
እንደ ዓለም አቀፍ የሥነ ሕዝብ ምንጮች ቁጥሩ፣ ወደ ሁለት ተኩል ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተሰራጭተው ይኖራሉ። አሜሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ደግሞ የአብዛኞቹ ነባር መዳረሻ ሲሆኑ ቁጥሩ የማይናቅ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በአውስትራሊያ፣ በሩቅ ምሥራቅና በአፍሪካ ውስጥ ይገኛል።እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ለተሻለ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔሀብታዊ(Economic) ሕይወት በሄዱባቸው ሀገራት ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፅሙበት ቦታና ሁኔታ ማግኘት ነው። በተለይ አኀት አብያተክርስቲያናት እንኳን በማይገኙባቸው አካባቢዎች ሕፃናት ሳይጠመቁ፣ አዋቂዎች ንስሀ ገብተው ወደ መስዋዕተ ወንጌል ሳይቀርቡ፣ የቅዳሴው ድምፅ፣ የዕጣኑ መአዛ እየናፈቃቸው ይኖራሉ።
በዚህ ኑሮ ውጥረት በሆነበትና ራስን ለማሸነፍ የማይሆነውን ለመሆን በሚገደዱበት የስደት ሕይወት የልጆቿን ጥያቄዎች መሠረት አድርጋ ሐገረ ስብከቶችን መመሥረት የጀመረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአሁን ሰዓት በውጪው የዓለም ክፍል ወደ ፳፭ አኅጉረ ስብከቶች ያሏት ሲሆን ይህም ከጠቅላላው የሀገረ ስብከቶች ቁጥር ሢሶውን(1/3) ይሸፍናል።በውጪው ዓለም የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ መስፋፋት የተጀመረው በሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጊዜ ሲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ደግሞ የሥርጭት አድማሱ ተስፋፍቷል። ቤተ ክርስቲያን እንደ ግሪክና የካረቢያን ሀገራት ሕጋዊ ሰውነትንም መጎናጸፍና የልዩ ልዩ ኅብረቶች አባል እስከመሆን ደርሳለች።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በኪራይ በሚገዙ አዳራሾች፣ ከአኀት አንዳንዴም ባስ ሲልም ከምሥራቅ ኦርቶዶክስና ካቶሊክ አብያተክርስቲያናት ጋር በፈረቃ ሥርዓተ አምልኮን በመፈፀም ነው። ይህ ደግሞ በሀገራቸው ከለመዱት አንጻራዊ ነጻነት የማምለክ፣ የመማማር ዕድልና በፈለጉበት ሰዓት ወደ ቤተክርስቲያን በመምጣት ብሶታቸውንም ሆነ ምስጋናቸውን ከማቅረብ ፍላጎታቸው ጋር የማይስማማ ነው። በኪራይም ሆነ በውሰት ቦታዎች ላይ ቅዳሴው አለቀ አላለቀ፣ መርሐግብር ተዘረጋ ታጠፈ፣ የአከራዮቻቸው ችግር አይደለም። በመሆኑም እንዲወጡ ወይም ኪራይ እንዲጨምሩ ይደረጋሉ። ይህንን ችግር ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ የራስ ቤተመቅደስ መገንባት ወይም መግዛት ብቻ መሆኑን በመረዳታቸው አብያተ ክርስቲያናት ፊታቸውን ወደዚህ ለማዞር ተገደዋል።በዚህ በያዝነው የታኅሣሥ ወር ውስጥ ብቻ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት የሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል በአሜሪካ ግዢው ተከናውኗል። በተያያዘም በእንግሊዝ ሎንደን የጽርሐ ጽዮን ቅድስት ማርያም የግዢና ዕድሳት ወጪ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል። ባሳለፍነው ኅዳር ወር ደግሞ በቻይና የደብረ ምሕረት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተባርኮ ጀምሯል። ከዚህ ቀደም በካሊፎርኒያ፣ በኳታር፣ በጀርመንና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች መሰል ተግባራት ተጀምረዋል፣ እየተከናወኑም ነው።
እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት መግዛትና መገንባት የዕለት ጉርስ ፍለጋና የቤተሰቡን ሕይወት ለመቀየር ከሀገር ለወጣው ለስደተኛው ምእመን ቀላል ነገር አይደለም። የ፳፻፲፮ቱ የእግዚአብሔር ምስሌነ ሰንበት ት/ቤት የክብር ተሸላሚውና ለሦስት የውጭ አብያተክርስቲያናት ግንባታና ግዢ ገንዘብ ያሰባሰበው ኮሜዲያን እሸቱ ሲናገር “ኢትዮጵያውያን በየሀገራቱ በቁጥር አናሳ ናቸው። ብቻቸውን ይህን ማድረግ አይችሉም። ያሉትም ከጉድለታቸው ቀንሰው አብያተክርስቲያናትን እያነፁ ነው። ይሄ ቅንጦት አይደለም ለዛም ነው ገቢ የምናሰባስበው” ይላል። አብያተክርስቲያናቱ የሚገዙት በብድርና ዕርዳታ ነው። “ኢትዮጵያውያን በሰው ሀገር የብድር ዕይታቸውን አስተካክለዋል” የሚሉት ደግሞ ከማኅበረ ቅዱሳን ቴቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ናቸው።በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያንን በባዕድ ምድር ባለርስት ማድረግ የቦታ ባለቤት በማድረግ ብቻ የሚወሰን አይደለም ይልቁንም ቤተክርስቲያን በባዕድ ከተሞች ልቡ ከቤተክርስቲያን የተሰደደበት ስደተኛ ልጇና ከኢትዮጵያ ውጫ በተወለደው ልጇ ልብ ላይም ባለርስት የሚያደርጋት ጭምር ነው። ካህናትና ምእመናን ያለመሳቀቅ ስብሐተ እግዚአብሔርን የሚያደርሱበት፣ ሕፃናትና ወጣቶች በሥነምግባር ታንፀው ስለ ቤተክርስቲያን የሚማማሩበት፣ ደስ ሲሰኙ መዝሙር የሚዘምሩበት፣ ሲከፋቸው ከዓለም ፊት የሚሸሸጉበት ጭምር ነው። አያድርገውና እንደ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካው ኢትዮጵያውያንን ዓላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሲከሰቱም ብቸኛ መጠለያ ካምፓቸው ቤተክርስቲያን ናት። የእነዚህ ቦታዎች መኖር የምስካየ ኅዙናንነት ተልእኮዋን ያስፋፋዋል። ከራሷ አልፎ ለኤርትራውያን ወንድሞችም ጭምር የእነዚህ አብያተክርስቲያናት መኖር የተስፋ ምልክት ነው።በዚህ ሳይገደብ እነዚህ ይዞታዎች የወንጌል ብርሃን ያልበራላቸውን የሀገሩን ነዋሪዎች ወደ ክርስቶስ አካልነት የመጥራት ምቹ ዕድልም በመስጠት በሀገሬው ልብ ውስጥም ባለ ርስት እንድትሆን ያደርጋታል። በመጣውና በሄደው ነገር ሁሉ የሚከፋፈለውን ስደተኛ ማኀበረሰብ ኅብረት አጠናካሪ ጭምር ነው። የዛሬውን በዚህ አበቃን አምላከ ቤተክርስቲያን በውስጥም በውጪም ያሉ ልጆቿን ይጠብቅ! ምርኮዋንም ያብዛ!

