ድንግል ማርያም ስለ ልጇ ስላለቀሰችው ለቅሶ


ወዳጆቼ ሆይ የአባቶቼ አለቃ የያዕቆብ ለቅሶ ዛሬ ታደሰ አለ። በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ለወለደችው ተወዳጅ ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? መከራ ስለተቀበለችበት ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? የድንግልና ጡቷን ላጠባችው ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? በቤተልሔም በበረት ለወለደችው ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? በማሕጸኗ ዘጠኝ ወር ለተሸከመችው ተወዳጅ ልጇ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስም? ከሃገር ሃገር አዝላው ለተሰደደችበት ልጇ ድንግል ማርያም ስለምን አታለቅስ? ከቶ መቃብራቸውን ስላላየችው ልጆቿ ራሄል የምታለቅስ ከሆነ በአንድ ልጇ መቃብር ደጃፍ ላይ ድንግል ማርያም ለምን አታለቅስ?


የባለ መልካም ስም ሽማግሌ የያዕቆብ ልቅሶ በብላቴናይቱ ድንግል ዛሬ ታደሰ። ወንድሞቹ ባሰሩት ጊዜ ያዕቆብ ወደ ዮሴፍ አልተመለከተም። ድንግል ግን ልጇ በእንጨት መስቀል ላይ ተቸንክሮ አየችው። ዮሴፍ በሰዲ ጉድጓድ ውስጥ ሳለ ያዕቆብ በላዩ እንዲያለቅስ ወደ ዮሴፍ አላየም። ድንግል ግን በአይሁድ ጉባኤ መካከል ተሰቅሎ ልጇን አየችው። ዮሴፍን ወንድሞቹ ልብሱን ሲያራቁቱት ያዕቆብ አላየም። ድንግል ግን በጎ ምክር በሌላቸው በአይሁድ መካከል ልብሱን ተገፎ ራቁቱን ሆኖ አየችው። ወንድሞቹ ዮሴፍን በሃያ ብር ሲሸጡት ያዕቆብ አላየም። ድንግል ግን ይሁዳ ልጇን በሰላሳ ብር ሲሸጠው አየች።አራዊት ባልቀደዱት ልብስና በሌላ ደም ላይ ያዕቆብ አለቀሰ። አምላካዊ ደም ግን ድንግል ማርያም ስለእርሱ በላዩ የምታለቅስበት በቀራንዮ አለት ላይ የፈሰሰው ነው። ድንግል ግን ዛሬ ያየችው ለልጇ ያለበሱትን ሌላ ልብስ ነበር የራሱን ልብስ ግን እርስ፡በእርሳቸው ተካፈሉት። የዮሴፍ ወንድሞች ወንድማቸው ዮሴፍን በሸሩት ጊዜ አለቀሱ ተጸጸቱ። የእስራኤል ልጆች ግን ጌታቸውን በሰቀሉት ጊዜ አላለቀሱም አልተጸጸቱም። የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው በነገሠ ጊዜ ተደሰቱ። አይሁድ ግን ጌታቸው ከሙታን ተለይቶ በተነሳ ጊዜ ደስ አላላቸውም።


ድንግል ሆይ በእውነት በልጅሽ መቃብር ላይ ልቅሶሽ ጣዕም ያለው አሳዛኝ ነበር።ማርያም ሆይ ለምን ተቀምጠሻል? ምን ታደርጊያለሽ ብለው የልጅሽን መሰቀሉን በነገሩሽ ጊዜ በመላእክት መካከል ቃልሽ ያማረ ነበር። እነሆ ልጅሽን በመኮንኑ ፊት አቁመውታል። የአይሑድ ሊቃነ ካህናትም ያሰቃዩታል። ያቃልሉታል። ማርያም ሆይ ምን ታደርጊያለሽ? እነሆ ልጅሽን በፍርድ አደባባይ መካከል ልብሱን ገፍፈው እያራቆቱት ነው።የኢያቄም ልጅ ማርያም ሆይ ለምን ተቀምጠሻል ምንስ ታደርጊያለሽ?እነሆ በኢየሩሳሌም ሜዳ የሚሰቀልበትን ግንድ ብቻውን ተሸክሟል። አንድስ እንኳን ወደ እርሱ የሚቀርብ የለም። የሃና ርግብ ሆይ ለምን ተቀመጥሽ? የምትሰሪውስ ምንድን ነው? እነሆ ልጅሽን ሰቅለውት በቀራንዮ ቦታ ቆሟል።የዳዊት ዘር ሆይ ልጅሽን በመስቀል ላይ ለምን ከፍ ከፍ አደረጉት?እመቤቴ ድንግል ሆይ በዮሐንስ ቤት ዛሬ ልቅሶሽ በእውነት ጣዕም ያለው ነበረ። እንዲህ ስትዪ ወዮ ለዚህ መራራ ወሬ ነጋሪ ለኢዮብና እስራኤል ለተባለ ያእቆብ ካረዷቸው መርዶ የመረረ ነው።ዛሬ ወደ እኔ ለሚመጣ ለዚህ ለክፉ ወሬ ወዮ ልጄ ሆይ ሃገሩን ባቃጠሉት ጊዜ ለሎጥ ካረዱት መርዶ ያስጨንቃል። በእኔ ላይ ለደረስው ለዚህ አስጨናቂ ነገር ወዮ ። ልጄ ሆይ ስለ ኃያላን እስራኤል ሞት ለዳዊት ካረዱት መርዶ ይበልጣል። በዚህ በክፉ ወሬ ወደ እኔ በመጣው ለዚህ ወሬ ነጋሪ ወዮ። ልጄ ሆይ እነሆ ስታረጋጋኝ ሠላሳ ዓመት ይሆናል።ልገስጽሕም አልተቻለኝም ዛሬ ወደእኔ ወሬህ እስከመጣ ድረስ ወጥተህ እስክትገባ አንዲትስ ሰዓት እንኳን አላመንኩም ።


ልጄ ሆይ ለሐዘኔ ሁሉ ምስክሬ ሰሎሜ ናት እኔ ዳኛውን አየው ዘንድ ከቤቴ አልወጣም፡ በፈራጁም ፊት አልቆምም ሌባውን ሲቆርጡት ሽፍታውንም ይገድሉት ዘንድ ሲፈርዱበት አላየሁም። ከቶ ቀራንዮን አላየሁትም። የጎልጎታን ቦታ አላውቀውም ሁልጊዜ በሚጣሉበት ቦታ አልቆምኩም። ልጄ ሆይ ክፉ የሆነ ፍርድ አላየሁም። በፍርድ አደባባይም ከቶ ለዘለዓለም አልቆምኩም ልጄ ሆይ ያደረግኩብህን ግፍ አላውቅም።

እኔም በዮሐንስ ቤት ነበርኩ። ወዳጄ ሆይ በሊቀ ካህናቱ በሃና ጊቢ የተቀበልከው ግፍ ወሬው መራራ ነው።ልጄ ወዳጄ ሆይ ዛሬ ከእኔ ላይ ነጻነቴን አስወገድኩ። ስለልደትህ በናዝሬት መልካም የምስራች ነገሩኝ ፡ ዛሬ ግን በኢየሩሳሌም ይህችን ክፉ መርዶ አረዱኝ ። በዮሴፍ ቤት መልካም ዜና ደረሰኝ፡ በዮሐንስ ቤት ግን የሞት ዜና መጣብኝ። ልጄ ወዳጄ ግን እኔ በልቤ ደስ እያለኝ ተቀምጬ ነበር ። በየዕለቱ ፋሲካ ደርሷል። በዓሉን እናከብር ዘንድ ወደ ቤታችን እንመለሳለን እያልኩ ነበር ። የዚህ አይነቱ አሽካም ደረሰኝ ። ልጄ ወዳጄ ሆይ በእንባና በሐዘን በዓሌ ወደ ለቅሶ ተመለስ። ፋሲካዬም ወደ ልብ ሐዘን።

ድንግልንም ልጇን ስላላየችው ፍጹም ሐዘንና ለቅሶ አገኛት። በዮሐንስ ቤትም ሳለች እንደገና ወደ ለቅሶዋ ተመልሳ ዮሐንስ ሆይ ወደ ቀራንዮ ትመራኝ ዘንድ እማጸንሃለሁ አለችው። ዮሐንስ ሆይ ከእኔ ጋር ወደ ጎልጎታ ትትሄድ እማጽንሐለሁ።ሌባውን ሲሰቅሉት ወንበዴን ቸብቸቦውን ሲቆርጡ አላየሁም እንደ ወንበዴ ልጄን ወዳጄን በውስጡ የሰቀሉበትን ቦታ አይ ዘንድ ሃገሬን ክብሬን ትቼ በእግሬ እሄዳለሁ።

ልጄ ሆይ ከወንድሞችህ አንድስ እንኳን አብሮ የቆመ የለም። ወይም ስላንተ አንድም ቃል የሚናገር የለም። ልጄ ሆይ በልጇ ላይ የእናት ሐዘን ሌላ ነው። ወዳጅም ስለ ወዳጁ የሚያዝነው ሌላ ነው። እናትም በተወዳጅ ልጇ ላይ ከልብ የምታዝነው ሐዘን ልዩ ነው። ወዳጅም በወዳጁ ልዩ ሐዘን አዝኖ ያለቅሳል ሐዘኔም በኢየሩሳሌም ካሉ ሰዎች ሁሉ ይጸናል።
ልጄ ወዳጄ ሆይ ልቅሶዬ በእኔ ዘንድ ከተሰበሰቡ ሰዎች ሁሉ ልቅሶ ይበልጣል። ዮሐንስም ከልቅሶና ከሐዘን መጽናናትን እንደማትችል፡ እርሱም ሊያረጋጋት እንደማይችል ባየ ጊዜ እርሷም ካላየሁት መጽናናት አልችልም እያለች ስለሆነ ዮሐንስም እኔ ካንቺ ጋር ወደ ቀራንዮ እሔዳለሁ ታዪው ዘንድ ተነሺ እንሒድ አላት። ድንግልም ከዮሐንስ ቤት ወጥታ በኢየሩሳሌም ሜዳዎች ውስጥ በእግሯ ተጓዘች። ድንግልንም ፈጥና ስትራመድ የሚያዩዋት ሰዎች እንዲህ የምታለቅስ ይህች ማናት አሉ። እርስ በእርሳቸውም ይነጋገሩ ነበር። ሌሎችም ከገበያ የምትሻውን ስትገዛ ከቶ ይህችን አላየናትም ይሉ ነበር። ሌሎችም እርስ በእርሳቸው ይህች እንግዳ ናት በሃገር ውስጥ ያለማስተዋል ትሄዳለችና ይሉ ነበር። የጌታ ኢየሱስ ደቀመዝሙር እንደሆነ ዮሐንስን የሚያውቁት እንጃ ይህችስ እናቱ ትሆናለች ። በመስቀል ተሰቅሎ ታየው ዘንድ ትሮጣለች ይሉ ነበር፡ ሌሎችም ይህች የዮሴፍ ሚስት ትሆናለች ስለልጇ ወሬ ነግረዋት ይሆናል ይሉ ነበር። ሌሎችም መልኳ ደም ግባቷ እንዴት ያምራል እዩ ይሉ ነበር።ሌሎችም በዚህ ሃገር ከቶ እንደዚህች አላየንም መልኳ የልጇን መልክ ይሉ ነበር። በገበያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለእርሷ ይነጋገሩ ነበር። ነገሩም በገበያ ሁሉ ተሰማ። ሰሎሜም በኋላዋ ትከተላት ነበር፡ ሌሎችም ሴቶች ራሳቸውን ተከናንበው ይከተሏት ነበር፡ በልብ ከማዘንም ምንም ወደቀኝም ወደግራ መለስ ቀለስ አትልም ነበርና።

ልመናዋ በረከቷ በሀገራችን በኢትዮጵያ በሕዝበ ክርስቲያኑም ላይ ለዘለዓለሙ አድሮ ይኑር። አሜን።