
ከዘመነ ሐዋርያት አንስቶ በተለያዩ ሀገራት ላይ የሠለጠኑ አረማውያን በቤተክር ስቲያን ላይ ያደረሱት ስደት በዘመኑ የነበረውን ክርስትና ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር ያሳያል። ቅድስት ቤተክርስቲያን የጸናች ናትና ሥጋቸውን እንጂ ነፍሳቸውን ማንም ሊገድል እንደማይችል እያስተማረች የማያልፈውን ዓለም እያሰቡ ከክርስቶስ ጋር መኖርን እንዲናፍቁ ታደርጋቸው ነበር። በጊዜው የነበራቸውን ቆራጥነት፣ ለሃይማኖታቸው ሲሉ የሚያሳዩትን ጭካኔ በአላውያን ወታደሮችና ነገሥታት ዓይን የሚያስደንቅ ነበር።
ክርስቲያኖቹ ከቤተ አይሁድ ይደርስባቸው የነበረው ግፍና መከራ ይልቅ ከቤተ አሕዛብ ይደርስባቸው ከነበረው በአንጻሩ የባሰ ነበር። በተለይ በሮማውያን ዘንድ የነበረው አምልኮተ ጣዖት በሀገራቸው ውስጥ ረሃብ፣ ችግርና ቸነፈር ሲነሣ በክርስቲያኖች ምክንያት አማልክቶቻቸው ስላዘኑ እንደደረሰባቸው ያስወሩና በክርስቲያኖችም ላይ ስም የማጥፋትን ዘመቻ ያሴሩ ነበር።የሕዝቡን ልብ በክርስቲያኖች ላይ ለማነሳሳት በኔሮን ቄሣር ዘመነ መንግስት በንጉሡ ኔሮን ሮም በእሳት እንድትጋይ ሆናለች። ቀድሞውን ይደርስባቸው የነበረው መከራና እንግልት በአዋጅ ጸድቆ ክርስቲያኖች በያሉበት ተሳደው እንዲገደሉ የሚል ትዕዛዝ ወጣ። ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዚሁ በኔሮን ዘመነ መንግስት ነበር። የሰማዕታቱን ዜና የሰሙ ከሮም ውጭ ይኖሩ የነበሩ ማኅበረ ምእመናን ይኽንን ክብር ለመቀበል በገፍ ወደ ሮም ይተሙ ነበር ።
ኔሮን ቄሣር በ፷፰ ዓ.ም. ከሞተ ወዲህ ላሉት ሁለት ዓመታት ሁለት ቄሣሮች ነግሠዋል። በቤተክርስቲያን ታሪክ ከ፸ – ፻፷፪ ያለው ዘመን የመሸጋገሪያ ጊዜ ተብሎ ይጠራል። በእኒኽ ዓመታት ውስጥ ሐዋርያውያን አበው (በርናባስ፣ ቀለሜንጦስ ዘሮም፣ ፖሊካርፐስ፣ ሔርማ፣ ዲዮናስዮስ፣ ፓፒየስና አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ) በእግረ ሐዋርያት ተተክተው ሲያስተምሩ የነበረበት ወቅት ነው። ከኔሮን ቄሣር በኋላ የተነሣው ወንድሙ ድምጥያኖስ ምስሉን በኤፌሶን አሰርቶ እንዲሰገድለት ትዕዛዝ አወጣ። በወቅቱ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ) ሀገረ ስብከቱ ነበረችና ሐዋርያዊ ተልዕኮውን እየፈጸመ ነበር። ይኽንን የድምጥያኖስን ተግባር አውግዞ፣ ከነበሩት የኤፌሶን ክርስቲያኖች ጋር ተቃወመ። በኋላም በድምጥያኖስ ትዕዛዝ ወደሮም ፍርድ ቤት ሄዶ ወደ ፍጥሞ ደሴት እንዲጋዝ ተደርጓል።
ከድምጥያኖስ በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ ከነበረው ጭካኔ በኋላ ከ፺፰ – ፻፲፯ ዓ.ም. የነገሠው ጨካኙ ቄሣር ትራጃን ነበር። በኃይል ብቻ ሳይሆን በዘዴና በማስፈራራት ጭምር ክርስቲያኖች ወደቤተ ጣኦት ለመመለስ ይሞክር ነበር።በአገዛዝ ቀንበራቸው በታሪክ ከነበሩ ነገሥታት ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ግፍ እጅጉን የከፋ ስለነበር በተለየ መልኩ ይጠቀሳሉ። ከትራጃን በኋላ ሀድርያን የተባለ ንጉሥ ፻፲፯ – ፻፴፰ የነገሠ ሲሆን ከበፊቱ ይልቅ መጪዎቹ ፵ ዓመታት ለክርስቲያኖች በአንጻራዊነት የእፎይታ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። ሀድርያን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት እንዳይገደሉ ትዕዛዝ አውጥቶ ነበር። ከእርሱ በኋላ የተነሣው አንቶኒዮስ ፒየስ ፻፴፰ – ፻፷፩ አንዳንድ ሕጎችን ከማሻሻል ውጪ ቀድሞ የነበረውን የአገዛዝ ስልት ይከተል ነበር። ሕዝቡ ክርስቲያኖች ላይ መከራ ሲያደርስ ግን አይከላከልላቸው። ከሐዋርያን አበው መካከል ቅዱስ ፖሊካርፐስ በ፻፶፭ ሰማዕትነትን የተቀበለው በአንቶንዮስ የንግሥና ዘመን ነበር።ከ፻፷፩-፻፷፫ የነገሠው ፈላስፋው ንጉሥ ማርቆስ አብሪሊዮስ “ክርስቲያኖች ሞገደኞች፣ ወፈፌዎች ናቸው” ይል ነበር፡፡ከ፻፹-፻፺፪ የነገሠው ቄሣር ከሞዶስ ቀስ በቀስ በዘዴ እያደረገ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ዕቅድ ነበረው፡፡ ሌሎችም እንደእነ እስክንድሮ – ሳዊሮስ (፪፻፳፪-፪፻፴፩)፣ እንደእነ ፊልጶስ ዓረባዊ (፪፻፵፬-፪፻፵፱) ያሉ ንቀውና ተጸይፈው ክርስቲያኖችን ከምንም አይቆጥሯቸውም ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የመጨረሻውን ድል ለማግኘት ብዙ ቄሣሮች ባላቸው ኃይልና ዘዴ በሙሉ ተጠቅመዋል፡፡ የመጨረሻውና የማያዳግመው ዘዴ ግን በዳክዮስ ዘመነ መንግስት (፪፻፵፬-፪፻፶፩ ዓ.ም.)የወጣው ዐዋጅ ነው፡፡

