ታላቁ አባ አቡፋና

በየካቲት ፳፭ ስንክሳር ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው የቅዱሱ አባታችን አቡፋና ታሪክ እንዲህ ነው ፡፡ በግብጽ ሀገር  ናይን አውራጃ በመዓልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊት አምስት መቶ ጊዜ አቡነዘበሰማያት የሚጸልዩ አባት ነበሩ። እህል ደግሞ በ፵ ቀን አንድ ጊዜ እየቀመሱ መላ ዘመናቸው በጽሞና ያሳለፉ ናቸው።
አንድ ቀን “እኔ ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ነው?” ሲሉ ዐሰቡ፤ ዓሳቡ ብዙዎቻችንጋ ያለ ግን ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው። እንዴት ቢሉ ጠቃሚ ሲባል ሰው ሞቱን ሲያስብ ንስሐ ይገባል፣ ክፋትን ይተዋል። ያልተፈቀደ ነው የተባለው ደግሞ ሰው አጭር ዕድሜ እንዳለው ቢያውቅ ሽብርና ጭንቀት ይበላዋል። ረጅም ዕድሜ እንዳለው ካወቀ ደግሞ ኃጢያት እየሠራ ልክ እንደ ኖህ ዘመን ሰዎች ለንስሐ ይዘናጋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ስለዚህ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሚለውን አስበን ልንኖር ይገባል። ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና አባ አቡፋ የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ “ዐስራ ስምንት አላቸው” እሳቸውም “ዐስራ ስምንት ምን?” ሲሉ ሳይመልስላቸው ተሰወረ። እሳቸውም “ዐስራ ስምንት ቀን ነው” ብለው ስዕለት ተሳሉ፤ ስዕለታቸውም እስክሞት አልቀመጥም የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ፲፰ ቀናት ቆመው ጸለዩ፣ ግን ሞት አልመጣም። “ዐስራ ስምንት ሱባዔ ይሆን እንዴ?” ብለው ፲፰ ሱባዔ ያዙ፤ አሁንም ሞት አልመጣም። “አይ ዐስራ ስምንት ወር ይሆናል” ብለው ቆመው ተጉ ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ይህን ጊዜ ወደ ፈጣሪ ጸለዩ፡ “ጌታዬ ያልኸኝ ዐስራ ስምንት ምንድን ነው?” አሉ። ቅዱስ መልአክ መጣና “አቡፋና ሆይ የቀረህ ዐስራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና” አለው። ቅዱሱም የገቡትን ስዕለት ሳያጥፉ ዐስራ ስምንት ዓመት እንደ ምሰሶ ተተክለው፣ ቆመው ጸለዩ። ስዕለቱን ሲፈጽሙ ዕረፍታቸውን አውቀው ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ወደ መኖሪያቸው ሔደው ራሳቸውን ዘንበል አድርገው ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ። የቅዱሱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን! ምንጭ፡ የየካቲት ፳፭ ስንክሳር

አድዋ

የዓድዋ ድል፣ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የሥነ ልቡና ልዕልና የተገኘ ነው። ጦርነቱ በሁለት አውሮፓውያን ወይም በሁለት አፍሪካውያን ሀገራት መካከል የተደረገ ቢሆን ኖሮ ጥቂትም ቢሆን የኃይል መመጣጠን ስለሚኖር ይህን ያህል አያስደንቅም ነበር። ነገር ግን በጉልበተኞች ጽንፍ ባለች በአንዲት ሀገርና በምስኪኖች ጽንፍ ባለች በሌላ ሀገር ምክንያት የተደረገ በመሆኑና ውጤቱም ሥጋ ለባሽ ከሚጠብቀው አመክንዮአዊ ውጤት እጅግ የተለየ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። ከጦርነቱ መጀመሩ አስቀድሞ ጳውሎስ ኞኞና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንደ ገለጹት ሁሉም፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደምታሸንፋት ያስቡ የነበረው ይህን አለመመጣጠን በሰውኛ መነጽር በማየት ነበር። ታዲያ ድሉ እንዴት ተገኘ? የድሉ ዋና መሠረት የሥነ ልቡናና ዐስተሳሰብ ሚዛን ነበር። የኢጣሊያ ወታደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎቻቸውና በውጊያ አቅማቸው ክፉኛ ተማምነውና መተማመናቸውም ወደ ትዕቢት ከፍ ብሎ ነበር።
“…በቅርብ ቀን ምኒልክን በቀፎ ውስጥ አሥሬ ሮማ ውስጥ አመጣዋለሁ…” ይል የነበረው የኢጣሊያ የጦር መሪ፣ የጄኔራል ባራቲዬሪ ንግግርም ይህንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ሕዝቡም ገና ጦርነቱ ሳይጀመር “ድል አድራጊው” እያሉ እርሱን መጥራታቸው የዚህ ሌላው ማሳያ ነበር። በኢትዮጵያውያን በኩል ምንም እንኳን የኢጣሊያ ዐቅም እጅግ እንደሚልቅ ቢረዱትም ከንጉሡ አዋጅ ጀምሮ ካላቸው የጦር ቁስ ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ መተማመናቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፡- ‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቶአል። እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የሀገሬ ሰው፤ ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ጣልያናዊ ተዋጊም በጦርነቱም ወቅት   “በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝና ወደ ግራ እየተመላለሰ ወደ ጦርነቱ ግቡ ኢጣሊያኖችን ማርኩ እያለ ትእዛዝ ሲሰጥና ሲዋጋን የዋለ ማነው?” ብሎ መጠየቁ እየተገለጸ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጋዥነት መገለጹም እዚህ ላይ መነሣት የሚገባው ነው። የዓድዋ ድል ብሔራዊና ዓለም-ዐቀፋዊ ትሩፋቱ ባሻገር ሃይማኖታዊ ትሩፋቱም መነገር የሚገባው ነው።
በእውነት የእግዚአብሔር ፍርድ በዕለቱ ተፈጸመ፤ ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።መልካም ዕለተ ሰንበትምንጭ፡ ሐመር መጽሔት  የካቲት ፳፻፲፫ዓ.ም.

ብስራተ ገብርኤል

ብሥራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጦ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ መወለድ ያበሠራት ዕለት፣ ታኅሣሥ ፳፪ “ብሥራተ ገብርኤል” ታላቅ በዓል ነው፡፡ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅ አስማምታ በምትፈትልበት ሰዓት ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ “ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።
ድንግል ማርያምም  “እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንዴት ይደረግልኛል?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ቅዱስ ገብርኤልም  “ማርያም ሆይ አትፍሪ! ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና። እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዩዋለሽ። ይህ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው፤ እርሱም  የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” አላት፡፡  
እርሷም “ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል፤ ወንድ ሳላውቅ?” አለቺው፡፡
መልአኩ ገብርኤልም “መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል፤ የልዑል ኃይልም ያድርብሻል” አላት፡፡
እርሷም የመልአኩን ቃል ተቀብላ “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” አለቺው፡፡
በዚህ ጊዜ አካላዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፡፡ ቅድስት ማርያም እምነቷን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋለችና በትንቢተ ነቢያት መሠረት በድንግልና ፀነሰቺው፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱፣ ኢሳ. ፯÷፲፬ )
ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ስለ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራትና ስለ አምላክ ሰው መሆን ሲመሰክር “እርሱ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ቅዱስ ገብርኤል የሚባል መልአክ ወደ አንቺ ላከ፤ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ያድራል፡፡ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፤ ከአባቱ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሺው፤ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማሕፀንሽ ተወሰነ፤ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መላኮት በማሕፀንሽ አደረ›› (ቅዳሴ ማርያም ቁ. ፵፭) ብሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የብሥራት ቀን በማሰብ ታከብረዋለች፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፤ ቅዳሴ ማርያም

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

        የዚህ ቅዱስ የአባት ስም እስጢፋኖስ እና የእናቱ ስም አመተ ማርያም ነው። እነርሱም በዘመድ የከበሩ ደጎች ናቸው። በአክሱም ምድርም ወለዱት፤ በአደገ ጊዜም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት አስተማሩት። አባቱና እናቱም በሞቱ ጊዜ ወደ ደብረ በንኰል ገዳም ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ ሔዶ የምንኵስና ልብስን ለብሶ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። ፈጽሞ ከሻገተ ጎመን በቀር አይበላም፤ የሚጠጣውም ውኃ ነው። እህል በመፍጨትና ውኃ በመቅዳት ሥራ መነኰሳትን ይረዳቸው ነበር። ዘመዶቹም ወደርሱ እየመጡ በአስቸገሩት ጊዜ ወደሌላ ቦታ ሔደ። እግሮቹም እስኪያብጡ ድረስ በጾም በስግደት በመቆም ተጋደለ። ከዚያም ወደሌላ በረሀ ሔዶ አርባ መዓልት፣ አርባ ሌሊት ምንም ምን ሳይቀምስ ኖረ። አንበሶችና ነብሮች የሚያስፈሩም አራዊት ሁሉ ወደርሱ በመምጣት ይሰግዱለታል፤ የእግሮቹን ትቢያ ይልሱ ነበር። በአንዲት ዕለት በጎዳና ሲጓዝ ታላቅ ወንዝ ውኃው መልቶ አገኘ። መጽሐፍና እሳትም ከእርሱ ጋር ነበር፤ ጸሎትም አድርጎ ወደ ውኃው ገባ። ውኃውም ዋጠውና ወደታች አወረደው በእግዚአብሔርም ኃይል ወደማዶ በጣለው ጊዜ መጽሐፉ ሳይደመሰስ እሳቱም ሳይጠፋ አገኘው።

ሰይጣንም በሚያስፈሩ አራዊት እየተመሰለ ይፈታተነው ነበር። እርሱ ግን ፈጣሪውን በመታመን ልቡ የታሠረና የጸና ስለሆነ አይፈራም። እርሱም ሲጸልይ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ። በምራቁም መላ ሕዋሳቱን ቀብቶ ኃይልን አሳደረበት፤ ከዚያችም ዕለት ጀምሮ እግሮቹን የሚያሥር ሆነ። ማቅንም ለብሶ በየሌሊቱ ሁሉ ከውኃ ውስጥ በመግባት የዳዊትን መዝሙር አምስት ጊዜ ያደርሳል። ቊጥር በሌለውም ግርፋት ጀርባውን ይገርፍ ነበር።አንበሶችም በበዓቱ አጠገቡ ይሰማራሉ፤ እርሱም አካላቸውን ይሰፍራል፣ ይለካል፣ ቊስላቸውንም በጥቶ እሾህና አሜከላ ያወጣላቸዋል። ከዚህም በኋላ ብዙ ደቀ መዛሙርት ወደርሱ ተሰበሰቡ፥ በተጋድሎም ተጠመዱ። ከእነርሱም የመጀመሪያው አባ ዘሩፋኤል ነው። በአንዲትም ዕለት በገዳመ ለጋስ የሚኖር ከአባ ገብረ መስቀል ጋር ተገናኘ። ከዚህም በፊት አልተያዩም ነበ፤ የእግዚአብሔርንም ገናናነት ሲጨዋወቱ ዋሉ። በራት ጊዜም ጸሎትን ሲያደርጉ የተዘጋጀ ማእድ ወርዶላቸው ተመግበው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ዕለት ከአንድ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ። እግዚአብሔርም ያደረገላቸውን ምሥጢር በሚነጋገሩ ጊዜ አባታችን አባ ሳሙኤል እንዲህ አለ “እነሆ እኔ በአርያም ቁሜ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የአምላክን መንበር ሳጥን ዐሥራ ሁለት ዓመት ሆነኝ።” ለመቀደስም በሚገባ ጊዜ ኅብስትና ወይንን የተመላ ጽዋ ይወርድለታል። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ውዳሴዋን ሲያነብ ክንድ ያህል ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከፍ ይላል። እመቤታችን ማርያምም ወደ እርሱ መጥታ የሚያበራ ዕንቊንና ንጹሕ ዕጣንን ሰጠችው።ፍልሰቱም ሲቀርብ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በክንፎቹ ተሸክሞ አወጣው። ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን ተድላዋን ሁሉ አሳየው፤ ወደ ልዑል እግዚአብሔርም ዙፋን ፊት አቅርቦት ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ተቀበለ። ወደ በዓቱም ሲመለስ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ከዚህም በኋላ ታኅሣሥ ፲፪ ቀን በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን! እኛንም በአባ ሳሙኤል ጸሎት ይማረን! በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር! ለዘለዓሙ አሜን።

ምንጭ፦ የታኅሣሥ ፲፪ ስንክሳር

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት፡

ኢያቄምና ሐና ቃል ኪዳናቸውን ለመፈጸም ዘመዶቻቸውን ባልንጀሮቻቸውን ከነልጆቻቸው በመጥራት፣ ሕፃን ልጃቸውን እመቤታችንን ልዩና ንጹሕ ልብስን አልብሰው በመንፈሳዊ ዝማሬ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ መብራትን በእጆቻቸው ይዘው እያበሩ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ወሰዷት። ያን ጊዜም ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ በካህናቱ ታጅቦ የምስጋና ዝማሬን ከልኡካኑ ጋር እያሰማ እነርሱን ለመገናኘት ከመቅደስ ወጣ።በዚያም ሊቀ ካህናቱ ብቻ ወደሚገባበት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚያስወጡ ፲፭ ደረጃዎች ሲኖሩ በየደረጃዎቹም መዝሙረ ዳዊት ተደጋግሞ ሲደረስባቸው ከሚጸለዩት የዳዊት መዝሙራት መካከል መዝ ፻፲፰(፻፲፱)፣ ፻፴፪ (፻፴፫) የሚገኙ ሲኾኑ እነዚኽንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አጥኚዎች “Psalms of Ascent” (የመውጣት መዝሙራት) ይሏቸዋል::

እናትና አባቷም ሊቀ ካህናቱን ካለበት ቅዱስ ቦታ ወደነርሱ እስኪመጣ ለመቆየት ልጃቸው ማርያምን ከአንደኛው ደረጃ ላይ ቢያኖሯትም እርሷ ግን በድንቅ አምላካዊ ሥራ መንፈሳዊ ኀይልን ተመልታ የሦስት ዓመቷ እመቤታችን ያለምንም ረዳት ብቻዋን ደረጃዎቹን በመውጣት በእጅጉን ወደተቀደሰው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ወዳለበት ስፍራ ኼደች ርሱም በእጅጉ ተደንቆ ባረካት።

ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለሊቀ ካህናቱ የሰው ዘርን በመላ ወደ ገነት የሚያስገባ፣ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የእግዚአብሔር ልጅን የምትወልደው እርሷ እንደኾነች ገለጸለት። ቦታዋም በጣም የተቀደሰውና እርሱ መሥዋዕት ለማቅረብ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገባበ፣ ከእርሱ በቀር ማንም ሰው የማይገባበት፣ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ መኾኑን ገልጾለታል ፡፡ እርሱም ይኽንን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራን በማድነቅ፣ ይኽቺን የመሰለች ልጅ ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምንስ እናጠጣታለን? ምን እናነጥፍላታለን? ብሎ ሲጨነቅ ለእስራኤል ደመና ጋርዶ መናን አውርዶ የመገበ፣ ለኤልያስም በመልአኩ እጅ በመሶበ ወርቅ ኅብስት የመገበ፣ ለእዝራ ሱቱኤልም በመልአኩ በቅዱስ ዑራኤል እጅ መልኩ እሳት የሚመስል ጽዋዐ ልቡና ያጠጣው ልዑል እግዚአብሔር ለእናትነት ወደ መረጣት ወደ እናቱ መልአኩ ፋኑኤልን ላከላት። (ዘፀ ፲፮፥፴፩፣ ፩ ነገ ፲፱፥፮፣ ዕዝ. ሱቱ. ፲፫፥፴፰-፵፩)

ከዚያም “ወሶቤሃ ወረደ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት ወጸለላ በአክናፊሁ ወተለዐለ ላዕለ መጠነ ቆመ ብእሲ ወወሀባ ወመጠዋ ወዐርገ ውስተ ሰማይ” ይላል።”  /  “በዚያን ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊን በብርሃን ጽዋዕ፣ ስቴ ሕይወትን ይዞ ረብቦ በመውረድ አንድ ክንፉን አንጥፎ፣ አንዱን ክንፉን አጎናጽፎ፣ ከመሬት የሰው ቁመት ያኽል ከፍ አድርጓት፣ ኅብስቱን መግቧት፣ ጽዋውን አጠጥቷት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ስላዩትና ስለተደረገው ነገር ኹሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አማናዊት የአምላክ መቅደስ፣ የአካላዊ ቃል ታቦት እመቤታችንን ምሳሌዋ ወደሚኾነው ቤተ መቅደስ ታኅሣሥ ፫ በሦስት ዓመቷ አስገብተዋታል። ከዚያም ኢያቄምና ሐና ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡የቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ መቅደስ ሕይወት በእጅጉ አስደናቂ ሲኾን የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ትውፊት (Holy Tradition) እንደሚያስረዳን ቤተ መቅደስ በኖረችባቸው ፲፪ ዓመታት የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለቤተ መቅደስ የሚያስፈልገውን ነገር በእጆቿ እየሠራች በፍጹም ንጽሕና እና ቅድስና ኾና እግዚአብሔርን በማመስገን መላእክት እያገለገሏት ኖራለች፡፡ ይኽነን በቤተ መቅደስ የነበራትን ቆይታ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በጥልቀት ጽፈዋል። እነሆ የሊቃውንቱ ቃል፦አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማኅሌተ ጽጌ
“ማርያም የሐናን ወተት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ብቸኝነት ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚመላለስ ደመናን የሚረግጥ የእሳት አበባ ፋኑኤል ከጓደኞቹ መላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በንጽሕና የማደግሽ ተአምር ደስ ያሰኘኛል።”

“በዐረብና በተርሴስ ወርቅ እንዳጌጠች ታቦት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ያጌጥሽ ማርያም ቀንሞስ፣ ቀናንሞስ የሚባሉ ሽቱዎች ኢያቄምና ሐና ለጳጦስ ምሳሌ የኾንሽ አንቺን ከአስገኙሽ ዘንድ በሦስት ዓመት በቤተ መቅደስ የመኖር ተአምርን አሳየሽ።”
      ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ። ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ። ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ። ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች መተዳደፍን የምታውቂ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ። ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም፤ የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፤ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ።”
         በ፭፻፭ (505) ዓ.ም. የተወለደው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን: “ከንጹሓን ይልቅ ንጽሕት የኾንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ ዕንጨት እንደተሠራ፣ በወርቅ እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በኾነ በሚያበራ ዕንቊ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ። እንዲኽ ኾነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤ መላእክት እየጐበኙሽ እንዲኽ ዐሥራ ኹለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፤ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር።” “መላእክት እመቤታችንን እኅታችን ይሏታል። በክንፋቸው ይጋርዷታል፤ በማር ወለላ የተመሰለ የእግዚአብሔር ቃል ከከንፈሮቿ ይፈስሳል፤ ጒንጮቿ እንደ ሮማን ቅርፍት ናቸው። ልዑል ወደዳት፣ ዳዊት በመዝሙሩ አመሰገናት፣ በቤተ መቅደስ ተቀበሏት።” ቅዱስ ያሬድ (መጽሐፈ ድጓ) ጌታ የመረጠሽ ማርያም ሆይ ለምኚልን። ዕፀ ጳጦስ ተብላ የተጠራችውን እመቤታችን ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ተቀበላት። ኹላቸውም ቅዱሳን ዐዲሲቱ እንቦሳ ይሏታል።በዓሉን የረድኤት የበረከት ያድርግልን!

፩. ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣
፪. ነገረ ማርያም በሊቃውንት ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ። ኢንኅድግ ማኅበረነ እግዚአብሔር ምስሌነ!

ገሪማ ገረምከኒ


የሮም ንጉሠ ነገሥት ከነበሩት ወላጆቹ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም አማላጅነት ተወልዶ ይስሐቅ የተባለው ፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ተምሮም ዲቁናን የተሾመውና በአባቱም ዙፋን ላይ በንግሥና በቅንነት እየገዛ ሰባት ዓመት የኖረው ቅዱስ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወጥቶ ወደ ምንኩስና የሄደው በዋሻ በሚኖረው አባ ጰንጠሌዎን መልእክት ነበር። የሚገርመው በመንገዱ ላይ ጌታችን የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጦለት ብርሃናውያን በሆኑ ክንፎቹም ተሸክሞ የዐሥር ወር የሚሆነውን መንገድ በሦስት ሰዓት አስፈጽሞ በአባ ጰንጠሌዎንም ደጅ አቁሞታል።አባ ጰንጠሌዎንም ቅዱስ ይስሐቅን ተቀብሎ በበዓቱም አስገብቶ የምንኲስና ልብስን ካለበሰው በኋላ፡ ይስሐቅ በጾም በጸሎትና በስግደት ተጠምዶ ቆዳው ከዐፅሙ እስከሚጣበቅ ተጋድሏል።


ወደ መደራ ሄዶም በእግዚአብሔር ኃይል ድንቅና ተአምር እያደረገ በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማስወጣት ብዙ ዘመን ኖሯል። በአንዲት ዕለትም በጥዋት ሥንዴ ዘራ በሠርክም መሥዋትን አሳረገ። በማግሥቱም በግራር ዛፍ ላይ በሮችን አውጥቶ የሥንዴውን ነዶ አበራ የሰባ ሰባት የእንቅብ መስፈሪያም ሆነ። ሁለተኛም የወይን ሀረግ በአለት ላይ ተከለ ወዲያውም በቀለች አበበችና አፈራች በእርሷም መሥዋዕትን አሳረገ። አንዲት ቀንም ሲጽፍ መሸና ፀሐይ ሊጠልቅ በተቃረበ ጊዜ በቦታውም እንዲቆም በማዘዝ ጽሕፈቱንም እስኪጨርስ አቆመው። ምራቁንም ትፍ ባለበት ዘንድ ጠበል ፈልቆ እስከ ዛሬ ለበሽተኞች ፈውስ ሆኖ ይኖራል።
ታዲያ በአንዲት ዕለት ሰዎች ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው “ቀሲስ ይስሐቅ እኮ ከበላ በኋላ የቁርባን ቅዳሴ ቀደሰ” ብለው ነገሩት አባ ጰንጠሌዎንም ወደርሱ ሄዶ “ልጄ ይስሐቅ ሆይ ምሥጢር ስለ አለኝ ከአጠገባችን ሰዎችን አስገልል” አለው ይስሐቅም “ሰዎችን ተውና ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ይገለሉ” አለ። ወዲያውኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ሸሹ። አባ ጰንጠሌዎንም “ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ” አለ ስለዚህም ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ገሪማ ተባለ።


መልካም ተጋድሎንና የቀና አካሔዱን በፈፀመ ጊዜ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት “ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያው ለሚያደርግ፣ ገድሉንም ለሚጽፍና ለሚያጽፍ፣ ለሚያነበውና ለሚተረጉመው ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ዳግመኛም “የተራበውን ላበላ፣ የተጠማውንም ላጠጣ እኔ የሕይወት እንጀራን እመግበዋለሁ የድኅነት ጽዋንም አጠጣዋለሁ” አለው። በቤተ ክርስቲያንህም በማኅሌት ያመሰገነውንና የጸለየውን እኔ የመላእክትን ምስጋና አሰማዋለሁ የተራቆተውንም ለሚያለብስ የብልህ እጅ ያልሠራው የብርሃን ግምጃን አለብሰዋለሁ ነፍሱም ከሥጋው በምትለይ ጊዜ የጨለማ መላእክት አይቀርቡትም። የብርሃን መላእክትም በዙሪያው አቆማቸዋለሁ። በስምህም ቤተ ክርስቲያን ለሠራ በሰማያት አርባ ሰባት የብርሃን ቦታዎችን እኔ እሰጠዋለሁ፣ ለቤተ ክርስቲያንህ መባ የሚሰጠውንም እኔ በመንግሥቴ እቀበለዋለሁ፣ ቦታህን የሚያከብረውንም እኔ በመንግሥቴ አከብረዋለሁ፣ ጠላቶች አጋንንትን ረግጦ የሚገዛበትንም እሰጠዋለሁ”። ብሎ ቃልኪዳን ገብቶለታል።
አባ ገሪማም “ይህን ታላቅ ሀብት በቸርነትህ ብዛት የሰጠኸኝ አቤቱ ስምህ ይክበር ይመስገን ግን ጌታዬ ሆይ መታሰቢያዬን ላደረገ፣ ገድሌንም ለጻፈ እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ” አለ። መድኃኒታችንም “እስከ ዐሥራ ሁለት ትውልድ እምርረዋለሁ” ብሎታል። አባ ገሪማም መድኃኒታችንን “ልጆች ባይኖሩትስ ምን ታደርግለታለህ” ባለው ጊዜ መድኃኒታችንም “ዐሥራ ሁለት ዕጽፍ ክብር እሰጠዋለሁ” ብሎ መልሶለታል።
ዳግመኛም “የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለሁ” አለውና ሰላምታ ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ቅዱስ አባ ገሪማም በልቡ ደስ ተሰኝቶ ሰኔ 17 ቀንም በብርሃን ሠረገላ ተነጥቆ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል።


ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም አባ ገሪማ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

ማንም ሲመግብህ አላየሁም አባ ኑፊር ( Abba Nufeir the Anchorite)

አንድ የስድስት ዓመት ልጅ በገዳም ከመነኮሳት ጋር እየኖረ ሳለ እንደ ልጅነቱ ቶሎ ቶሎ መመገብ ያስፈልገው ስለነበር ወደ ምግብ አብሳዩ እየሄደ ዳቦ፣ ዘይት እና ፍራፍሬ ይጠይቃል። ምግብ አብሳዩም ሁልጊዜ የሚጠይቀውን እየሰጠው ይዞ ይሄድ ነበር።
ታድያ አንድ ቀን የገዳሙ ምግብ አብሳይ ይሄ ልጅ ዳቦውን እየያዘ ወዴት ነው የሚሄደው ? ምን አልባት ዶሮ እየመገበበት ይሆን? በማለት ተገርሞ ሊመለከት ሕጻኑን ተከትሎት ሄደ ። ሕፃኑ ኑፊርም የተሰጠውን ዳቦ ይዞ ወደ ገዳሙ ቤተክርስቲያን በመግባት በሩን ሲዘጋው ምግብ አብሳዩም በመስኮት በኩል የሚሆነውን ይከታተል ጀመር። ሕፃኑም የተሰጠውን ዳቦ ወስዶ ጌታችን በእመቤታችን እቅፍ ሆኖ ወደ አለው ሥዕል ተጠግቶ ” እስካሁን ማንም ሲምግብህ አላየሁም ፤ ክርስቶስ ሆይ እኔ ግን ዛሬ ዳቦ አምጥቼልሀለሁ” ብሎ የያዘውን ዳቦ ወደ ሥዕሉ ሲዘረጋው ጌታችን ከሥዕሉ እጁን ዘርግቶ ዳቦውን ሲቀበለው ምግብ አብሳዩ ተመለከተ።
ምግብ አብሳዩ ባየው ነገር እጅግ ተደንቆና ተገርሞ ወደ አበ ምኔቱ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው። አበምኔቱም “ነገ መጥቶ ዳቦ ስጠኝ ብሎ ቢለምንህ እንዳትሰጠው ይልቁንም እስከ ትላንት ድርስ ስትመግበው የነበረው ልጅ ይስጥህ” በለው ብለው ያሰናብቱታል።ሕጻኑ ኑፊርም እንደለመደው በቀጣዩ ቀን ዳቦ ፍለጋ ወደ ምግብ አብሳዩ ሲሄድ አብሳዩም አበምኔቱ የነገሩትን ነገሮ ያሰናብተዋል ሕፃኑ ኑፊርም ወደ ገዳሙ ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለው በሥዕለ አድህኖ ፊት ቆሞ ጌታችንን ” ክርስቶስ ዛሬ ዳቦ አላመጣሁልህም እንደውም እሱ ይስጥህ አሉኝ አንተ ግን ዳቦ ከየት ታመጣለህ ?” አለው ጌታችንም ከሥዕሉ እጁን ዘርግቶ እጅግ ግዙፍ የሆነና በጥዑም መአዛው ገዳሙን የሚያውድ ሰማያዊ ዳቦ ሰጠው።
ሕጻኑም ዳቦውን መሸከም ስላልተቻለው በዳቦው ጥዑም መዓዛ ከተሰበሰቡት መነኮሳት ሁሉቱ ቀርበው ያግዙት ጀምር። ይህ ድንቅ ተአምርም በገዳሙ እና በአካባቢው ሰው ሁሉ ተሰማ። የገዳሙም መነኮሳት ከዳቦው በልተው ጠገቡ። በሚበሉም ጊዜ ዳቦውም አይጎድልም ነበር። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የገዳሙ መነኮሳት ለሕፃኑ ትልቅ ክብር እና ተስፋ ኖራቸው። እያደገ ሲሄድ ቅድስናው እንደሚጨምር በማወቅ በፍቅር እና በተስፋ ይጠብቁት ነበር።
ይህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥዕለ አድህኖው በኩል ያናገረው ቅዱስ ሰው አባ ኑፊር ይባላል።ከሕጻንነታቸው ጀምሮ በግብፅ ሄርሞፖሊስ በምትባል ከተማ ውስጥ በምትገኝ ገዳም ከመነኮሳት ጋር ያደጉ ነበር።ገዳም ውስጥ ባደጉበት ጊዜ ቃለ እግዚአብሔር እና የምንኩስና ሕይወትን በሚገባ ተምረው አድገዋል። እድሜያቸው ከፍ ሲል የምነናን ሕይወት ልባቸው ስላሻተ የገዳሙን አበምኔት አስፈቅደው ወደ በረሀ ገብተው ለ60 ዓመታት ያህል የሰው ፊት ሳያዩ ከእግዚአብሔር ጋር በብሕትውና ኖረዋል።በበረሀ በሚኖሩበት ጊዜ ጢማቸው ሰውነታቸውን በመሸፈን እንደ ልብስ ሆኖ ያገለግላቸው ነበር። እረፍታቸው ሲቃረብ ልዑል እግዚአብሔር አባ በፍኖትዮስ የተባሉ አባትን ወደ አባ ኑፊር ላከ። አባ በፍኖትዮስም ከአባ ኑፊር ቅዱስ የሆነውን ተጋድሏቸውን ከሰሙ በኋላ ታሪካቸውን ጽፈው ለእኛ አስቀምጠውልናል።
አባ ኑፊር የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ በአባ በፍኖትዮስ እጅ በዛው በተጋደሉበት በረሀ ውስጥ ተቀብረዋል።
ከረድኤታቸው ያሳትፈን።
Father Stefanos Anagnostopoulos
Excerpt from [ “Explaining the Divine Liturgy” Byzantine Publishing House, 2005, pp. 251-252]

ባለሽቱዋ ማርያም- ማርያም እንተ ዕፍረት

የሕማማት ዕለተ ረቡዕ ከምክረ አይሁድ ባሻገር የእንባና የሽቱ ቀን ተብሎ ይጠራል። በዚህች ቀን ማርያም እንተ ዕፍረት የጌታችንን እግሮች በእንባዋ ማጠቧንና ሽቱ መቀባቷን እናስባለን።

ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው የመንግሥቱ ወንጌል በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ስሟ ስለሚታሰበው ቅድስት፡ ስለቀባችው ሽቱና ስለቀባችበት ሁኔታ እናንብብ።


ይህች ቅድስት ቀድሞ በዝሙት የኖረችበትን አስከፊ ሕይወት በመተው በቆራጥ ኅሊና ፍጹም ንስሓ ገብታ ገንዘቧን ሁሉ አውጥታ እጅግ ውድ የሆነውን ሽቱ ገዝታ ጌታችንን ስትቀባው ጌታችንም በፍጹም ንስሓዋ ተደስቶ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል›› በማለት አስደናቂ ትእዛዙን የሰጠላት ቅድስት ናት፡፡ ማቴ 26፡6፡፡ ይህንን የጌታችንን ትእዛዝ ልብ ብለን ካየነው በውስጡ ብዙ ምሥጢራትን የያዘ ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ስለ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው ራሱ መድኀኔዓለም ክርስቶስ መሆኑን በዚሁ ልብ ይሉታል፡፡


ማርያም እንተ ዕፍረት የቀድሞውን ሕይወቷን ስናየው ሁልጊዜ ከነጭ ሐር የተሠራ ልብስ የምትለብስ፣ ከሽቱ ሁሉ ይልቅ የሚበልጥ ውድ ሽቱን ትቀባ ነበር፡፡ በወርቅም ታጌጥና በክፉ ሥራ ሁሉ ጸንታ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የዚህን ዓለም ጣዕም አጣፈጠላት፡፡ ነገር ግን ስለዚህች ሴትና ስለ ኃጥአን ሁሉ ጌታችን ከጌትነቱ ከፍታ ሳይለወጥ ከልዑል ዙፋኑ ወረደ፡፡ በሰዎች መካከልም ከእነርሱ እንደ አንዱ እየተመላለሰ አስተማረ፡፡


አንድ ቀን እንደልማዷ ማርያም እንተ ዕፍረት ነጭ ሐር ለብሳ፣ አጊጣና ተኳኩላ ፊቷን በመስታወት አይታ ውድ ሽቱ ተቀባች፡፡ ጉንጮቿ ቀያዮች፣ ዐይኖቿ የተዋቡ ሆነው ደም ግባቷ በጣም አማራት፡፡ እንደዚህ እየተመለከተች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች፡፡ ከዚህ በኋላ መልካም አሳብ በእርሷ ላይ አድሮ እንዲህ አለች፡- ‹‹ይህን ሁሉ ታስወግድ ዘንድ መልኬንም ትለውጥ ዘንድ ሞት ትመጣ የለምን? ይህ መልካም ሽታ ወደ ትልነትና ወደ መሽተት ይለወጣል፡፡ ይህስ ብርታት ፍጻሜው ጉስቁልናና ድካም አይለምን? ሊቀርቡኝ የሚወዱትስ የሚርቁኝ አይደሉምን? እንደዚህስ ከሆነ ዘለዓለም ከጥፋትና ከኩነኔ በቀር እንግዲህ ምን አገኛለሁ? የዚህን ዓለም ገንዘብ ብገዛ፣ ብነዳ ከድካም በዐይኖቼም ዕንባን ከማፍሰስ የሚያድነኝ ይኖራልን? ወይስ ይህ ሁሉ ከሞት ያድነኝ ዘንድ ይችላልን? ነፍሴ ሆይ! እንግዲህ ሁሉን ለሚገዛ ጌታ ምን ትመልሻለሽ? ከእውነተኛው ፈራጅ ዘንድ በአንቺ ላይ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! ንስሐ በሌለበት፣ ነፍስ የተናቀች በምትሆንበት ጩኸት፣ ልቅሶና ጩኸት ባለበት ቦታ የሚረዳሽ ማነው? ነጭ ሐርና ኅብሩ ልዩ ልዩ የሆነ ልብስ በመልበስ ደስ የምትሰኝ ሥጋዬ ሆይ በክብር ባለቤት በእግዚአብሔርና በመላእክቱ ፊት ራቁትሽን በቆምሽ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! በዚህ ዓለም የተደሰችው ምን ይጠቅምሻል?…›› እያለች ራሷን መመርመር ጀመረች፡፡


ከዚህ በኋላ በማመን ጸንታ እንዲህ ብላ አሰበች፡- ‹‹ስለ ኃጥአን ወደዚህ ዓለም የመጣ ስለ እነርሱ በመካከላቸው እንደሰው የተመላለሰ ይህ አይደለምን? የኃጢአተኛን መመለሱን ነው እንጂ ሞቱን አልሻም ያለውስ እርሱ አይደለምን? ነፍሴ ሆይ ምሕረትስ ቅርብ ናት፣ ባለመድኃኒትም የራቀ አይደለም፣ ሌላ መድኃኒትሽን ተስፋ የምታደርጊበትስ አለን? መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዲቱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልጋት የሚሄድ አይደለምን? ባገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከማታል፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሷ ደስ የሚሰኝ አይደለምን? እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ የሚል እርሱ መድኃኒት ክርስቶስ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ለምን እሰንፋለሁ? ለምንስ ንስሓ አልሻም? እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ወደ እርሱ ሄጄ ራሴን በፊቱ እክዳለሁ›› ብላ ካሰበች በኋላ ተጽናናችና በፍጥነት ተነስታ ገንዘቧን፣ የገዛችውን ወርቋንና ብሯን ሁሉ ሰበሰበች፡፡

‹‹ምን አደርጋለሁ ይህን ገንዘብ ወስጄ ብሰጠው አይቀበልም እርሱ ፈጣሪ፣ ጌታና የዓለም መድኃኒት ነውና›› ብላ አሰበች፡፡


ከዚህ በኋላ ሽቱ ወደሚሸጥ ሰው ፍለጋ ሄደች፣ ያን ሰው ከጥንት ጀምሮ ታውቀው ነበርና ከእርሱ ዘንድ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቱን ገዛችና በደስታ ስትሄድ እነሆ ሰይጣን በወርቅ ያጌጠች ሴት መስሎ ወደ እርሷ መጣ፡፡ የዚህን ዓለም ምኞት እያጣፈጠ ይነግራት ጀመር፡፡ መብላትን፣ መጠጣትን፣ ያማረ ልብስ መልበስን፣ ሽቱ መቀባትን… ይህን ሁሉ ያሳስባት ጀመር፡፡ ጌታችንም በይቅርታው ብዛት የጠላት ዲያብሎስን ክፋት ገለጠላትና ‹‹ለበደልና ለኃጢአት ሥራ የተዘጋጀሁ አድርገኸኛልና ኃፍረትና ጉስቁልናንም በእኔ ላይ አምጥተሃልና አንተ ሰይጣን ከእኔ ወግድ›› ብላ በቁርጥ ነገር መለሰችለት፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የሃይማኖቷን ጽናት ባየ ጊዜ ከእርሷ ሽሽቶ ፈሪሳዊ ወደሚሆን ስምዖን ወደሚባል ሰው ዘንድ ሄዶ ልቡናውን ያውከው ጀመር፡፡ እርሱም ጌታን በቤቱ ማዕድ ይመገብ ዘንድ ጋብዞት ነበርና፡፡በልቡናው ያደረው ክፉ ሰይጣንም እንዲህ እንዲል አደረገው፡- ‹‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ኃጢአተኛ እንደነበረች አያውቅም ነበር? ብሎ እንዲያስብ አድረገው፡፡››


“ከንቱ ነገርን ስትመለከቱ የኖራችሁ ዐይኖቼ ሆይ! ጌታን ታዩ ዘንድ ተሰጣችሁ፤ ርኩስን የምትዳስሱ እጆቼ ሆይ! የሰማያዊ ጌታን እግር ትዳስሱ ዘንድ ሰጣችሁ፤ ኃጢአተኛ ነፍሴ ሆይ! እነሆ ፈጽሞ ከፍ ያለ ባለሟልነትን አገኘሽ፤ ስላደረገልኝ ምን እከፍለዋለሁ› እያለች ታላቅ ልቅሶን አለቀሰች፡፡ የጌታንም እግር ይዛ በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ ታብስ ጀመር፡፡ አስቀድማ በልቧ እንዲህ ብላ አስባለችና ‹በጌታ ፊት ባለሟልነትንስ ካገኘሁ ወደ እርሱ ዘንድ እንድቀርብ ያደርገኛል፡፡ በሥራዬም ክፋት ካበረረኝ ግን ዳግመኛ አልድንም› ብላ አስባ ነበር፡፡ ከጌታም ባለሟልነትን ባገኘች ጊዜ ጨክና በራሱ ላይ ሽቱውን ጨመረች፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋርም ልቅሶንና ልመናን አላቋረጠችም፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ በእርሷ ላይ እንደበዛ ባየ ጊዜ ጠላት ዲያብሎስ በእርሷ ላይ ታላቅ መቅናትን ቀናባት፡፡ ተቆጥቶም ወደ ስምዖን ተመልሶ ልቡን አወከው፡፡ ‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ኃጢአተኛ እንደሆነች ያውቅ ነበር› እንዲል አደረገው፡፡

  ጌታችንም ስምዖንን ሁሉ ከእርሱ እንዳልተደበቀና ሀሳቡንም እንዳወቀበት እንዲረዳና እግዚአብሔርም በደለኞችን ማዳንና ከኃጢአታቸው ማንጻት እንደሚችል ያውቅ ዘንድ እንዲያስተውል አደረገው፡፡›› ሉቃ 7፡36-50፡፡

ይህ እጅግ ውድ ዋጋ ያለው የማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መነሻ መገኛው ራሱ ጌታችን ነው፡፡ ይኸውም ነገሩ እንዲህ ነው፡- ‹‹ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን አረጋዊ ዮሴፍ ሕፃኑንና እመቤታችንን ይዞ ወደ ምድረ ግብፅ ሲሄዱ በመንገድ ላይ አንድ ፈረሰኛ ሰው አገኛቸውና ከእነርሱም ጋር ይሄድ ጀመር፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በመንገድ እንደደከመች ባየ ጊዜ ሕፃኑን አንሥቶ ፈረሱ ላይ አውጥቶ በጭኑ ታቀፈው፡፡ ያንጊዜም በፈረሱ ላይ የመልካም ሽቱ መዓዛ ይሸት ነበር፡፡ ወዙም ሲንጠፈጠፍ ባየው ጊዜ መልካም ሽታም እንዳለው ባየ ጊዜ ሻሹን ከራሱ ላይ አውልቆ የሕፃኑን ወዝ ጠረገለትና ቆይቶ ሕፃኑን ለእናቱ ሰጥቷት በጐዳናው ሄደ፡፡ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ልብሱን ታጥበው ዘንድ ለእናቱ ሰጣት፣ እርሷም በሻሹ ላይ ያለውን መልካም ሽታ ካየች በኋላ በማጠቢያ ባስቀመጠችው ጊዜ ከሻሹ ውስጥ ሽታው እጅግ የሚያስደስት መልካም ዘይት ወጣ፡፡

እርሷም ደስ ተሰኝታ ከቅባቷ ጋር በማሰሮ አድርጋ አስቀመጠችው፡፡ ያም ዘይት ባለበት በዚያች መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ የሽቶውን መዓዛ ያደንቁ ነበርና ስለዚህ ያች ሴት ከአገረ ገዥው ጋር እንዳያካስሷት ፈርታ በብዙ ገንዘብ ሽቱ ከሚገዙ ነጋዴዎች ለአንዱ ሸጠችለት፣ እርሱ ግን ምን እንደሆነ አያውቅም ነበር፡፡ ያም ዘይት ብፅዕት ማርያም እንተ ዕፍረት እስክትመጣ ድረስ ለብዙ ዘመን በእርሱ ዘንድ በዚያ ኖረ፡፡ ማርያም እንተ ዕፍረትም ከእርሱ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ ገዝታ በጌታችን ሥጋ ላይ አፈሰሰችው፡፡ እነሆም ይህ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነው ሽቱ ከጌታችን ዘንድ እንደተገኘ የታወቀ ሆነ፡፡ ያም በፈረስ ላይ ተቀምጦ ጌታችንን በሕፃንንቱ በጭኑ አቅፎ የያዘው ፈረሰኛ ሰው ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ያመነበት ፊያታዊ ዘየማን (ጥጦስ) ነው፡፡››


ማርያም እንተ ዕፍረት ጌታችን ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ ዐርፋለች፡፡ የንግሥ በዓላቶቿ መጋቢት 21 ቀን የጌታችንን እግር ሽቱ የቀባችበት ሲሆን የካቲት 6 ቀን ደግሞ ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ጥቅምት 1 ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሏ እንዲሆን አባቶቻችን ሕግ ሠሩልን፡፡ የማርያም እንተ እፍረትን ገድሏንና ድርሳኗን የጻፈላት ታላቁ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡
የቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረትን ረድኤት በረከቷን ያሳድርብን፣ በጸሎቷም ይማረን።

( ገድለ ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት፣ የጥቅምትና የካቲት ስንክሳር)

ቅዱስ ጊዮርጊስና የአድዋ ድል

‹‹ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ። በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም።… በአፍሪካ በኩል ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሣቱ ታወቀ። የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ። ጥቁሩ ዓለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምጽና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ሐበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል። የኛ ዓለም ገና ቶርና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ ሐበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው። አሁን የኹሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው…››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ ገጽ ፻፶፱)። ይህንን የተናገረው ቤርክሊይ የተባለ ጸሐፊ ነው። (Berkeley, George; The Campaign of Adowa and the Rise of Menilik)።

ከአድዋ ጦርነት በኋላ ይህና እንዲህ ዓይነቱ የአድናቆት ምስክርነት ከዓለም ዙሪያ ለኢትዮጵያውያን መበርከቱን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። የአድዋ ድል የዓለም ፖለቲካዊ አካሔድ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበረው። እንዲያውም የዚያን ዘመኑን የቅኝ ግዛት ዘመን ከአድዋ በፊትና ከአድዋ በኋላ ብሎ መክፈልና ማጥናት ይቻላል። በዓለም ላይ ከታዩ እጅግ አስገራሚና ወሳኝ ክስተቶች እንደ አንዱም መመደብ የሚችል ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በጊዜው አሉ የተባሉትን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀችና ከጊዜው ኃያላን አንዷ የሆነች አንዲት አውሮፓዊት ሥልጡን ሀገር፣ እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣኔ በሌላትና እንደ አውሮፓውያኑ የምታመርተው ቀርቶ የምትገዛውና በእርዳታ የምታገኘው የጦር መሣሪያ እንኳን በቁጥር ውሱንና እጅግ ኋላ ቀር በሆነ፣ ዘመናዊ የጦርነት ስልትን እንደ ሌሎቹ ያልተራቀቀችበት፣ ጦርና ጋሻን በያዙ ዜጎቿ የምትዋጋ እንጂ የወታደሮቿ ቍጥር ጥቂት በሆነባት፣ በአንዲት አፍሪካዊት ሀገር መሸነፏ ነበር። ጦርነቱ በሁለት አውሮፓውያን ወይም በሁለት አፍሪካውያን ሀገራት መካከል የተደረገ ቢሆን ኖሮ፡ ጥቂትም ቢሆን የኃይል መመጣጠን ስለሚኖር ይህን ያክል አያስደንቅም ነበር። ነገር ግን በጉልበተኞች ጽንፍ ባለች በአንዲት ሀገርና በምስኪኖች ጽንፍ ባለች በሌላ ሀገር ምክንያት የተደረገ በመሆኑና ውጤቱም ሥጋ ለባሽ ከሚጠብቀው አመክንዮአዊ ውጤት እጅግ የተለየ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል።

ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞ ጳውሎስ ኞኞና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንደ ገለጹት ‹‹ሁሉም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን እንደምታሸንፋት›› ያስቡ የነበረው ይህን አለመመጣጠን በሰውኛ መነጽር በማየት ነበር። ታዲያ ድሉ እንዴት ተገኘ? የድሉ ዋና መሠረት የሥነ ልቡናና አስተሳሰብ ሚዛን ነበር። የኢጣሊያ ወታደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎቻቸውና በውጊያ አቅማቸው ክፉኛ ተማምነውና መተማመናቸውም ወደ ትዕቢት ከፍ ብሎ ነበር። ‹‹…በቅርብ ቀን ምኒልክን በቀፎ ውስጥ አሥሬ ሮማ ውስጥ አመጣዋለሁ…›› ይል የነበረው የኢጣሊያ የጦር መሪ፡ የጄኔራል ባራቲዬሪ ንግግርም ይህንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ሕዝቡም ገና ጦርነቱ ሳይጀመር ‹‹ድል አድራጊው›› እያሉ እርሱን መጥራታቸው የዚህ ሌላው ማሳያ ነበር። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፷፫)።

በኢትዮጵያውያን በኩል ምንም እንኳን የኢጣሊያ ዐቅም እጅግ እንደሚልቅ ቢረዱትም፡ ከንጉሡ አዋጅ ጀምሮ ካላቸው የጦር ቁስ ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ መተማመናቸው ጎልቶ ይታይ ነበር፡- ‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። ‹‹አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቶአል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው፤ ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ ለሚሽትህ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ።›› (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፶፮-፻፶፱)። በዚህ አዋጅ ላይ ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ የሚያኖረው እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ ርትዕንና ፍትሕን እስከ ያዙ ድረስ በእግዚአብሔር እርዳታ አለመጠራጠር፣ ጠላትን በጠላትነት የመፈረጁ ነገር የመጣው ሀገር የሚያጠፋና ሃይማኖት የሚለውጥ በመሆኑ እንደ ሆነ፣ በእግዚአብሔር ረዳትነት እንደሚዋጉት፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በውጊያና በጉልበት ብቻ ሳይሆን ለሃይማኖት ሲባል በማዘንም ማገዝ እንደሚቻል ማመን እንደሚገባ ተገልጾአል። ጦርነትን በውጊያ ብቻ ሳይሆን ‹‹የሚያዝኑ ብፁዐን ናቸው›› እንደ ተባለ በማዘንና ወደ እግዚአብሔር በማልቀስ ድል መንሣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ምን ዓይነት መንፈሳዊ የሥነ ልቡና ልዕልና ነው? (ማቴ. ፭፡፬)። ኢጣሊያኖች የጎደላቸው ይህ ዓይነቱ ‹‹መሣሪያ›› ነበር።


የኢጣሊያ መልእክተኞች ሁሉ ለጦርነት መቋመጣቸውንና በጉልበታቸው ክፉኛ መመካታቸውን ያዩት እቴጌ ጣይቱም ‹‹የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ ይህን ግፍ ተመልከት። በመድፋቸውና በጠብ መንጃቸው ተመክተው የፈቀዳቸውን ተናገሩ፤ ኃይል የእግዚአብሔር መሆኑን አላወቁም። እኛም በክርስቶስ ኃይል አንፈራቸውም›› ማለታቸው ያነሣነውን ጉዳይ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የአድዋ ጦርነት እጅግ የተለያየ የኑሮና የፍልስፍና ሐሳብ (Paradigm) ባላቸው ሁለት ተቃራኒ ሀገራት መካከል የተደረገ ጦርነት ነው። አንደኛዋ ሀገር ቅኝ ገዢና ወራሪ፣ ብዙ ሀገራትን አስቀድማም የወረረች፣ አሉ ከተባሉ ሥልጡን ሀገራት አንዷ፣ ባለኝ የጦር መሣሪያና የሠለጠነ የወታደር ኃይል አሸንፋለሁ ብላ የምታስብና የምትወጋትን ሀገር እጅግ የናቀች፣ ጥቁር የነጭ ባሪያ መሆንና በነጭ ሥር መተዳደር አለበት ብላ የምታምን፣ የሌላ ሀገርን ሀብትና ንብረት ለመዝረፍ የመጣች፣ የወታደሮቿ የመጨረሻ ግብ ቅኝ ገዝተው ጀግና ተብለው መሞገስና የተሻለ ሀብትንና ዝናን እንደ ሀገርም እንደ ግልም ማካበት የሆነባት… ወዘተ ነበረች።

ሁለተኛዋ ደግሞ በተቃራኒው ቅኝ ገዝታም ተገዝታም የማታውቅ፣ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብንም ‹አግባብ አይደለም› ብላ የምትጠየፍ፣ ከሥልጣኔ አንጻር እጅግ ኋላ ቀር የምትባል፣ ከጉልበት ይልቅ በእግዚአብሔር የሚያምኑ ዜጎች የሞሉባትና የቱንም ሀገር ስለ ድህነቱ የማትንቅ፡ ስለ ብልጽግናውም ክባ የማትፈራ፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረና እኩል እንጂ ማንም የማንም ባሪያ እንዳልሆነ የምታምን፣ የሌላን የማትነካ የራሷንም የማታስነካ፣ የዜጎቿ (የወታደሮቿ) የመጨረሻ ግብ ሀገርንና ሃይማኖትን ማዳንና ለዚህም ሲባል በመሠዋት ሰማያዊ ክብርን ማግኘት … ወዘተ ነበር።


በዚህ የእሳቤ መሠረት የተነሣ ኢትዮጵያውያን ወኔያቸው ልዩ ነበር። ይህ ወኔ ‹‹የቆምኩትና የምዋጋው ለእውነት ነው፤ ምድራውያን ብቻ ሳይሆኑ እግዚአብሔርና በሰማይ ያሉ አገልጋዮቹ ሁሉ አብረውኝ አሉ፤ ብሞት እንኳን ሞቴ የከበረ ነው›› የሚል ግዙፍ አስተሳሰብ የፈጠረው ፍርሃትን የሚያርቅ ወኔ ነው። በዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች ወደሚሞቱበት ቦታ ሲወሰዱ እንደ ሌሎች ከመፍራትና ከመለማመጥ ይልቅ በፈገግታና ወደ ሰርጉ እንደሚሔድ ሙሽራ በደስታ እንደ ነበረው ሁሉ፡ ኢትዮጵያውያንም ይህ ዓይነቱ አሳብ በልባቸው የተሰነቀ ነበር። ስለዚህ ምንም መሣሪያን ያልያዙት፣ እንኳን መሣሪያን ሊይዙ ይቅርና ለእግራቸው ጫማ ያላደረጉትም ቢሆኑ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጸጉሩ የታጠቀ የኢጣልያ ወታደር ፊት ሲቆሙ በጥብዐትና በጀግንነት ነበር። በአንጻሩ ደግሞ የኢጣልያ ተዋጊዎች የኃይል ሚዛኑ በጥቂቱም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያውያን ባደላበት ጊዜ ሁሉ ፍርሃት የሚወራቸው ዓይነት ነበሩ። የአምባላጌን በመሰሉት ውጊያዎች ላይ የኢትዮጵያውያኑን ድል ካዩ በኋላ አስጨናቂ የፍርሃት ዝግጅትን ያደርጉ የነበረው ለዚሁ ነበር። የመቀሌው ምሽግ እዚህ ላይ ሁነኛ ማስረጃ ይሆነናል፤ ጳውሎስ ኞኞ (፻፸፪-፻፸፭) እንደ ተረከው በመቀሌው ምሽግ የኢጣሊያ ወታደሮች በቅድሚያ ፫ ሜትር ስፋት ያለው ግንብ ገነቡ።
ይህ አልበቃ ብሏቸው በ፴ ሜትር ውስጥ በጣም የሾሉ ከፍታቸው ፴ ሳ.ሜ. የሆኑና አንዱ ካንዱ በ፳ ሳ.ሜ. የሚርቁ እንጨቶችን በብዛት ቸከሉ። ኢትዮጵያውያኑ ግር ብለው ሲመጡ እግረኞቹም ፈረሰኞቹም በነዚህ እንጨቶችላይ እየወደቁ ተሰክተውባቸው እንዲሞቱ ነበር። ይህም አልበቃቸውም፤ ከዚያ ቀጥሎ እሾኻማ ሽቦ እያድበለበሉ አስቀመጡ። ይህም ‹‹እንኳን ሰው ወፍ አያሾልክም›› የተባለለት ነበር። አሁንም ፍርሃቱ ስላልለቀቃቸው ጠርሙስ ሰብረው ነሰነሱ። ይህም በባዶ እግራቸው የሚመጡ የኢትዮጵያውያንን እግር ሸረካክቶ ለማስቀረት ነበር። ለመሞት አስቀድመው የተዘጋጁት አባቶቻችን ግን ታንክና ተዋጊ ቆራርጦ ባይኖራቸውም፡ ይህን ሁሉ ያልፉ ዘንድ በሃይማኖት ጥብዐት የተቃኘው ወኔያቸው በቂ ነበር። በባዶ እግራቸው በጠርሙስ ላይ ለመራመድ፣ ስስ ልብስ በሸፈነው ገላቸውም የተጠቀለለ ሽቦን ለመሻገር አላመነቱም። ግዙፉን ምሽግ እግዚአብሔርን ይዘው ሰበሩት። ይህ የኢትዮጵያውያኑ ወኔ ያስገረመው የኢጣሊያው የጦር መሪ የነበረው ጄኔራል ባራቲዬሪ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹እኛ የሠለጠነው ዓለም ሥልጡን ወታደሮች ምንም አያውቁም ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን የምንማረው ትምህርት አለ።
አበሾች ለባሩድና ጥይት ይሳሳሉ። የሚገድሉ ካልሆነ በስተቀር አይተኩሱም። ለዚያውም ቢሆን ፲ እና ፲፭ እርምጃ ያህል ቀርበው ባንድ ጥይት ደራርበው መግደል ይፈልጋሉ። ያለዚያ ተደበላልቀው በጎራዴ መምታት ይመርጣሉ እንጂ ጥይት ማበላሸት አይወዱም። ይህም በማስጮህ ብቻ ጥይት ለሚያባክነው ለሠለጠነው አገር ወታደር ጥሩ ትምህርት ነው። ለምሳሌ ደጀን የነበረው የመድፈኛው አዛዥ ካፒቴን ፍራንዚኒ መድፎቹን ይዞ ከጦር ሜዳ እንዲገባ ታዘዘ። ፴ ኪ.ሜ. ያህል ተጉዞ ከጦሩ ሜዳ ገባ። ቦታውን አመቻችቶ አንድ የመድፍ ጥይት ገና እንዳስተኮሰ ተገደለ። ይህም ሊሆን የቻለው ያቺን የመድፍ ጥይት ድምጽ የሰሙ ኢትዮጵያውያን በንዴት ተሞልተው በብዛት ሆነው ስለ ወረሩት ነው። የተመካንባቸው ደጀን የነበሩት መድፎቻችንም ካንድ ጥይት ተኩስ በኋላ ተማረኩ…››። ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ በሚል መጽሐፋቸው እንደ ገለጹትም ‹‹…ሠራዊቱ ቀለብ ሊያመጣ የሔደው፣ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሊስም የሔደው ኹለት እጁ ነው እንጂ አንድ እጁ ለጦር አልደረሰም። የተኩሱን መድመቅ በሰማ ጊዜ ሠራዊቱ ተሰልፎ ተነሣ። አጤ ምኒልክም ከበቅሎ ወጥተው ወደሱ መንገድ ጀመሩ። ሰልፉ ግን አልተገናኘም። በየፊቱ ክምር እንዳየ ዝንጀሮ ወደ ጦሩ ወደ መድፉ ይሮጥ ነበር።… መድፉ ይመታኛል፣
ነፍጡም ይጥለኛል እሞታለሁ ብሎ ልቡ አልፈራበትም። …የቈሰለውም ሰው ‹አልጋው ይቁም እንጂ ኋላ ስትመለስ ታነሣኛለህ፣ በመሀይም ቃሌ ገዝቼሃለሁ› ይለው ነበር። ጥይትም ያለቀበት እንደ ሆነ የቈሰለውን ሰው ከወገቡ ዝናሩን እየፈታ እያባረረ ወደ ፊት ይተኩስ ነበር። ሰውም ከመንገድ ርዝመት ከተኩሱ ብዛት የተነሣ ደክሞት የተቀመጠ እንደ ሆነ ‹የምኒልክ ወሮታ፣ የጮማው የጠጁ ይህ ነውን?› እየተባባለ እንደ ገና እየተነሣ ይዋጋ ነበር››። በኢጣሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነትን ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ከጦርነቱ በፊት ጦርነቱ እንዳይካሔድ ያደረጉት ጥረትና ከጦርነቱ በኋላም ያሳዩት ጠባይ ከፍርሐትም ከተዐብዮም የራቀና ክርስቲያናዊነትን የተሞላ ነበር።

የዐፄ ዮሐንስ ልጅ የሆኑት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከአዲ አምባይ የጦር ሰፈር ለጣልያኑ ንጉሥ አስቀድመው ‹‹ለታላቁና ለተከበሩ ንጉሥ ኡምቤርቶ፤ በአሁኑ ጊዜ ሰይጣን በመካከላችን በመግባቱ ክርስቲያን የሆንን ሕዝቦች እርስ በርሳችን እንድንፋጅ ሆነ፤ ባለፈው ጊዜ የደረሰው ሁሉ የሰይጣን ሥራ ነው። ሰላምን ስለምንፈልግ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነ ሰው ይላኩ።›› በማለት መልእክትን መላካቸው ለዚህ ማሳያ ነው። ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላም ታዲያ ይህ ትሕትና በትዕቢትና በትምክህት ሳይቀየር ንጉሡ ‹‹በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አረግሁአቸው ብዬ ደስ አይለኝም…›› ማለታቸው ይህንን የመንፈሳዊ ልዕልና ያሳያል። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፶፱)። ‹‹እኔ ሴት ነኝ። ጦርነት አልወድም። ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ…›› (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፻፵፰) ብለው የተናገሩት የእቴጌ ጣይቱ ታዋቂ ንግግርም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ሲተረጉም ‹‹እግዚአብሔር ከሌለበት ሰላም እግዚአብሔር ያለበት ጦርነት ይሻላል›› ብሎ ከተናገረው ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው። (ሮሜ.፲፪፥፲፰)።

በእውነትም ሀገርና ሃይማኖትን ከሚያሳጣ ‹ሰላም›ስ ጦርነት ይሻላል። በርግጥ በአድዋ ድል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ በብዙ መልኩ የሚነገር ነው።


በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውንና ሕዝቡን የሚመሩ አባቶችን ሁሉ አዝምታለች፤ ማዝመቷም በጸሎት እንዲያበረቱ ነው። ይህም ለዘማቹ ሁሉ እጅግ የሚያበረታታ ተግባር ነበር። ከዘመቱት መካከል ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ፣ እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፣ የደብረ ሊባኖስ ፀባቴ፣ ከእንጦጦ ማርያም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ኪዳነ ወልድ፣ ንቡረ ዕድ ተክለ ጊዮርጊስ፣ መምሬ ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ተክለ ማርያም፣ አፈ ንቡረ ዕድ ገብረ ማርያም፣ መምህር አርአያ፣ መምህር ገብረ መድኅን፣ ቀኝ ጌታ ቢሆን…ወዘተ ካህናት፣ ሊቃውንት (ከቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ ከሆለታ ኪዳነ ምሕረት….) ይገኙበታል። ሕዝቡ እግዚአብሔር አብሮት እንዳለ እንዲያስብና በዘመቻ መንገዱ ሁሉ የሥነ ልቡናው ብርታት እንዳይሸረሸርም የንዋያተ ቅድሳት አብሮ መዝመት አስፈላጊ ነበር። ከታቦታት– የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም፣ ከሸዋ የግንባርዎ ማርያም፣ የበር ግቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የአክሱም ማርያምና መድኃኔዓለም…ወዘተ የዘመቱ ሲሆን መስቀሎች፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት፣ ቃጭል፣ ጥላዎች፣ ድባቦች፣ ሥዕላት – በተለይም የግንባርዎ ማርያም ‹አምለሱ› ሥዕለ ማርያም …ወዘተ ዘምተዋል። (በአድዋ ጦርነትና ድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ፣ ገጽ ፳፮-፳፰)::


በርግጥ ታቦትና ንዋያተ ቅዱሳትን ይዞ መዝመት ብቻ ለድል አያበቃም፤ እግዚአብሔርን በማያስቆጣ መንገድ መጓዝና ከእውነትና ከፍትሕ ጎን መሰለፍ እንጂ። ቤተ ክርስቲያንም ንዋያተ ቅድሳትንና የሃይማኖት አባቶችን ከማዝመትም በላይ የምእመናንን ሥነ ልቡና የገነባችበት መንገድ ለጦርነቱ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ምናልባትም ያ ባይኖር ድሉም አይኖርም ነበር። ብዙ ጸሐፊዎችም ድሉን ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያያይዙት ለዚሁ ነው። አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ የተባሉ ሊቅ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ-ነው መልኳ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው የአድዋውን ድል መሠረት እንደሚከተለው ገልጠዋል። ‹‹… ምኒልክን ለአድዋው ድል ያበቃቸው አንዱም ፣ ኦርቶዶክሳዊ እምነታቸውና የልብ ጸሎታቸው ነው።›› (ገጽ፣፷፭) ዳንኤል ሮኘስ የተባለ ታዋቂ የፈረንሳይ ጋዜጠኛ ‹‹የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ታውቋታላችሁን?›› በሚል ርእስ ባዘጋጀው መጣጥፍ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል። “ወራሪዎች ምድርዋን የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴ መሣሪያዋ ሆኖ በመገኘቱ በነፃነት ተመልሳ ተገኝታለች›› የአድዋን ድል በቀጥታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ጋር ያያያዙት ሌሎችም ኢትዮጵያን በአፍሪካ እንደምትገኝ ኢየሩሳሌም አድርገው መቍጠር ጀምረው ነበር። ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጆናስ ‹‹ THE BATTLE OF ADWA:-African victory in the age of Empire›› በተሰኘው ታሪካዊ መጽሐፋችው ‹‹የዓድዋን ድል ተከትሎ በመላው ዓለም ተበትነው ያሉ ዝርዋን አፍሪካውያን የዓድዋን፣ የምኒልክንና የነጻይቱን አገር ኢትዮጵያን ስም በልዩ ሁኔታ ማንሣት ጀመሩ፤ ጥቁር ሕዝቦች እንደ ታላቂቷ ጽዮናዊት ኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ጉዞ ማድረግ ጀመሩ።›› ሲሉ መግለጻቸው ለዚህ ምስክር ነው። አንድ ጣልያናዊ ተዋጊም ‹‹በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ወደ ቀኝና ወደ ግራ እየተመላለሰ ወደ ጦርነቱ ግቡ ኢጣሊያኖችን ማርኩ እያለ ትእዛዝ ሲሰጥና ሲዋጋን የዋለ ማነው?›› ብሎ መጠየቁ እየተገለጸ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጋዥነት መገለጹም እዚህ ላይ መነሣት የሚገባው ነው። (በአድዋጦርነትና ድል…፣፶፫)። ይህንንም በአንድ ባለ ቅኔ፡- ‹‹ኃይል ውእቱ ዘጊዮርጊስ፣ አኮኑ ኵዕናት በላዔ ሮማዊት ነፍስ፣ ዘጌዴዎን ምኒልክ ዘአውረደ በዐውደ ሮምያ ጠለ ደም እምርእስ። (በአድዋ ጦርነትና ድል…፣ ፶፪)። (የሮማዊትን ነፍስ (ሰውነት) የበላ (ድል ያደረገ) የጊዮርጊስ ኃይል እንጂ ጦር አይደለም፣የጌዴዎን ምሳሌ ምኒልክ በሮምያ አደባባይ ከራስ ላይ እስካወረደ ጠብታ ደም።) ተብሎ የተነገረ ነው። የአድዋ ድል ብሔራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ትሩፋቱ ባሻገር ሃይማኖታዊ ትሩፋቱም መነገር የሚገባው ነው።

‹ኢትዮጵያውያንን እንደ እስራኤል ዘነፍስ መቍጠርና ሀገሪቱንም ጸጋ እግዚአብሔርን የታደለችና ሀገረ እግዚአብሔር እንደ ሆነች አድርጎ ማየት፣ ሀገረ እግዚአብሔር ከሆነች ዘንድም መደፈር የለባትም በሚል እሳቤ ድንበሯን መጠበቅና በዚህም ሂደት መሠዋት የዜግነት ክብር ብቻ ሳይሆን ጽድቅም ነው ብሎ ማመን› ለኢትዮጵያውያን አዲስ እሳቤ ባይሆንም በአድዋ ድል ግን ይበልጥ ጠንክሯል፤ ከዓለም ሕዝብ መካከልም ይህንን ያመኑ እጅግ ብዙ ነበሩ። ከነጮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ በተለይ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ ‹ኢትዮጵያኒዝም› በሚል ስያሜ እንዲጀመር መሆኑ ለዚህ ምስክር ነው። ለማጠቃለል ያህል የአድዋ ድል ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገነባችው የመንፈሳዊ ሥነ ልቡና ብርታትና ለሀገርና ለሃይማኖት እስከ ሞት የመጋደል ወኔ የተገኘ መሆኑ ከድሉ እኩል መነገር ያለበት ነው።

ኢትዮጵያውያን የኢጣሊያን ወረራ በሀገረ እግዚአብሔር ላይ እንደ ተደረገ ሰይጣናዊ ጥቃት ነበር የቈጠሩት። ለዚህም ነው ድሉን እንኳን ሰይጣን ድል ከተነሣበት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር በማመሳሰል ‹‹ሞዖ ለሞት ሠዐሮ ለጣዖት ገብረ ትንሣኤ በሰንበት›› እያሉ ዳግመኛም‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ሰማዕታት›› ብለው እየዘመሩ ያከበሩት። (በአድዋ ጦረነትና ድል…፣ ፷)።


የአድዋ ጦርነት ሊጀመር ሰዓታት በቀሩበት ጊዜ እንደ ተዋጊ ሳይጨነቁ፣ ሁሉን ትቶ በተጠንቀቅ ከመቆምና የነደፉትን የውጊያ ስልት ከማሰላሰል ይልቅ ‹እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይበልጣል› በሚል ታላቅ የሥነ ልቡና ዐቅም ዐፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ …ወዘተ በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እያስቀደሱ ነበር። በርግጥ ከዚህም በኋላም ንጉሡ በእርጋታቸው ጸንተው ዕለቱ ጊዮርጊስ በመሆኑ አሁንም ወደማይጕዓጕዓ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ልባዊ ጸሎትን አቅርበው ነበር። በጦርነት መጀመሪያ የመጨረሻው ሰዓት ለዚያውም ዐቅሙ እጅግ የሚገዝፍ ጠላት ከፊት ተደግኖ እንዲህ ዓይነት መረጋጋትን ያሳዩ ሌሎች ተዋጊዎች መኖራቸው እጅጉን አስገራሚ ነው። ይህ በርግጥም መንፈሳዊ ጥብዐት እንጂ ምን ይባላል? በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፡ ተሰብስበው ሲያስቀድሱ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ቀዳሽ ነበሩ። እርሳቸውም ከቅዳሴ በኋላ ሲያስተምሩ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ልጆቼ ሆይ… ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነው። ኺዱ ለሃይማኖታችሁ፣ ለሀገራችሁ ሙቱ፤ እግዚአብሔር ይፍታህ››። (ጳውሎስ ኞኞ፣ ፪፻፫)። በእውነት የእግዚአብሔር ፍርድ በዕለቱ ተፈጸመ፤ ለሀገርና ለሃይማኖት የተሠዉትን ሁሉ ነፍሳቸውን ይማርልን።(ሐመር መጽሔት)