
ከዓመታት ወዲህ በሰሙነ ሕማማት ከቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ከማልገኝባቸው ቀናት መካከል አንደኛው ቅዳሴ የሚቀደስበት ሐሙስ ነው። ተጨባጭ የሆነ ምክንያት የለኝም፡ ግን በስራም፡ በስንፍናም እያመካኘሁ ሐሙስን አልገኝም። የሚገርመው ነገር የሕማማትን ሐሙስ ካስቀደስኩ ዘመናት እንደነጎዱ ያስተዋልኩት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ዛሬ ሰፈራችን በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ስላለሁ ነው። ወይ ጊዜ።
የዛሬን አያድርገውና…የዛሬን አያድርገውና …
እኔም በዕለተ ሐሙስ የተሰራው የምስጢረ ቁርባን ስርዓት ተሳታፊ ነበርኩኝ። ነጣ ያለ ሱሪዬን አጣጥቤ፡ ነጠላዬን አጣፍቼ “ስጋዬንም የበላ ደሜንም የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” የሚለውን ዝማሬ በለሆሳስ እያልኩ ወደ ቤተ ክርስቲያን የማቅናት ልምድ ነበረኝ።
አሑን አሑን ግን እንኳን ለስጋና ለደሙ ነጠላ እንኳን ለመልበስ እፈራለሁ። አንዳንድ ጊዜ አስባለሁ ፡ እኔንጃ ነውሬ የነጠላውን ነጭ ቀለም የሚያመነችክ ይመስለኝ ይሆን፡ እንጃ ብቻ።
ለምን ከስጋ ወደሙ ራቅክ? ለምን ንስሐ አትገባም? የዘለዓለም ሕይወትን ማግኘት አትፈልግም? ብለህ ብትጠይቀኝ ስጋ ወደሙ ለወጣቶች አልተፈቀደም የሚል ምላሽ አልሰጥህም። እንደውም በብዙ ለታመምን እኛ በብዙ የሚያድነው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስጋና ደም ምን ያህል እንደሚያስፈልገን በብዙ ማስረጃ ላስረዳህ እችላለሁ።
ታድያ ለምን ንስሐ የማልገባ ይመስልሃል? ይቅር ባይ መሆኑን አውቃለሁ። እንደ እርሱ አይነት መሐሪ ማን አለ? እኔም ሰው ተብዬ ደጁን ለመርገጥ ከመብቃቴ የበለጠ ለእርሱ መሐሪነት ማስረጃ የሚሆን ምን አለ? የይሁዳ ትልቁ ኃጢያት የዓለምን መድኃኒት በሠላሳ ዲናር ከመሸጡ የበለጠ አምላኩ ይቅር አይለኝም ብሎ ራሱን ማጥፋቱ እንደሆነስ መች ጠፍቶኝ።
የዘለዓለም ሕይወትን እንደሚያሰጥም አውቃለሁ። አምላኬ አማኑኤል የተናገረውን ቃል መቼ አጥፎ ያውቃል? “ስጋዬንም የበላ ደሜንም የጠጣ፡ የዘለዓለም ሕይወት አለው”ብሎ የተናገረውንስ እንዴት አላምንም። ለማስረዳት ጠይቁ ብሎ ጠይቄ ያገኘሁትን ወይስ ከልለኝ ብዬው የሰወረኝን ልዘርዝር?
ታዲያ ለምን አልቆርብም? ስንፍና፡ ትዕቢት፡ መሞትን መርሳት ፡ በድጋሚ እንጃ ብቻ።
አላውቅም።
ተጠየቅ – አምላክህ በመስቀል ተሰቅሎ በፍቅር አይኑ እያየ ስጋዬን ብሉና የዘለዓለም ሕይወትን አግኙ ሲል ፡ ከእርሱ መሸሽ ምን ይባላል? በትሕትና የሐዋርያቱን እግር ያጠበው አምላክ ንስሐ ብንገባ ከክፉ ስራችን ሁሉ ሊያነጻን፡ ሊያጥበን እንደ ማርያም እንተ ዕፍረት በደላችንን ሊረሳ ፡ አስበኝ እንዳለው ፊያታዊው ዘየማን ከእርሱ ጋር በገነት ሊያኖረን የሚወድድን አምላክ ስለምን ይሆን የምሸሸው ? የእናንተን አላውቅም። እኔ ግን ምን ሆኛለሁ? እስከመቼስ እንደዚህ እቀጥላለሁ? ራሴን እጠይቃለሁ?
ለምን… እስከ መቼ?

