
ዕለተ አርብ ለክርስቲያኖች ሁሉ የሕማም የመገረም የመደሰት እለት ናት። በዚህች ቀን ስለሰው ሁሉ ፍቅር ሰው የሆነው ክርስቶስ ሕማምን ተቀብሏልና ከእርሱ ጋር እየወደቁና እየተነሱ ከሊቀካህናቱ ጊቢ እስከ ሊጦስጥራና ቀራንዮ ድረስ አብረው ይታመማሉ።
በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለው ግን መታመም ብቻ አይደለም። መደመምም ጭምር እንጂ። “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” ዮሐ 15፥13 ብሎ ያስተማረ አምላክ የኃጢአተኛውን ሰውነት ገንዘብ ከማድረግ አልፎ ሊያድነው በመጣው ሰው ሕማምን ተቀብሎ በማዳን ስለገለጠው ፍቅር ይደነቃል። ከልበ አምላክ ዳዊት ቃል ተውሶ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጎበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? እያለ በፍፁም መገረም ይጠይቃል። ነገሩ በመገረም አያበቃም በተከፈለላቸው ዋጋ ያገኙትን ያቃሉና በፍፁም ደስታ ሆነው በመልክአ ሕማማቱ ስብሃት ለከ እያሉ ያመሰግናሉ።
በዚህ የታላቁ የፍቅር ቀን መደመማችንን ዘላለማዊው ፈራጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በአላፊ ጠፊ ፈራጆች ፊት በመቆሙ እንጀምር።
የእለተ አርብ የአይን ምስክር ወንጌላዊው ዮሐንስ እንደሚነግረን አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሊጦስጥራ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት ጲላጦስ የተሰኘው ሀገረ ገዢም ወደነሱ መጥቶ የዚህ ሰው በደሉ ምንድነው አላቸው እነርሱም “ክፉ ባይሆንስ ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነው ነበር” ብለው መለሱለት። ጲላጦስ ራሳቸው በህጋቸው እንዲወስኑ የፈለገ ቢሆንም እነርሱ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም ብለው እርሱ እንዲፈርድበት ግድ አሉት። በዚህ ሰዓት ጲላጦስ ክርስቶስን “የአይሁድ ንጉስ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። ክርስቶስ የጲላጦስ ጥያቄ ከራሱ ከጲላጦስ ወይም ከሌላ የመጣ መሆኑን በሚመረምር ጥያቄ መለሰለት። ጲላጦስ ጥያቄው ከአይሁድ የመጣ መሆኑን ሲነግረው ጌታችን ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” አለው። ጲላጦስ ግን መልሶ ጠየቀው “እንግዲያስ አንተ ንጉስ ነህ” ደግሞ ጠየቀው ኢየሱስም “እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” አለው። ጲላጦስ በዚህ ሰዓት ሁሉ ይጠይቀው ዘንድ የሚገባውን ጥያቄ ጠየቀው “እውነት ምንድነው?”
ይህ የጲላጦስ ጥያቄ መሠረታዊ ጥያቄ ነበር። ነገር ግን ጲላጦስ ጠይቆ መልስ እስኪያገኝ ድረስ አልታገሰም። በዚህ ሰው ላይ በደል አላገኘሁበትም ይል ዘንድ ወደ አይሁድ ሄደ እንጂ ቢታገስ ኖሮ እውነት ማለት ክርስቶስ መሆኑን ይረዳ ነበር። ጲላጦስ ግን መሰረታዊ ጥያቄ ጠይቆ መሠረታዊውን መልስ ለመስማት ጊዜ አጣ።
ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን የሰማው ጲላጦስ በወቅቱ በኢየሩሳሌም ወደ ነበረው የገሊላው ገዢ ወደ ሄሮድስ መላኩን ይነግረናል። በነቢዩ ኢሳያስ (ነበር53:7) እንደተተነበየው ሄሮድስም ጌታ ኢየሱስን በብዙ መንገድ ቢመረምረውም እንደሚታረድ በግ አንዳች አልመለሰለትም ነበር። በዚህም የአለሙን ሀጢአት የሚያስተሰርይ በግ ተብሎ በመጥምቁ ዮሐንስ የተነገረውን ቃል እውነተኝነት አስረገጠ።
ሄሮድስ በደል እንዳላገኘበት ገልፆ ለጲላጦስ ቢልክበትም ሚስቱ ስለእርሱ በህልም መሰቃየቷን መልዕክት በመላኳና ለሞት የሚያበቃው በደል ስላላገኘበት ሊፈታው ወዶ አብዝቶ ወንጀል ከሰራው ከበርባን ጋር ኢየሱስን ለምርጫ አቀረበው። ከዕፀ በለስና ከእፀ ሕይወት እፀ በለስን ያስመረጠው ሰይጣንም አይሁድን በሊቀ ካህናቶቻቸው አድሮ በርባንን አሰመረጣቸው።
ጲላጦስም ፀብ ክርክር እንጂ ምንም እንደሌለ አውቆ ክርስቶስን ገርፎ አሳልፎ ሰጣቸው። ከደሙ ነፃ ነኝ ብሎ እጁን ታጠበ። የይስሐቅን ምርቃትን ከወንድሙ ጋር የተሻማው የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን እርግማኑን ተሻሙ። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻቸውም ደሙን ተሻሙ። አስቀድሞ ይሁዳ ገንዘቡን ሲመልስ በኋላም ጲላጣስና ሄሮድስ የኢየሱስን ንፅህና ቢነግሯቸውም አይሁድ የተባባሪዎቻቸውን ቃል መስማትን እንኳን አሻፈረን አሉ።
ስለዚህች የፍርድ ሰዓት እንደመማለን እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ ያለውን አምላክ፣ ሂጅ አልፈርድብሽም ብሎ የታፈሩትን የፈታው ክርስቶስ ተፈረደበት። በዳግም ምፅዐቱ አለም ሁሉ በፍርድ ዙፋኑ ፊት የሚቆሙለት ክርስቶስ ተፈረደበት። ያውም የተከሳሽነት ከብር ተነፍጎት እየተዳፋና እየተደበደበ በፈራጆች ፊት ቆመ። አይሁድ ከሆሳዕና ጀምሮ ይጠይቁትና እንከን ይፈልጉበት ዘንድ ባቀረቡት በአንዱም ጥፋት ያልተገኘበትን፣ በፈራጆች ፊት ንፁህ መሆኑን የገለጠውን ክርስቶስ ስለህዝብ ጩኸት ብቻ ሲሉ ፈረዱበት። እውነት በድምፅ ብልጫ፣ ንፅህናም በጩኸት ተሸጠ።
ጠላቶቹን የሚወድ ክርስቶስ ግን በሞቱ የተለያዩትን ሰውና መላዕክት አንድ ለማድረግ በመጣበት በዚህች ዕለት ስለ እርሱ የተለያዩትን ሁሉ አንድ ያደርግ ነበር። አስቀድሞ በክስ ፈሪሳውያንንና ሰዱቃውያንን አንድ ያደረገ እርሱ ለፍርድ በፊታቸው ቆሞ ተጣልተው የነበሩትን ጲላጦስንና ሄሮድስን አስታረቃቸው። በሞት ላይ ይፈርድ ዘንድ፣ በሲኦል ላይ ይበይን ዘንድ ተፈረደበት።

