የባዕድ ምድር ባለርስቶች

   እንደ ዓለም አቀፍ የሥነ ሕዝብ ምንጮች ቁጥሩ፣ ወደ ሁለት ተኩል ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይኖራሉ። አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ደግሞ የአብዛኞቹ ነባር መዳረሻ ሲሆኑ ቁጥሩ የማይናቅ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በአውስትራሊያ፣ በሩቅ ምሥራቅና በአፍሪካ ውስጥ ይገኛል።እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ለተሻለ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔሀብታዊ(Economic) ሕይወት በሄዱባቸው ሀገራት ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፅሙበት ቦታና ሁኔታ ማግኘት ነው። በተለይ አኀት አብያተክርስቲያናት እንኳን በማይገኙባቸው አካባቢዎች ሕፃናት ሳይጠመቁ፣ አዋቂዎች ንስሀ ገብተው ወደ መስዋዕተ ወንጌል ሳይቀርቡ፣ የቅዳሴው ድምፅ፣ የዕጣኑ መአዛ እየናፈቃቸው ይኖራሉ።

በዚህ ኑሮ ውጥረት በሆነበትና ራስን ለማሸነፍ የማይሆነውን ለመሆን በሚገደዱበት የስደት ሕይወት የልጆቿን ጥያቄዎች መሠረት አድርጋ ሐገረ ስብከቶችን መመሥረት የጀመረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአሁን ሰዓት በውጪው የዓለም ክፍል ወደ ፳፭ አኅጉረ ስብከቶች ያሏት ሲሆን ይህም ከጠቅላላው የሀገረ ስብከቶች ቁጥር ሢሶውን(1/3) ይሸፍናል።በውጪው ዓለም የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ መስፋፋት የተጀመረው በሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጊዜ ሲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ደግሞ የሥርጭት አድማሱ ተስፋፍቷል። ቤተ ክርስቲያን እንደ ግሪክና የካረቢያን ሀገራት ሕጋዊ ሰውነትንም መጎናጸፍና የልዩ ልዩ ኅብረቶች አባል እስከመሆን ደርሳለች።

ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በኪራይ በሚገዙ አዳራሾች፣ ከአኀት አንዳንዴም ባስ ሲልም ከምሥራቅ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ አብያተክርስቲያናት ጋር በፈረቃ ሥርዓተ አምልኮን በመፈፀም ነው። ይህ ደግሞ በሀገራቸው ከለመዱት አንጻራዊ ነጻነት የማምለክ፣ የመማማር ዕድልና በፈለጉበት ሰዓት ወደ ቤተክርስቲያን በመምጣት ብሶታቸውንም ሆነ ምስጋናቸውን ከማቅረብ ፍላጎታቸው ጋር የማይስማማ ነው። በኪራይም ሆነ በውሰት ቦታዎች ላይ ቅዳሴው አለቀ አላለቀ፣ መርሐግብር ተዘረጋ ታጠፈ፣ የአከራዮቻቸው ችግር አይደለም። በመሆኑም እንዲወጡ ወይም ኪራይ እንዲጨምሩ ይደረጋሉ። ይህንን ችግር ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ የራስ ቤተመቅደስ መገንባት ወይም መግዛት ብቻ መሆኑን በመረዳታቸው አብያተ ክርስቲያናት ፊታቸውን ወደዚህ ለማዞር ተገደዋል።በዚህ በያዝነው የታኅሣሥ ወር ውስጥ ብቻ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት የሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል በአሜሪካ ግዢው ተከናውኗል። በተያያዘም በእንግሊዝ ሎንደን የጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም የግዢና ዕድሳት ወጪ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል። ባሳለፍነው ኅዳር ወር ደግሞ በቻይና የደብረ ምሕረት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተባርኮ ጀምሯል። ከዚህ ቀደም በካሊፎርኒያ፣ በኳታር፣ በጀርመንና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መሰል ተግባራት ተጀምረዋል፣ እየተከናወኑም ነው።

እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት መግዛትና መገንባት የዕለት ጉርስ ፍለጋና የቤተሰቡን ሕይወት ለመቀየር ከሀገር ለወጣው ለስደተኛው ምእመን ቀላል ነገር አይደለም። የ፳፻፲፮ቱ የእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት የክብር ተሸላሚውና ለሦስት የውጭ አብያተክርስቲያናት ግንባታና ግዢ ገንዘብ ያሰባሰበው ኮሜዲያን እሸቱ ሲናገር “ኢትዮጵያውያን በየሀገራቱ በቁጥር አናሳ ናቸው። ብቻቸውን ይህን ማድረግ አይችሉም። ያሉትም ከጉድለታቸው ቀንሰው አብያተክርስቲያናትን እያነፁ ነው። ይሄ ቅንጦት አይደለም ለዛም ነው ገቢ የምናሰባስበው” ይላል። አብያተክርስቲያናቱ የሚገዙት በብድርና ዕርዳታ ነው። “ኢትዮጵያውያን በሰው ሀገር የብድር ዕይታቸውን አስተካክለዋል” የሚሉት ደግሞ ከማኅበረ ቅዱሳን ቴቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ናቸው።በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያንን በባዕድ ምድር ባለርስት ማድረግ የቦታ ባለቤት በማድረግ ብቻ የሚወሰን አይደለም ይልቁንም ቤተክርስቲያን በባዕድ ከተሞች ልቡ ከቤተክርስቲያን የተሰደደበት ስደተኛ ልጇና ከኢትዮጵያ ውጫ በተወለደው ልጇ ልብ ላይም ባለርስት የሚያደርጋት ጭምር ነው። ካህናትና ምእመናን ያለመሳቀቅ ስብሐተ እግዚአብሔርን የሚያደርሱበት፣ ሕፃናትና ወጣቶች በሥነምግባር ታንፀው ስለ ቤተክርስቲያን የሚማማሩበት፣ ደስ ሲሰኙ መዝሙር የሚዘምሩበት፣ ሲከፋቸው ከዓለም ፊት የሚሸሸጉበት ጭምር ነው። አያድርገውና እንደ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካው ኢትዮጵያውያንን  ዓላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሲከሰቱም ብቸኛ መጠለያ ካምፓቸው ቤተክርስቲያን ናት። የእነዚህ ቦታዎች መኖር የምስካየ ኅዙናንነት ተልእኮዋን ያስፋፋዋል። ከራሷ አልፎ ለኤርትራውያን ወንድሞችም ጭምር የእነዚህ አብያተክርስቲያናት መኖር የተስፋ ምልክት ነው።በዚህ ሳይገደብ እነዚህ ይዞታዎች የወንጌል  ብርሃን ያልበራላቸውን የሀገሩን ነዋሪዎች ወደ ክርስቶስ አካልነት የመጥራት ምቹ ዕድልም በመስጠት በሀገሬው ልብ ውስጥም ባለ ርስት እንድትሆን ያደርጋታል። በመጣውና በሄደው ነገር ሁሉ የሚከፋፈለውን ስደተኛ ማኀበረሰብ ኅብረት አጠናካሪ ጭምር ነው። የዛሬውን በዚህ አበቃን አምላከ ቤተክርስቲያን በውስጥም በውጪም ያሉ ልጆቿን ይጠብቅ! ምርኮዋንም ያብዛ!

ወጥመድ

“ዘወትር በወጥመዶች መካከል እንደምትኼድ በገደልም መካከል እንደምትመላለስ ዕወቅ”(ሲራ9:13)
ከመስከረም 26 ጀምሮ እስከ ኅዳር 6 ድረስ ወርኅ ጽጌ ብለን በምንጠራው ይህ ወቅት ቅድስት በቤተክርስቲያናችን የአምላክ እናት የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያምንና የልጇ ክርስቶስን ስደት እያሰበች በአበባ ታጅባ ሌሊቱን በሙሉ በማኅሌት ታመሰግናለች።
ታድያ እናንተስ እንዴት አደራችሁ? ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ነጠላችሁን አጣፍታችሁ አጥቢያችሁ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ለማኅሌት ተፋጠናችሁ? አበባ ይዛችሁ “ልጅሽን ታቅፈሽ እመቤቴ ሆይ ነይ ማርያም”እያላችሁ ከሊቃውንቱ ጋር ወረባችሁ? ሌሊቱን ሙሉ ነጫጭ ለብሰው “አክሊለ ጽጌማርያም”ከሚሉምዕመናን መካከልበእጣኑ ልዩመዓዛታውዳችሁ፡የከበሮድምጽእየሰማችሁየቅዱሳን መላእክትን ምግብተመገባችሁ? ኪዳንአደረሳችሁ? ታላቁን የቤተክርስቲያን ጸሎት ቅዳሴን አስቀደሳችሁ? ለምን? ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለወፎች ክንፍ የተሰጣቸው በወጥመድ እንዳይያዙ ነው። ሰዎችም የማሰቡ ኃይልን የተሰጣቸው ኃጢአትን እንዲያስወግዱ ነው በማለት ይነግረናል። ሊቁ ይህንን የሚነግረን እንሰሳት በወጥመድ መያዝ እንደማይፈልጉ ሊያስረዳን አይደለም።ይልቁኑ የማሰብ ኃይል ተሰጥቶን ሳለ ይባስ ብለን ከምድር አራዊት በታች የማናስተውልከኾንን ሊደረግልን የሚችል ምሕረት ወይም ይቅርታ እንደምን ያለ ምሕረት እንደምንስ ያለ ይቅርታ ነው? ብሎ በተግሳጽ ከተያዝንበት ሊመልሰን ነው። የሚደንቀው ነገር ደግሞ እንሰሳት ሲሆኑ፡ የያዛቸው ወጥመድ ተመልሶ የማይ’ዛቸው መኾኑነው።
እንደምታውቁት ወጥመድ እንሰሳትን ለመግደል፡ ወይንም ደግሞ ለመያዝ የምንጠቀመው መሳሪያ ነው። ወጥመድ ስናጠምድ ፡ የሚወዱትንና አይተውት ሊያጓጓቸው የሚችሉ ነገሮችን ከፊት በማስገባት ነው። በወጥመድ የተያዘ እንሰሳ መጨረሻው የሚሆነው ወይ መሞት ወይንም ደግሞ የተጠመደበትን አላማ ሲፈጽሙ መኖር ነው። ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስየሰውን ልጅ ዓለም እንደፈለገ ለማድረግ የሚጠበቅበት አንዱንና ዋነኛውን የሰውነት ክፍል ብቻ መያዝ፡ ማዘናጋትና መቆጣጠር ነው። አእምሮን። ለሰው ልጅ “እንደ ባለአእምሮ ተመላለሱ”የሚል ትእዛዝ እስኪሰጠው ድረስ አእምሮው ኃያልና ለሚሰራቸው ነገሮች ሁሉ ዋና ክፍል ነው።ታድያ ይህ ክፍል በወጥመድ በተያዘ ጊዜ መላ ሰውነት አይንቀሳቀስም።ውጤታማ አይሆንም።
አብዛኞቻችን ከስልኮቻችን ጋር ያለን ቁርኝት የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ ከተቀመጥን እንዳንነሳ፡ ከምንም በላይ ደግሞ አምሽተን ተኝተን ጠዋት ላለማስቀደሳችን፡ ማጠናቀቅ የሚገቡንን ስራዎች ጨርሰን ወደ ቤተክርስቲያን እንዳንሄድ ምክንያቶቻችን ናቸው።አንድ ደቂቃ ብቻ ውሰዱና አስቡት በአንድቀን ምን ያህል መንፈሳዊ መጻሕፍትን ታነባላችሁ? ምን ያህል ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ትማራላችሁ? በቀን ለምን ያህል ደቂቃ ጸሎት ታደርሳላችሁ? ምን ያህል የእግዚአብሔርን ፍቅር ታስባላችሁ? በሌላ በኩልስ በእጃችሁ የምትይዙት ስልክ ይህንን አእምሮዋችሁ ምን ያህል ተቆጣጠረው? ምን ያህል ሰዓታትን በስልክ ታጠፋላችሁ? በስልክ ላይስ ለተመለከታችሁት አሉታዊ፡የማይጠቅም ከእናንተ ጋር የማይገናኝና
የማይመለከታችሁ ነገር ምን ያህል ታወራላችሁ? ምን ያህል ስልካችሁ አእምሮዋችሁን ፡ ሰዓታችሁን ጉልበታችሁን ይመጠዋል? ያደርቀዋል? ይቆጣጠረዋል? መልሱን ለእናንተ ትተነዋል!!!

ብሥራተ ገብርኤል

ትመስሊ ፊደለ
ወትወልዲ ወንጌለ
ወታገምሪ መስቀለ
ፊደልን ትመስያለሽ
ወንጌልን ትወልጃለሽ
መስቀልን ትወስኛለሽ
__
መጽሐፈ ሰዓታት

  እንኳን ለጌታችን የጽንሰት በዓል
      በሰላም አደረሳችሁ!
     _______________
 የደብረ ገሊላ ዐማኑኤል ካቴድራል እግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት
     እግዚአብሔር ምስሌነ
   EGZIABHER MESLENE
    ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
  join  us on t.me/EMislene

ምድራዊ መልአክ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

༺ ༻
የአባታቸው ስም ስምዖን ፣የእናታቸው ደግሞ አቅሌስያ ይባላሉ። በደቡባዊ ግብፅ ይኖሩ ነበር።በትዳር ሲኖሩ ልጅ ባለመውለዳቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ልጅ እንዲሰጣቸው ይጸልዩ ነበር ።
ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል “ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል” ይላል (ማቴ ፯÷፯-፰)
አቅሌስያ እግዚአብሔን የሚፈራ ልጅ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚሆንልጅ እንዲሰጣት እግዚአብሔርን የማያውቅ ከሆነ ግን ማኅፀኗን እንዲዘጋው ትለምን ነበር።ልጅ እንደምትወልድ ተነግሯት ወደ ቤቷ ተመለሰች።
-የሚሳነው የሌለ እግዚአብሔር ከ30በኋላ መጋቢት ፳፱ ሌሊት የአቅሌስያ ማኅፀን መልካም ፍሬ አፈራ።
በእግዚአብሔር ኃይል የተዘራው ፍሬም አፍርቶ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ለክርስቲያ ተስፋ የሚሆን ልጅ ተወለደ።ወዲያው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስሙን ገብረ መንፈስ ቅዱስ አለው።እንደ ተወልዱ ስብሐት ለአብ ፣ ስብሐት ለወልድ ፣ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣቸውን ፈጣሪ አመስግነዋል።
የእናታቸውንም ጡት ሳይቀምሱ በእግዚአብሔር ተአምር. እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይኖሩ ጀመሩ። ስምዖን እና አቅሌስያም ባዩት ነገር ተደነቁ።በዚህም ሁኔታ ፫ዓ ዓመታት ተቆጠሩ።ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ታዞ ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ተቀብለህ ገዳማውያን ወዳሉበት ውሰደውና ከአበምኔቱ በር አስቀምጠው ስለምግቡ እንዳይጨነቁ ፣ምግቡም ቃለ እግዚአብሔር ነው ብለህ ንገር አለው።
ቅዱስ ገብርኤልም ሕፃኑን አቅፎ ወደ ፯ኛው ሰማያት ወስዶ ከእግዚአብሔር ጋር አገናኘው።
እግዚአብሔርም ከእድንግል ማርያምና ከቅዱሳኑ ጋር እንዲገናኙ መልአኩን አዘዘው።መልአኩም መልሶ ወደ አባ ዘመደ ብርሃን ወሰደው ።ሕፃኑን አባ ዘመደ ብእሃን በር ላይ አገኙት፣ደስ ብሏቸውም ተቀበሉት።አስተምረቅ መዓርገ ዲቁና አቡነ አብርሃም ከተባሉ ጳጳስ እንዲቀበሉ አደረጓቸው።
እግዚአብሔር 60 አንበሶችና 60 ነብሮችም አብረዋቸው ይኖሩ ነበር።እነዚህን ምን አበላቸዋለሁ አሉ ጻድቁ? “የረገጥከውን እየላሱ ይጠግባሉ፣ወደ እኔም እስክተመጣው አብረውህ ይኖራሉ” አላቸው።
ከራስ ፀጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸውም ፩ ክንድ ከስንዝር የሚሆን ፀጉር በቀለላቸው።ከሰው ተለይተው ፃድቁ በጫካ ከአናብርትና ከአናብስት ጋር ይኖሩ ጀመር።
በግብፅ ለ፫ ዓመታት ሲጋደሉ ኖረው ወደ ኢትዮጵያ ለመሔድ ተነሡ። ምድረ ከብድ ላይም ለመጀመሪያ ጊዜ እግራቸውን የኢትዮጵያን አፈር ነካ።ከዚያም መልእከ ወደ ደብር ቅዱስ ዝቋላ ወሰዳቸው።
ከባሕር ዳር ቁመው የኢትዮጵያን ሰዎች ኃጢአት ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፣ ወደ ባሕር ተወርውረው በመዘቅዘቅ ይጸልዩ ነበር።መልአከ እግዚአብሔር ውጣ ሲላቸው መላውን የኢትዮጵያ ን ሕዝብ ካልማርክልኝ አልወጣምብለው ተጋድሎአቸውን ቀጠሉ። መቶ ዓመታት ያህል በባሕር ወድቀው ከጸለዩ በኋላ ጌታችን ወደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሄዶ መላውን ሕዝብ ምሬልሃለሁ ውጣ አላቸው።ሰይጣን ሲፀልዩ በቊራ ተመስሎ ፪ቱንም ዐይኖቻቸውን አጠፋቸው።ሳያቋርጡ ፀለዩ ።
ቅዱስ ጳውሎስ ” ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ” እንዲል (፩ ተሰ ፭÷፲፰) እስከ ፯ ሱባኤም እንደ ቆዩ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ወርደው ዐይናቸውን እፍፍ ቢሉባቸው ከቀድሞው የላቀ ብርሃን አገኙ።ወደ ዝቋላ ሂደው መቶ ዓመት ሲዋጓቸው የነበሩትን አጋንንትን አጠፏቸው።
ምንጭ፣÷ ገድለ መንፈስ ቅዱስ
ሐመር መጽሔት ጥቅምት 2008 ዓ/ም
ከጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን።

💧⚡️እንኳን ለሰማዕተ ክርስቶስ ለቅድስት አርሴማ አመታዊ በዓል አደረሰን✨

“ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደዳለን እንደሚታረዱ በጎችም ተቆጠርን።”
ሮሜ 8፤36
መስከረም 29 ቀን የምስክርነት በዓልዋ
አንገትዋ በሰይፍ ተከሎ የወደቀችበት
ዐብይ በዓል ነው
የገነት ሙሽራ የወንጌል ፍሬ የወራዙት መቅረዝ የነገሥታት ሥጦታ ያላማለላት የውበት ደም ግባት ከንቱነት በተግባር ያሳየች በአላውያን ነገሥት ውልድ ፍጡር ቤተክርስቲያን ድንጋይ ሎቱ ስብሐት በሚሉ መሐል ቆማ አምላኬ እግዚእነ ኢየሱስ ክርሰቶስ ነው ብላ የመሰከረች፤
ክብር ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የክብሩን ጸዳል ያበራባት እናታችን ቅድስት አርሴማ በረከትዋ ይደርብን በቃልኪዳንዋ ትጠብቀን ምልጃ ጸሎትዋ አይለየን።
🙏አሜን አሜን አሜን🙏

መንፈሳዊነት ምንድነው ?

ለመሆኑ መንፈሳዊነት ምንድን ነው፡፡ ረዥምቀሚስ መልበስ ነው? ፀጉርን በአሮጌ ሻሽ መሸፈን ነው? ገላን ያለመታጠብ ነው? አንገትን መድፋት ብቻ ነው? ቀስ ብሎ መናገር ነው? ኋላ ቀርነት ነው? አይመስለኝም፡፡ ቴሌቭዥን አለማየት፣ኢሜይል አለመጠቀም ነው? ከጸሎት መጻሕፍት በቀር ሌላ ነገር አለማንበብ ነው? መንፈሳዊነትኮ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው፡፡ ራስን ማሸነፍ ነው፡፡ አእምሮን እና ልቡናን ቀና እና ሰላማዊ ማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ የውስጡ መንፈሳዊነት አይደለም እንዴ ወደላይ መገለጥ ያለበት፡፡ ስለ ሐዋርያት ስንናገርኮ የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ቅድስና ለልብሳቸው፣ የልብሳቸው ቅድስና ደግሞ ለጥላቸው ተረፈ ነው የምንለው፡፡ መንፈሳዊነቱ ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ ወደ ውስጥ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ «መንፈሳዊነት» ከ «መንፈሳይነት» ጋር እየተመሳሰለ የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ነው ይህችን ቃል ያመጣት፡፡ ከሁለት ቃላት «መንፈሳዊ» እና «መሳይ» ከሚሉ ቃላት ቆራርጦ «መንፈሳይ» የሚል ቃል ፈጠረ፡፡ ትርጉሙም «መንፈሳዊ መሳይ» ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈሳውያን ይመስላሉ እንጂ አይደሉም፡፡

አባ ኤፍሬም ሶርያዊ ባስልዮስን ለማየት በሄደ ጊዜ ስለ ክብረ ወንጌል ሲል ከላዩ የወርቅ ልብስ ለብሶ ፣ የወርቅ ወንበር ዘርግቶ፣ የወርቅ ጫማ ተጫምቶ በጉባኤው ላይ ባየው ጊዜ «ደገኛ መምህር የተባለው ባስልዮስ ይኼ ነውን?» ብሎ ነበር፡፡ በኋላ ግን ተአምራቱን አይቶ አድንቆታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የውጭ ገጽታ ውስጥን ሊገልጥም ላይገልጥም ይችላልና፡፡ ልክ ነው ክርስቲያናዊ አነጋገር፣ አለባበስ፣ አረማመድ፣ ገጽታ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት መንፈሳዊነት ጅልነት፣ ከርፋፋነት፣ ኋላ ቀርነት ወይንም ደግሞ፣ ንጽሕናን አለመጠበቅ ማለት ግን አይደለም፡፡ በመንፈሳዊነታቸው የሚደነቁት የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ባስልዮስ ዘቂሳርያ በዘመኑ በነበረው የግሪክ ፍልስፍና እና ዕውቀት የበለጸጉ ነገር ግን ዕውቀታቸውን እናሥልጣኔያቸውን በወንጌል የቃኙ ነበሩ፡፡

ብዙዎቻችን ከውስጥ ለሚመነጩ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ታዛዥነትን፣ ትኅትናን፣ አርቆ ማሰብን፣ ኀዘኔታን፣ ፍቅርን፣ ትጋትን ለመሰሉ ነገሮች ትኩረት አንሰጥም፡፡ ከዚያ ይልቅ ተዋንያን ሊያደርጉት የሚችሉትን የውጭ ገጽታን ብቻ በማየት መመዘን እንመርጣለን። እውነተኛው መንፈሳዊነት ግን ከመንፈሳይነት መለየት አለበት፡፡ መንፈሳይ ሰዎች የራሳቸው መለያ ባሕርያት አሏቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከውስጣዊ መንፈሳዊነት ይልቅ ለውጫዊ ነገሮች ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ማንነታቸውን ለመሸፈን ሲሉ ሕግ ከሚፈቅደው በላይ ለውጫዊ ገጽታ ይጨነቃሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ የፀጉር አያያዝ የራስዋ ባህል አላት፡፡ እነርሱ ግን ፀጉር መታጠብን ኃጢአት ያደርጉታል፡፡ ክርስቲያኖች የሚለብሱት ልብስ ራሳቸውን የማያጋልጥ እንዲሆን ትመክራለች፡፡ እነርሱ ግን ልብስ ሁሉ መሬት ካልጠረገ ይላሉ፡፡ ያደፈ በመልበስ፣ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ይመስል እጅግ ቀሰስ ብለው በመናገር፣ ሰው መሆናቸውን ረስተው ምንም ነገር እንደማይበሉ እና እንደማይጠጡ በማሳመን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በመልበስ፣ ሰንሰለት በመታጠቅ፣ ትልልቅ መቁጠርያ እጃቸው ላይ በመጠቅለል፡፡ ይበልጥ መንፈሳዊ ሆነው መታየት ይፈልጋሉ፡፡

ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው በዱርዬ እና በሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ያለውን ያህል ፈሪሃ እግዚአብሔር በአገልጋዮች ዘንድ የለም ይል ነበር፡፡

አንዳንዶች በአገልግሎት እየበረቱ ሲሄዱ ከመንፈሳዊነት ወደ መንፈሳይነት ስለሚለወጡ፡፡ጋሽ ግርማ ከበደ ከሚያስተምረው ነገር የማልረሳው ቃል አለ፡፡ «ሰው የሚጠላውን ኃጢአት ደጋግሞ ይሠራዋል» ይላል፡፡ ለምንድን ነው ደጋግሞ ይሠራዋል ያለው? እኔ እንደ ተረዳሁት መጀመርያውኑ ይህ ሰው ውስጡ ያላመነበትን እና ሊያደርገው የማይፈልገውን ነገር ነው ለማስመሰል ሲል እያወራ ያለው፡፡ ስለዚህም በውስጡ ያንን የጠላውን ነገር ላለማድረግ መንፈሳዊ ተጋድሎ ስለማያደርግ ደጋግሞ ሲሠራው ይገኛል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች መንፈሳያን ስለ አንድ

ሰው መንፈሳዊነት ደጋግመው በጥላቻ ወይንም በንቀት፣ ወይንም ደግሞ በመመጻደቅ የሚያወሩ ከሆነ ያንጊዜ አንዳች ነገር ተረዱ፡፡ ሳያስቡት እየተናገሩ ያሉት ስለ ራሳቸው ነው፡፡ መንፈሳውያን ሰዎች ስለሌሎች ውድቀት ሲያነሡ ከርኅራኄ እና ከኀዘኔታ ጋር ነው፡፡ የደስታ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ እንደ ጀብዱም አይቆጥሩትም፡፡ ለዚህም ነው በቅዳሴ አትናቴዎስ ሊቁ ስለ አዳምና ሔዋን አንሥቶ «እኛስ እናንተን ልንወቅሳችሁ አንችልም» በማለት የተናገረው፡፡ መንፈሳውያን ይነበባሉ፤መንፈሳያን ግን ይታያሉ፡፡ መንፈሳውያን ይቀመሳሉ፣ መንፈሳያን ግን ይላሳሉ፡፡ መንፈሳውያን ያዳምጣሉ፤ መንፈሳያን ግን ይለፈልፋ፡፡ መንፈሳውያን ያስተውላሉ፤ መንፈሳያን ግን ይቸኩላሉ፤ መንፈሳውያን ያጠግባሉ፣

መንፈሳያን ግን ያቁለጨልጫሉ፡፡ መንፈሳውያን ይመዝናሉ፤ መንፈሳያን ግን ያፍሳሉ፡፡ መንፈሳውያን ያርማሉ፤ መንፈሳያን ግን ይተቻሉ፡፡ መንፈሳውያን ጠላቶቻቸውን አንድ ሺ ዕድል ይሰጣሉ፤ መንፈሳያን ግን ወዳጆቻቸውን ጠላቶቻቸው ለማድረግ አንድ ሺ በር ይከፍታሉ፡፡ መንፈሳውያን ይጾማሉ፣ መንፈሳያን ይራባሉ፤ መንፈሳውያን ይጸልያሉ፣ መንፈሳያን ግን ይናገራሉ/ያነባሉ፡፡ መንፈሳውያን ሱባኤ ይይዛሉ፣ መንፈሳያን ግን ስለ ሱባኤያቸው ያወራሉ፡፡ መንፈሳውያን ይሰጣሉ፣ መንፈሳያን ግን ሲሰጡ ያሳያሉ፡፡ መንፈሳውያን ቃለ እግዚአብሔርን ያስተምራሉ፣ መንፈሳያን ግን በራሳቸው ቃላት ይጠበባሉ፤ መንፈሳውያን ወደ ውስጥ፣ መንፈሳያን ወደ ውጭ ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን የነገን፣ መንፈሳያን የዛሬን ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን ምክንያቱን፣ መንፈሳያን ድርጊቱን ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን ራሳቸውን፣ መንፈሳያን ሌላውን ያያሉ፡፡

መንፈሳውያን ከመፍረዳቸው በፊት ይመክራሉ፤ መንፈሳያን ከፈረዱ በኋላ ይመክራሉ፡፡ መንፈሳውያን ዘጠኝ ጊዜ ለክተው አንድ ጊዜ ይሰፋሉ፣ መንፈሳያን ግን ዘጠኝ ጊዜ ሰፍተው አንድ ጊዜ ይለካሉ፡፡ መንፈሳውያን ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፣ መንፈሳያን ከተናገሩ በኋላ ያስባሉ፡፡ መንፈሳውያን ይወስናሉ፣ መንፈሳያን አስተያየት ያበዛሉ፡፡ መንፈሳውያን ሰው እንዳይሞት በችግሩ ጊዜ ይረዳሉ፣ መንፈሳያን ግን ሰው ሲሞት የልቅሶ ትርኢት ያሳያሉ፡፡ መንፈሳውያን ስለ ሌሎች በጎ መናገርን ያዘወትራሉ፣ መንፈሳያን ስለ ራሳቸው በጎ መናገርን ይፈልጋሉ፡፡ መንፈሳያን ነጭ እና ጥቁር ብቻ ያያሉ፣ መንፈሳውያን ግን ግራጫንም ጨምረው ይመለከታሉ፡፡ መንፈሳዊ ሰው አንድ ሰው ነው፡፡ መንፈሳይ ሰው ግን ሁለት ሰው ነው፡፡ ውጩ ሌላ ውስጡ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ገና ያልተሸነፈ፣ እንዲያውም እየገነገነ እና እየገነተረ የሚሄድ ክፉ ጠባይ አለባቸው፡፡ አይጋደሉትም፡፡ አይጸየፉትም፡፡ ሊያሸንፉት አይፈልጉም፡፡ አይቃወሙትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ጥሩ ተዋናይ በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በአረማመድ፣ በመቅለስለስ፣ በመሸፋፈን እና ለሰው መስለው በመታየት ሊገልጡት የሚፈልጉት ሌላ ማንነት ደግሞ አላቸው፡፡ ይህ የውስጥ ማንነት አንድ ቀን ያሸንፍና እንደ ዴማስ ያስኮበልላቸዋል፡፡ ያን ጊዜ በሰው ይፈርዱ የነበሩትን ነገር ሁሉ አብዝተው ያደርጉታል። ወጣ ወጣ እና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ የተባለው ይደርስባቸዋል፡፡ አንዳንዴ መንፈሳይነት ሕይወት ሳይሆን በሽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያውም የአእምሮ መዛባት/ mental disorder/፡፡ በሁለት ማንነቶች መካከል እየተምታቱ መኖር፡፡ መንፈሳዊ ሰው ኃጢአት ቢሠራ እንኳን ንስሐ ይገባበታል፡፡ ያርመዋል፡፡ ይጋደልበታል፡፡ ኃጢአቱን በመሸፈን እና በማስመሰል ሳይሆን በመጋደል እና በማስወገድ ያምናል፡፡ መንፈሳይ ሰው ግን ሌሎች እንዳያዩት እንጂ እግዚአብሔር እንዳያየው አይጨነቅም፡፡ አሁን እኛ እስኪ ራሳችንን እንየው መንፈሳዊ ነን ወይስ መንፈሳይ?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዘጋጅ፡ ኃይለ ገብርኤል

ጸሐፊ፡- ዲ/ን ዳንኤል ክብረት