
የሕማማት ዕለተ ረቡዕ ከምክረ አይሁድ ባሻገር የእንባና የሽቱ ቀን ተብሎ ይጠራል። በዚህች ቀን ማርያም እንተ ዕፍረት የጌታችንን እግሮች በእንባዋ ማጠቧንና ሽቱ መቀባቷን እናስባለን።
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው የመንግሥቱ ወንጌል በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ስሟ ስለሚታሰበው ቅድስት፡ ስለቀባችው ሽቱና ስለቀባችበት ሁኔታ እናንብብ።
ይህች ቅድስት ቀድሞ በዝሙት የኖረችበትን አስከፊ ሕይወት በመተው በቆራጥ ኅሊና ፍጹም ንስሓ ገብታ ገንዘቧን ሁሉ አውጥታ እጅግ ውድ የሆነውን ሽቱ ገዝታ ጌታችንን ስትቀባው ጌታችንም በፍጹም ንስሓዋ ተደስቶ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል›› በማለት አስደናቂ ትእዛዙን የሰጠላት ቅድስት ናት፡፡ ማቴ 26፡6፡፡ ይህንን የጌታችንን ትእዛዝ ልብ ብለን ካየነው በውስጡ ብዙ ምሥጢራትን የያዘ ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ስለ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው ራሱ መድኀኔዓለም ክርስቶስ መሆኑን በዚሁ ልብ ይሉታል፡፡
ማርያም እንተ ዕፍረት የቀድሞውን ሕይወቷን ስናየው ሁልጊዜ ከነጭ ሐር የተሠራ ልብስ የምትለብስ፣ ከሽቱ ሁሉ ይልቅ የሚበልጥ ውድ ሽቱን ትቀባ ነበር፡፡ በወርቅም ታጌጥና በክፉ ሥራ ሁሉ ጸንታ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የዚህን ዓለም ጣዕም አጣፈጠላት፡፡ ነገር ግን ስለዚህች ሴትና ስለ ኃጥአን ሁሉ ጌታችን ከጌትነቱ ከፍታ ሳይለወጥ ከልዑል ዙፋኑ ወረደ፡፡ በሰዎች መካከልም ከእነርሱ እንደ አንዱ እየተመላለሰ አስተማረ፡፡
አንድ ቀን እንደልማዷ ማርያም እንተ ዕፍረት ነጭ ሐር ለብሳ፣ አጊጣና ተኳኩላ ፊቷን በመስታወት አይታ ውድ ሽቱ ተቀባች፡፡ ጉንጮቿ ቀያዮች፣ ዐይኖቿ የተዋቡ ሆነው ደም ግባቷ በጣም አማራት፡፡ እንደዚህ እየተመለከተች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች፡፡ ከዚህ በኋላ መልካም አሳብ በእርሷ ላይ አድሮ እንዲህ አለች፡- ‹‹ይህን ሁሉ ታስወግድ ዘንድ መልኬንም ትለውጥ ዘንድ ሞት ትመጣ የለምን? ይህ መልካም ሽታ ወደ ትልነትና ወደ መሽተት ይለወጣል፡፡ ይህስ ብርታት ፍጻሜው ጉስቁልናና ድካም አይለምን? ሊቀርቡኝ የሚወዱትስ የሚርቁኝ አይደሉምን? እንደዚህስ ከሆነ ዘለዓለም ከጥፋትና ከኩነኔ በቀር እንግዲህ ምን አገኛለሁ? የዚህን ዓለም ገንዘብ ብገዛ፣ ብነዳ ከድካም በዐይኖቼም ዕንባን ከማፍሰስ የሚያድነኝ ይኖራልን? ወይስ ይህ ሁሉ ከሞት ያድነኝ ዘንድ ይችላልን? ነፍሴ ሆይ! እንግዲህ ሁሉን ለሚገዛ ጌታ ምን ትመልሻለሽ? ከእውነተኛው ፈራጅ ዘንድ በአንቺ ላይ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! ንስሐ በሌለበት፣ ነፍስ የተናቀች በምትሆንበት ጩኸት፣ ልቅሶና ጩኸት ባለበት ቦታ የሚረዳሽ ማነው? ነጭ ሐርና ኅብሩ ልዩ ልዩ የሆነ ልብስ በመልበስ ደስ የምትሰኝ ሥጋዬ ሆይ በክብር ባለቤት በእግዚአብሔርና በመላእክቱ ፊት ራቁትሽን በቆምሽ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! በዚህ ዓለም የተደሰችው ምን ይጠቅምሻል?…›› እያለች ራሷን መመርመር ጀመረች፡፡
ከዚህ በኋላ በማመን ጸንታ እንዲህ ብላ አሰበች፡- ‹‹ስለ ኃጥአን ወደዚህ ዓለም የመጣ ስለ እነርሱ በመካከላቸው እንደሰው የተመላለሰ ይህ አይደለምን? የኃጢአተኛን መመለሱን ነው እንጂ ሞቱን አልሻም ያለውስ እርሱ አይደለምን? ነፍሴ ሆይ ምሕረትስ ቅርብ ናት፣ ባለመድኃኒትም የራቀ አይደለም፣ ሌላ መድኃኒትሽን ተስፋ የምታደርጊበትስ አለን? መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዲቱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልጋት የሚሄድ አይደለምን? ባገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከማታል፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሷ ደስ የሚሰኝ አይደለምን? እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ የሚል እርሱ መድኃኒት ክርስቶስ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ለምን እሰንፋለሁ? ለምንስ ንስሓ አልሻም? እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ወደ እርሱ ሄጄ ራሴን በፊቱ እክዳለሁ›› ብላ ካሰበች በኋላ ተጽናናችና በፍጥነት ተነስታ ገንዘቧን፣ የገዛችውን ወርቋንና ብሯን ሁሉ ሰበሰበች፡፡
‹‹ምን አደርጋለሁ ይህን ገንዘብ ወስጄ ብሰጠው አይቀበልም እርሱ ፈጣሪ፣ ጌታና የዓለም መድኃኒት ነውና›› ብላ አሰበች፡፡
ከዚህ በኋላ ሽቱ ወደሚሸጥ ሰው ፍለጋ ሄደች፣ ያን ሰው ከጥንት ጀምሮ ታውቀው ነበርና ከእርሱ ዘንድ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቱን ገዛችና በደስታ ስትሄድ እነሆ ሰይጣን በወርቅ ያጌጠች ሴት መስሎ ወደ እርሷ መጣ፡፡ የዚህን ዓለም ምኞት እያጣፈጠ ይነግራት ጀመር፡፡ መብላትን፣ መጠጣትን፣ ያማረ ልብስ መልበስን፣ ሽቱ መቀባትን… ይህን ሁሉ ያሳስባት ጀመር፡፡ ጌታችንም በይቅርታው ብዛት የጠላት ዲያብሎስን ክፋት ገለጠላትና ‹‹ለበደልና ለኃጢአት ሥራ የተዘጋጀሁ አድርገኸኛልና ኃፍረትና ጉስቁልናንም በእኔ ላይ አምጥተሃልና አንተ ሰይጣን ከእኔ ወግድ›› ብላ በቁርጥ ነገር መለሰችለት፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የሃይማኖቷን ጽናት ባየ ጊዜ ከእርሷ ሽሽቶ ፈሪሳዊ ወደሚሆን ስምዖን ወደሚባል ሰው ዘንድ ሄዶ ልቡናውን ያውከው ጀመር፡፡ እርሱም ጌታን በቤቱ ማዕድ ይመገብ ዘንድ ጋብዞት ነበርና፡፡በልቡናው ያደረው ክፉ ሰይጣንም እንዲህ እንዲል አደረገው፡- ‹‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ኃጢአተኛ እንደነበረች አያውቅም ነበር? ብሎ እንዲያስብ አድረገው፡፡››
“ከንቱ ነገርን ስትመለከቱ የኖራችሁ ዐይኖቼ ሆይ! ጌታን ታዩ ዘንድ ተሰጣችሁ፤ ርኩስን የምትዳስሱ እጆቼ ሆይ! የሰማያዊ ጌታን እግር ትዳስሱ ዘንድ ሰጣችሁ፤ ኃጢአተኛ ነፍሴ ሆይ! እነሆ ፈጽሞ ከፍ ያለ ባለሟልነትን አገኘሽ፤ ስላደረገልኝ ምን እከፍለዋለሁ› እያለች ታላቅ ልቅሶን አለቀሰች፡፡ የጌታንም እግር ይዛ በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ ታብስ ጀመር፡፡ አስቀድማ በልቧ እንዲህ ብላ አስባለችና ‹በጌታ ፊት ባለሟልነትንስ ካገኘሁ ወደ እርሱ ዘንድ እንድቀርብ ያደርገኛል፡፡ በሥራዬም ክፋት ካበረረኝ ግን ዳግመኛ አልድንም› ብላ አስባ ነበር፡፡ ከጌታም ባለሟልነትን ባገኘች ጊዜ ጨክና በራሱ ላይ ሽቱውን ጨመረች፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋርም ልቅሶንና ልመናን አላቋረጠችም፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ በእርሷ ላይ እንደበዛ ባየ ጊዜ ጠላት ዲያብሎስ በእርሷ ላይ ታላቅ መቅናትን ቀናባት፡፡ ተቆጥቶም ወደ ስምዖን ተመልሶ ልቡን አወከው፡፡ ‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ኃጢአተኛ እንደሆነች ያውቅ ነበር› እንዲል አደረገው፡፡
ጌታችንም ስምዖንን ሁሉ ከእርሱ እንዳልተደበቀና ሀሳቡንም እንዳወቀበት እንዲረዳና እግዚአብሔርም በደለኞችን ማዳንና ከኃጢአታቸው ማንጻት እንደሚችል ያውቅ ዘንድ እንዲያስተውል አደረገው፡፡›› ሉቃ 7፡36-50፡፡
ይህ እጅግ ውድ ዋጋ ያለው የማርያም እንተ ዕፍረት ሽቱ መነሻ መገኛው ራሱ ጌታችን ነው፡፡ ይኸውም ነገሩ እንዲህ ነው፡- ‹‹ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን አረጋዊ ዮሴፍ ሕፃኑንና እመቤታችንን ይዞ ወደ ምድረ ግብፅ ሲሄዱ በመንገድ ላይ አንድ ፈረሰኛ ሰው አገኛቸውና ከእነርሱም ጋር ይሄድ ጀመር፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያምን በመንገድ እንደደከመች ባየ ጊዜ ሕፃኑን አንሥቶ ፈረሱ ላይ አውጥቶ በጭኑ ታቀፈው፡፡ ያንጊዜም በፈረሱ ላይ የመልካም ሽቱ መዓዛ ይሸት ነበር፡፡ ወዙም ሲንጠፈጠፍ ባየው ጊዜ መልካም ሽታም እንዳለው ባየ ጊዜ ሻሹን ከራሱ ላይ አውልቆ የሕፃኑን ወዝ ጠረገለትና ቆይቶ ሕፃኑን ለእናቱ ሰጥቷት በጐዳናው ሄደ፡፡ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ልብሱን ታጥበው ዘንድ ለእናቱ ሰጣት፣ እርሷም በሻሹ ላይ ያለውን መልካም ሽታ ካየች በኋላ በማጠቢያ ባስቀመጠችው ጊዜ ከሻሹ ውስጥ ሽታው እጅግ የሚያስደስት መልካም ዘይት ወጣ፡፡
እርሷም ደስ ተሰኝታ ከቅባቷ ጋር በማሰሮ አድርጋ አስቀመጠችው፡፡ ያም ዘይት ባለበት በዚያች መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ የሽቶውን መዓዛ ያደንቁ ነበርና ስለዚህ ያች ሴት ከአገረ ገዥው ጋር እንዳያካስሷት ፈርታ በብዙ ገንዘብ ሽቱ ከሚገዙ ነጋዴዎች ለአንዱ ሸጠችለት፣ እርሱ ግን ምን እንደሆነ አያውቅም ነበር፡፡ ያም ዘይት ብፅዕት ማርያም እንተ ዕፍረት እስክትመጣ ድረስ ለብዙ ዘመን በእርሱ ዘንድ በዚያ ኖረ፡፡ ማርያም እንተ ዕፍረትም ከእርሱ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ ገዝታ በጌታችን ሥጋ ላይ አፈሰሰችው፡፡ እነሆም ይህ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነው ሽቱ ከጌታችን ዘንድ እንደተገኘ የታወቀ ሆነ፡፡ ያም በፈረስ ላይ ተቀምጦ ጌታችንን በሕፃንንቱ በጭኑ አቅፎ የያዘው ፈረሰኛ ሰው ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ያመነበት ፊያታዊ ዘየማን (ጥጦስ) ነው፡፡››
ማርያም እንተ ዕፍረት ጌታችን ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ ዐርፋለች፡፡ የንግሥ በዓላቶቿ መጋቢት 21 ቀን የጌታችንን እግር ሽቱ የቀባችበት ሲሆን የካቲት 6 ቀን ደግሞ ያረፈችበት ዕለት ነው፡፡ ጥቅምት 1 ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሏ እንዲሆን አባቶቻችን ሕግ ሠሩልን፡፡ የማርያም እንተ እፍረትን ገድሏንና ድርሳኗን የጻፈላት ታላቁ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡
የቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረትን ረድኤት በረከቷን ያሳድርብን፣ በጸሎቷም ይማረን።
( ገድለ ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት፣ የጥቅምትና የካቲት ስንክሳር)

