
በቤተክርስቲያን የጸሎት ሕይወት ውስጥ ታላቅ ቦታ ካላቸው ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ‹መጽሐፈ ግብረ ሕማማት› ነው፡፡ ሊቃውንቱ ‹ግብር› የሚለውን ‹አገልግሎት› ብለው ይተረጉሙትና ‹ግብረ ሕማማት› ማለት ‹በሕማማት ወቅት የሚፈጸም አገልግሎት› ማለት ነው ይላሉ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹እርሱ ሕመማችንን ተሸከመ› (ኢሳ 53÷4) በማለት የገለጠው ኃይለ ቃል ለሰሙኑም ሆነ ለመጽሐፉ ስያሜ መነሻ መሆኑንን ሊቃውንቱ ይገልጣሉ፡፡ ሐዋርያትም በሥርዓት መጽሐፋቸው ‹ወአንት ሙሰ ተዐቀቡ ወግበሩ ተዝካረ ሕማማቲሁ – እናንተ ግን ተጠበቁ፣ የሕማማቱንም መታሰቢያ አድርጉ› ብለው ደንግገዋል (ግብረ ሕማማት፣ 1996፣9) ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም <ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክብረ ወስብሐተ – የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና ብሎ የጠራ እግዚአብሔር ይመስገን› ብሎ ገልጦ ነበር፡፡
ግብረ ሕማማት ከበዓለ ሆሳዕና እስከ በዓለ ፋሲካ የሚከናወነውን ሥርዓት የያዘ ትልቅ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፉ የተወሰነ ክፍልና ሥርዓቱ ከ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ ጀምሮ በግብጽ ቤተክርስቲያን ነበረ፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ አሁን በምናየው መልኩ የሰሙነ ሕማማት ምንባባትን ያዘጋጁት የገዳመ መቃርስ መነኮሳት መሆናቸውን ግብረ ሕማማት ይገልጥልናል፡፡ በእነዚህ የገዳመ መቃርስ አባቶች በመታገዝ የእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ገብርኤል 2ኛ (1131-1145) (የኛ ግብረ ሕማማት “ጸሐፊ የነበረው የታሪክ ልጅ አባታችን አባ ቅብርያል” ይለዋል፡፡ ኢብንቱርያክ የሚለውን ተርጉሞ ሳይሆን አይቀርም፡፡) የሰሙነ ሕማማት መጽሐፍ (ፓሻ) በእርሱ አስተባባሪነት ሊቃውንቱ ለየቀኑ እና ለየሰዓቱ የሚሆኑትን ምንባባት ከብሉይ እና ከሐዲስ እያውጣጡ አዘጋጇቸው፡፡
ፓትርያርክ ገብርኤል አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስና የሊቃውንት ትርጓሜ ዕውቀት ያላቸው ሊቃውንት በማሰባሰብ ለየሰዓቱና ለየኩነቱ የሚነበበውን ሥርዓትና ንባብ አዘጋጁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በሰላማ መተርጉም ጊዜ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ከጎንደር መድኃኔዓለም ተወስዶ በብሪቲሽ ሙዝየም በሚገኘው ግብረ ሕማማት ላይ ከአባ ሕርያቆስ ድርሳን መጨረሻ ላይ <<ዘንተ መጽሐፈ ዘተርጎመ ብፁዕ ወርቱዕ ሃይማኖት አቡነ አባ ሰላማ ይጽሕፍ ስሞ እግዚአብሔር ውስተ መጽሐፈ ሕይወት› ይላል፡፡
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ የብሕንሳው ጳጳስ አቡነ ቡትሮስ ምንባባቱን ለየሰዓታቱ በተመጣጣኝ ሁኔታ በማካፈል ሁሉም ቀናት ተመጣኝ የሆኑ ሁሉም ዓይነት ምንባባት እንዲኖሯቸው አድርገዋል፡፡ ግብረ ሕማማታችንም «ከኦሪት እና ከነቢያት፣ ከነዌ ልጅ ከኢያሱ፣ ከንጉሥ ሰሎሞን መጽሐፍ ወስዶ ሁላቸው ትክክል እስከ ሆኑ ድረስ በየሰዓቱ ሁሉ የሚገባውን አደረገ፡፡ አባቶች ከተናገሩት ሁለት ሁለት ተግሣፅ እና ምክር አንዱ በነግህ አንዱም በማታ እንዲነበብ አደረገ» ይላል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንደሚሉት ከሆነ ግብረ ሕማማትን አሁን ባለው መልክ ያዘጋጁት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ናቸው፡፡ እስከ 14ኛው መክዘ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለሰሙነ ሕማማት የሚሆኑ የጸሎት ሥርዓት ሳይኖሯት ቆየች ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ አቡነ ሰላማ መተርጉም የተወሰነውን የመጽሐፈ ግብረ ሕማማት ድርሳናት በመተርጎም ቀድሞ በነበረው የሰሙነ ሕማማት የጸሎት ሥርዓት ውስጥ መጨመራቸውን ይገልጣሉ ። አሁን ባሉን የግብረ ሕማማት ቅጅዎች የአቡነ ሰላማን ስም የሚያነሣው ከሊቃውንቱ ድርሳናት መጨረሻ ላይ የሆነውም ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ አቡነ ሰላማ መተርጉም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን አሰባስበው የትርጉም ሥራ ይሠሩ የነበሩት በደቡብ ጎንደር ስማዳ በምትገኘው ደብረ ዕንቁ ማርያም ነበር፡፡ አቡነ ሰላማ የግብጹን ግብረ ሕማማት ይዘውት የመጡ ይመስላል፡፡ በደብረ ዕንቁ የነበሩ ሊቃውንት መጽሐፉን መነሻ በማድረግና ከቀደመው የቤተክርስቲያን ጸሎት ጋር በማስማት አሁን የምናውቀውን ግብረ ሕማማት አዘጋጅተውልናል፡፡
እስካሁን ባሉን መረጃዎች ረጅም እድሜ ያስቆጠሩት የግብረ ሕማማት ቅጅዎች በ15ኛው መክዘ የተጻፉት ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ በኢትዮጵያ ማይክሮ ፊልም ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ (EMML 1765, 4434, 4752) EMML 1765 የሐይቅ እስጢፋኖስ ቅጅ ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ላይ ልዩ ልዩ ድርሳናትን የተረጎሙት አባ ሰላማ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ EMML 4434 የእንዳ ፍሬ ማርያም (ሞረት) ሲሆን EMML 4752 ደግሞ ሰሜን ሸዋ የሚገኘው የሙሽ ዜና ማርቆስ ንብረት ነው፡፡
በግብረ ሕማማት ውስጥ ከጾመ ድጓና ምዕራፍ የተወሰዱ ጸሎቶች መኖራቸው ፤ በግብጹ መጽሐፍ ላይ የሌሉ ከተአምረ ማርያምና ከተአምረ ኢየሱስ የሚነበቡ ምንባባት መገኘታቸው ፤ እንዲሁም የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቅርጽ ካልሆነ በቀር በብዛትና በዓይነት የተለዩ መሆናቸው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የመጽሐፉን መነሻ ከግብጽ ወስደው ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እንዲሆን አድርገው ማዘጋጀታቸውን እንደሚያሳይ የሚገልጡ አሉ፡፡ ለብዙ ዘመናት ግብረ ሕማማት በግእዝ ብቻ የሚገኝ መጽሐፍ ነበር፡፡ በሊቀ መዘምራን ላዕከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ (ዘአሰላ) ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ታትሟል፡፡
√ በግብረ ሕማማት ውስጥ ሦስት ነገሮች አሉ፡-
የመጀመሪያው ጸሎት ሲሆን ‹ዐማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም› እየተባለ የሚጸለየውና ካህናትና ምእመናን በየመካከሉ የሚደግሙት ዳዊት የዚሁ መገለጫ ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ ስግደት ነው፡፡ በመጀመሪያው ሰዓት፣ በሦስት፣ በስድስት፣ በዘጠኝና በ11 ሰዓት ከጸሎት ጋር የሚደረግ ስግደት አለ፡፡ በዕለተ ዓርብ ደግሞ የ12 ሰዓት ጸሎትና ስግደት አለው፡፡ ከግብረ ሕማማት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ሦስተኛው ክፍል ንባቡ ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት በመጽሐፈ ግብረ ሕማማት መሠረት የሚነበቡ ብዙ ምንባባት አሉ፡፡ እነዚህንም በአራት መድበን መመልከት እንችላለን፡፡
- መጽሐፍ ቅዱስ፡- በተለይም በዋናነት ከብሉይ ኪዳን ከኦሪት፣ ከጥበብ መጻሕፍት (ምሳሌ ፣ መኃልየ መኃልይ፣ ጥበበ ሰሎሞን፣ ሲራክ፣ ኢዮብ፣ ከመጽሐፈ ኢያሱ፣ ከመጽሐፈ ሩትና ከሌሎችም የሚቀርቡ ከሰሞኑ ጋር የሚሄዱ ምንባባት አሉ፡፡
- ትርጓሜ፡- የልዩ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትርጓሜ ይነበባል፡፡ በተለይ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያን ትርጓሜ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ከእርሱም ጋር የኤጲፋንዮስ፣ የአትናቴዎስ፣ የቄርሎስና የያዕቆብ ዘሥሩግ ትርጓሜያት ይሰማሉ፡፡
- ምዕዳን፡- በግብረ ሕማማት የክርስቲያንን ልዩ እሴቶች የሚመለከቱ ምክሮች ይቀርባሉ፡፡ ስለ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ወገንን መርዳት የተመለከቱ ምንባባት አሉ፡፡
- መጻሕፍተ ሊቃውንት፡- በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ከተዘጋጁና እምብዛም ከማናገኛቸው ድርሳናት መካከል በግብረ ሕማማት ውስጥ የምንሰማቸው አሉ፡፡ መጽሐፈ ዶርሖ፣ ላሃ ማርያም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ከተለመዱት ምንባባት ደግሞ ስንክሳር ፣ተአምረ ኢየሱስና ተአምረ ማርያም ይጠቀሳሉ፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ መጽሐፉ በአማርኛ የሚነበብ በመሆኑ ምእመናን ሁላችን በማስተዋል ብናዳምጥ በሌላ ጊዜ የማናገኛቸውን የቤተክርስቲያን ታሪኮች ፣ ምሥጢራትና ምንባባትን የምናዳምጥበት ዕድል ይሆናል፡
በቀሲስ ኢዩኤል ሰለሞን።

