
ሕማማት ከአለም አቀፋዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊቶች መሐል አንዱ ነው። አብዛኞቹ የምሥራቅም ሆነ የኦርየንታል አብያተክርስቲያናት ከኢትዮጵያና ከግብፅ አብያተክርስቲያናት የዘመን አቆጣጠር ጋር የሚመሳሰለውን የጁልያን የዘመን አቆጣጠር ስለሚከተሉ ሕማማቱን በተመሳሳይ ቀን በተቀራራቢ ሥርዓት ያከብሩታል። የሕማማት ሰሙን ስርዓት ዓለማቀፋዊነት ማሳያዎች መካከል በሰሙነ ህማማት ወቅት በምልጃ የሚጠሩ ዓለምአቀፋዊ ቅዱሳንና ወደ ግዕዝም ሆነ አማርኛ ያልተተረጎሙ ቃላት መገኘታቸው ነው።
እኒህ እንግዳ ቃላት የሦስት ጥንታዊ ቋንቋዎች ማለትም ቅብጥ፣ ግሪክና ዕብራይስጥ ቃላት ሲሆኑ በግብረ ሕማማት መጽሐፍ ትዕዛዝ በሚባለው ክፍል ውስጥ የሚገኙና በስግደት ወቅት ካህናትና ምዕመናን በምልልስና በቅብብል የሚሏቸው ውብ ቃላት ናቸው።
1. በአምስቱም ቀናት የምንጠቀምባቸው ቃላት
ከቅብጥ (ከግብፅ ቤተክርስቲያን ጥንታዊ ቋንቋ) የመጡ
ናይናን፡- የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ ፣ማረን» ማለት ነው፡፡ ቃሉ ከኢየሱስ፣ ክርስቶስ፣ አማኑኤል፣ እብኖዲ፣ ማስያስ፣ታኦስ፣ ትስቡጣ ተከትሎ የሚገባ ቃል ነው
እብኖዲ፡- የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው፡፡
ከጽርዕ (ከጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ) የመጡ
ኪርያላይሶን/ኪርዬኤሌይሶን:- «ኪርዬ» ማለት «እግዚነ»ማለት ሲሆን«ኤሌይሶን» ማለት ደግሞ «እግዚኦ-ማረን» ማለት ነው፡፡ ትርጉሙም «አቤቱ ማረን» ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ኪርያ ማለት እግዝእትነ/እመቤታችን ማለት ስለሆነ ሲጠራ «ኪርዬኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡
ታኦስ፡- «ጌታ ፣አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው
ትስቡጣ/ዴስፓታ:- ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው፡
ከዕብራይስጥ (ከአይሁድ ጥንታዊ ቋንቋ) የመጡ
ማስያስ፡- «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡
2. በዕለተ አርብ ብቻ የምንሰማቸው ቃላት
በዕለተ አርብ በስድስት ሰዓት ከወንጌልና የድህረ ወንጌል ንባባት በኋላ በቤተክርስቲያን ያሉ ሁሉ ቁጭ ብለው ሦስት ካህናት ጥቁር ለብሰው በዕዝል ዜማ የሚያዜሙት ዜማ አለ። ዐርፍተ ነገሮቹ የቅብጥ ሲሆን ትርጉማቸውም:-
አምነስቲ ቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ
ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ – አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ ማለት ነው፡፡
አምንስቲ ቲ ሙአግያ አንቲ ፋሲልያሱ
ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ – አቤቱ ቅዱሱ ሆይ በመንግስትህ አስበኝ፡ ማለት ነው።
አምንስቲ ቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ
ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን ማለት ነው፡

