አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

        የዚህ ቅዱስ የአባት ስም እስጢፋኖስ እና የእናቱ ስም አመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጎች ናቸው። በአክሱም ምድርም ወለዱት፤ በአደገ ጊዜም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት አስተማሩት። አባቱና እናቱም በሞቱ ጊዜ ወደ ደብረ በንኰል ገዳም ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሔዶ የምንኵስና ልብስን ለብሶ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። ፈጽሞ ከሻገተ ጎመን በቀር አይበላም፤ የሚጠጣውም ውኃ ነው። እህል በመፍጨትና ውኃ በመቅዳት ሥራ መነኰሳትን ይረዳቸው ነበር። ዘመዶቹም ወደርሱ እየመጡ በአስቸገሩት ጊዜ ወደሌላ ቦታ ሔደ። እግሮቹም እስኪያብጡ ድረስ በጾም በስግደት በመቆም ተጋደለ። ከዚያም ወደሌላ በረሀ ሔዶ አርባ መዓልት፣ አርባ ሌሊት ምንም ምን ሳይቀምስ ኖረ። አንበሶችና ነብሮች የሚያስፈሩም አራዊት ሁሉ ወደርሱ በመምጣት ይሰግዱለታል፤ የእግሮቹን ትቢያ ይልሱ ነበር። በአንዲት ዕለት በጎዳና ሲጓዝ ታላቅ ወንዝ ውኃው መልቶ አገኘ። መጽሐፍና እሳትም ከእርሱ ጋር ነበር፤ ጸሎትም አድርጎ ወደ ውኃው ገባ። ውኃውም ዋጠውና ወደታች አወረደው በእግዚአብሔርም ኃይል ወደማዶ በጣለው ጊዜ መጽሐፉ ሳይደመሰስ እሳቱም ሳይጠፋ አገኘው።

ሰይጣንም በሚያስፈሩ አራዊት እየተመሰለ ይፈታተነው ነበር። እርሱ ግን ፈጣሪውን በመታመን ልቡ የታሠረና የጸና ስለሆነ አይፈራም። እርሱም ሲጸልይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ። በምራቁም መላ ሕዋሳቱን ቀብቶ ኃይልን አሳደረበት፤ ከዚያችም ዕለት ጀምሮ እግሮቹን የሚያሥር ሆነ። ማቅንም ለብሶ በየሌሊቱ ሁሉ ከውኃ ውስጥ በመግባት የዳዊትን መዝሙር አምስት ጊዜ ያደርሳል። ቊጥር በሌለውም ግርፋት ጀርባውን ይገርፍ ነበር።አንበሶችም በበዓቱ አጠገቡ ይሰማራሉ፤ እርሱም አካላቸውን ይሰፍራል፣ ይለካል፣ ቊስላቸውንም በጥቶ እሾህና አሜከላ ያወጣላቸዋል። ከዚህም በኋላ ብዙ ደቀ መዛሙርት ወደርሱ ተሰበሰቡ፥ በተጋድሎም ተጠመዱ። ከእነርሱም የመጀመሪያው አባ ዘሩፋኤል ነው። በአንዲትም ዕለት በገዳመ ለጋስ የሚኖር ከአባ ገብረ መስቀል ጋር ተገናኘ። ከዚህም በፊት አልተያዩም ነበ፤ የእግዚአብሔርንም ገናናነት ሲጨዋወቱ ዋሉ። በራት ጊዜም ጸሎትን ሲያደርጉ የተዘጋጀ ማእድ ወርዶላቸው ተመግበው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ዕለት ከአንድ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ። እግዚአብሔርም ያደረገላቸውን ምሥጢር በሚነጋገሩ ጊዜ አባታችን አባ ሳሙኤል እንዲህ አለ “እነሆ እኔ በአርያም ቁሜ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የአምላክን መንበር ሳጥን ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆነኝ።” ለመቀደስም በሚገባ ጊዜ ኅብስትና ወይንን የተመላ ጽዋ ይወርድለታል። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ውዳሴዋን ሲያነብ ክንድ ያህል ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ ይላል። እመቤታችን ማርያምም ወደ እርሱ መጥታ የሚያበራ ዕንቊንና ንጹሕ ዕጣንን ሰጠችው።ፍልሰቱም ሲቀርብ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በክንፎቹ ተሸክሞ አወጣው። ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ተድላዋን ሁሉ አሳየው፤ ወደ ልዑል እግዚአብሔርም ዙፋን ፊት አቅርቦት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ተቀበለ። ወደ በዓቱም ሲመለስ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ ታኅሣሥ ፲፪ ቀን በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን! እኛንም በአባ ሳሙኤል ጸሎት ይማረን! በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር! ለዘለዓሙ አሜን።

ምንጭ፦ የታኅሣሥ ፲፪ ስንክሳር