
በአንድ አጀንዳ ዙሪያ መመካከር የተለመደ ነው። ሰዎች በአንድ ግለሰብ ብቻ መወሰን በማይችሉ ጉዳዮች ላይ ይመለከታቸዋል ከሚሏቸው ሰዎች ጋር ይወያያሉ፣ ይወስናሉ። እነዚህ መሰባሰቦች ጉባኤ፣ ሸንጎ፣ ምክር ተብለው ይጠራሉ። በመዝሙረኛው ዳዊትም በሕብረት መቀመጥ ተብሎ ተጠርቷል።
ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ ነውና ምንም እንኳን በጉባኤ ተሰባስቦ መነጋገር ጠቃሚና ዘመን የጠገበ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልማድ ቢሆንም ጉባኤዎች ሁሉ ንጹሐንና ጠቃሚዎች አለመሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስና የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል።
የምክር ምልከታችንን ንጹሑን ዮሴፍን ለማጥፋት በመከረው የአስራ አንዱ ወንድሞች ታሪክ እንጀምር። የዘፍጥረት ጸሐፊው ሙሴ በ37ኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ስለዛች ምክር እንዲህ ብሎ ይጀምራል “እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ።”— ዘፍጥረት 37፥18 ለምክራቸው መነሻ የሆነው ዮሴፍ ያየው ህልም ነበር። ህልሙ የፈጠረባቸውን ቅናት መቆጣጠር ስላልቻሉ
በምክራቸው ላይ አንደኛው ወንድሙ እንግደለው ብሎ ሲነሳ ሌላኛው አይ በሕይወት ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው ሲል እናደምጣለን። የጉባኤው ሀሳብም የመጨረሻ ውጤት የዮሴፍ መሸጥና የያዕቆብ እንባ ነበር።
የዚሁ ምክር ተመሳሳዩን በሐዲስ ኪዳንም እናገኛለን። መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ አልአዛርን ከሞት ካስነሳው በኋላ የሰራቸውን ድንቆችና ተዓምራት የሰሙ አይሁድ ክርስቶስን ሊያስወግዱ ጉባኤ ሰሩ።
የብሉይ ኪዳኑ ምክረ ውሉደ ያዕቆብና የሐዲስ ኪዳኑ ምክረ አይሁድ መሐል የበዛ መመሳሰል እናያለን። በብሉይ ኪዳኑ ጉባኤ ዮሴፍ ላይ የተነሱበት ወገኖቹ ነበሩ። በሐዲስ ኪዳኑ ምክርም ላይ አይሁድ የተነሱት ለሙሴ ከወንድሞች መሐል እንዳንተ ያለን አስነሳለው ተብሎ በተነገረለት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር።
የብሉይ ኪዳኑ ምክር መነሻው ቅናት ነበር። እኛን ሊገዛና የበላያችን ሊሆን ይወዳል ብለው ነበር ለመግደል በኋላም ሀሳቡን አሻሽለው በባርነት ለመሸጥ የተስማሙት። የሐዲሱም ምክር ምንም እንኳን የሮማን የበላይነት ለማጽናትና የአይሁድን እምነትና ባህል ለመጠበቅ የሚል ሽፋን ቢኖረውም ትክክለኛው ምክንያቱ ግን ቅናት ነበር። ይሄም በጲላጦስ ዘንድ ጭምር የታወቀ እንደነበር ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ያነሳዋል። “በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።” ማቴዎስ 27፥18
የምክራቸው ሀሳብም ተመሳሳይ ነበር የተመቀኙትን ሰው እንዴት ማስወገድ እንዳለባቸው። በዮሴፍ ላይ የመከሩት ይገደል አይገደል በሚለው ሃሳብ ተከፋፍለው እንደነበረው ሁሉ በአይሁድም መካከል ይህ አይነት ክርክር እንደነበረና ሦስት ቀን እንደፈጀባቸው ዕለተ ረቡዕም የተስማሙበት ቀን መሆኑን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያነሱታል። ኢየሱስን የመሸጥ ሀሳብ በይሁዳ የቀረበውም ልክ እንደ ዮሴፍ መሸጥ ዘግየት ብሎ ነበር። ዮሴፍ ከጉባኤ ውጪ ላሉ ነጋዴዎች ሲሸጥ ኢየሱስ ግን ከጉባኤው ውጭ ባለ ሰው ለጉባኤተኞች ለድርድር ቀረበ። የዮሴፍ መሸጥ ከወንድሞቹ ምክር በኋላ እንደ መጣ ሁሉ ይሁዳም የመጣው ጉባኤው ከተበተነ ከሰዓታት በኋላ ነበር። ከእንግዲህ ባሮች አይደላችሁም ወንድሞች እንጂ ተብሎ የተነገረለት ይሁዳ ወንድሙ ይሆን ዘንድ በትህትና ራሱን ዝቅ ያደረገውን ክርስቶስ ሊሸጠው ከአይሁድ ጉባኤ መልስ ተገኘ።
ከደቀመዛሙርቱ መካከል አሳልፎ የሚሰጣቸው ሰው ይኖራል ብለው ለማይገምቱት አይሁድ የይሁዳ መምጣት ያልተጠበቀ ሆኖላቸው ነበር። “ሁከት እንዳይፈጠር በበዓል አንያዘው” ማቴ 26:5 ብለው ያሉት በስውር አሳልፎ የሚሰጣቸው ደቀ መዝሙር እንዳለ ስላላወቁ ነበር። “ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት” የሚለውም ቃል የይሁዳ መምጣት በአይሁድ ጉባኤ ያልተጠበቀ መሆኑን አመላካች ነበር።
የክፉዎች ምክር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ መሸጥ የሚያበቃ ብቻ አይደለም። “ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል።” ዮሐ 15፥20 ብሎ እንደተናገረው በክርስቶስ ላይ የመከሩ ጠላቶች በሐዋርያቱና በአርድእቱም ላይ ለመነሳት ከመምከር ወደ ኋላ አላሉም። ሐዋ 4:17፣ ሐዋ 9:23
የክፉዎች ምክር በዘመነ ሰማዕታትም ብዙ ሰማዕታትን በመከራ ውስጥ ለእግዚአብሔር ምስክር እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሄ የአይሁድና የአህዛብ በክፉ የመዶለት ጠባይ ታዲያ በኋላ ዘመን በተነሱና የኢየሱስ ክርስቶስ ስምን በሚጠሩ ነገር ግን የእርሱን የማይመስል ወንጌል በሚሰብኩ መናፍቃንም ጭምር መታየት ጀመረ። ይህንንም ከታሪክ ሁሉ ጎልቶ በሚታየውና ቅዱስ አባት ዲዮስቆሮስን ስለእውነት በብቸኝነት ባቆመው የኬልቄዶን ጉባኤም ላይ እንመለከተዋለን። አስቀድመው የቅዱሱ አባት ዲዮስቆሮስ ወንድም የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት የክርስቶስን የተዋሕዶ ስግው ቃልነት በመሰከረ ወንድማቸው ላይ ተነሱበት። በሀሰት ጉባኤያቸው አውግዘው ለዩት። ነገር ግን በዚህ ቁጣቸው ያልበረደላቸው መለካውያኑ ግን በዲዮስቆሮስ ላይ እጃቸውን አነሱበት ጥርሱን አርግፈው ጽሕሙን ሲነጩት እንኳን ለቀናኢ እምነቱ ለእርጅና ክብሩ እንኳን አልተጨነቁም ነበር።
እኒህንና ሌሎች መሰል ምክሮችን ለታሪክ እንተወውና ፈጣሪ አለማት ክርስቶስን ለማስወገድ ወደተመከረባት ወደዚህች ቀን እንመለስ። ይህች ቀን የክርስቶስን መሲሕነት የተገለጠባት ስለመሆኑ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11 ከቁጥር 49-52 እንዲህ ያነሳልናል
“በዚያችም ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው “እናንተስ ምንም አታውቁም። ምንም አትመክሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ህዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናል”
ይሄ ምንኛ የሚደንቅ ምስክርነት ነው? የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው እንዲሉ ለመግደል ከተሰበሰበ ጉባኤ ያውም ከሊቀ ካህኑ ይሄንን መስማት እንደምን ያስደምም። ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለዚህ ምስክርነት እንዲህ ይለናል
“…ይህንም ከልቡ የተነገረው አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ህዝቡ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ። ስለ ህዝቡ ብቻ አልነበረም የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ”
የመንፈስ ቅዱስን ስራ እዚህ ጋር እንመልከት ስምዖን ጴጥሮስ አንተ የህያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ያስመሰከረ መንፈስ ቅዱስ የካህናት አለቃው ቀያፋንም ልቡን አንቅቶ ፊቱን ፀፍቶ የእውነትን ቃል እንዲናገር አደረገው። ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሆኖ በመስቀል ላይ መስዋዕትነቱን እስኪፈጽም ድረስ ኦሪት አላለፈችም ነበርና በክፉ ተንኮል ሥራ ተጠምዶ በነበረው በቀያፋም አንደበት እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን የትንቢት ቃልን አኖረ። ይሄም ዛሬም ያሉ ካህናት ምንም እንኳን ኃጥእ ቢሆኑ ክህነታቸው እስኪሻር ድረስ እግዚአብሔር በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሥራውን የማያቋርጥ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
“የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል። በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።” መዝ 2:2-4
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሁኖ መከራን ተቀበለ። በመከራውም አዳነን።

