉ የመንግሥቴን ወንጌል እንደተቀበለ ይሁን፤ አንተን ያከበረ እኔን እንዳከበረ ይሁን፡፡ ደቀ መዛሙርቴን እናንተን የሰማ እኔን የሰማ ነው፣ እናንተን የካደ እኔን የካደ ነው እንዳልኳቸው አሁንም አንተን የሰማ ቃልኪዳንህንም ያመነ እኔን ጌታህን የሰማ ነው እልሃለሁ፡፡ መከራህንና ቃልኪዳንህን የካደ ሰው ቢኖር እኔ በምድር የተቀበልኩትን መከራ እንደ ካደ ሰው ነው፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጸሎትህ ኃይል የታመኑ ሁሉ ማደሪያቸው ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለቤተክርስቲያኖችህ አምኃ የሰጠ ቢኖር እንደ ደሜ ፍሳሽ እንደ ሥጋዬ ቁራሽ አድርጌ እቀበለዋለሁ፡፡››

ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ ጌታችን የሰጠው ቃልኪዳን፡- ቅዱስ ላሊበላ ጌታችን ባሳየውና ባዘዘው መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱን አንጾ ከጨረሰ በኋላ በቀኝና በግራው ዓሥር ዓሥር ኪሎ የሚመዝን የዓለት ድንጋይ ተሸክሞ ለ7 ዓመት ሲጾም ሲጸልይ ከኖረ በኋላ ጌታችን ተገልጦለት በፊት የገባለትን ቃልኪዳን በዚህም ጊዜ በድጋሚ አረጋግጦለታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹…ወደ ደጅህ የመጡት ሁሉ አስራት ይሁኑልህ፣ አንተ ከገባህበትም ይግቡ፣ አንተንም ከ12ቱ ሐዋርያት ጋር በፍርድ ቀን 13ኛ አደርግሃለሁ፡፡ ያነጽካቸውን ቤተ መቅደሶች የተሳለመውን ኢየሩሳሌምን እንደተሳለመ አደርግለታለሁ፤ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ በዚህ ቦታ ላይ መጥቶ አማልደኝ ያለውን፣ በአማላጅነትህ የተማጸነውን ሁሉ እስከ 15 ትውልድ ምሬልሃለሁ›› ብሎ የመጨረሻውን ቃልኪዳን ሰጥቶታል።

ሰላም ለላሊበላ ሐናጼ መቅደስ በጥበብ
በዕብን ይቡስ እንበለ መሬት ርጡብ
በዘይትአመር ሎቱ ምስፍና ወምግብ
ዝንቱ መዓር ተድላ ነገሥት ወሕዝብ
በእለተ ተወልደ ተዐግተ በንህብ

( በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ከዕንጨት እና ከጭቃ ያይደለ ድንጋዮች እንደ ጭቃ እየተሳቡለት ቤተ መቅደሶቹን ላነጸ ንጉሥ ላሊበላ ሰላምታ ይገባል። ነጋሢነቱን እና ምስፍናውን ይጠይቅለት ዘንድ የነገሥታት እና የምዕመናን ሁሉ ደስታ ይሆን ዘንድ ጻድቅ ላሊበላ በተወለደ ጊዜ በንብ ተከበበ። )

ከቅዱስ ላሊበላ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!!