
የሮም ንጉሠ ነገሥት ከነበሩት ወላጆቹ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም አማላጅነት ተወልዶ ይስሐቅ የተባለው ፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ተምሮም ዲቁናን የተሾመውና በአባቱም ዙፋን ላይ በንግሥና በቅንነት እየገዛ ሰባት ዓመት የኖረው ቅዱስ መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወጥቶ ወደ ምንኩስና የሄደው በዋሻ በሚኖረው አባ ጰንጠሌዎን መልእክት ነበር። የሚገርመው በመንገዱ ላይ ጌታችን የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጦለት ብርሃናውያን በሆኑ ክንፎቹም ተሸክሞ የዐሥር ወር የሚሆነውን መንገድ በሦስት ሰዓት አስፈጽሞ በአባ ጰንጠሌዎንም ደጅ አቁሞታል።አባ ጰንጠሌዎንም ቅዱስ ይስሐቅን ተቀብሎ በበዓቱም አስገብቶ የምንኲስና ልብስን ካለበሰው በኋላ፡ ይስሐቅ በጾም በጸሎትና በስግደት ተጠምዶ ቆዳው ከዐፅሙ እስከሚጣበቅ ተጋድሏል።
ወደ መደራ ሄዶም በእግዚአብሔር ኃይል ድንቅና ተአምር እያደረገ በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማስወጣት ብዙ ዘመን ኖሯል። በአንዲት ዕለትም በጥዋት ሥንዴ ዘራ በሠርክም መሥዋትን አሳረገ። በማግሥቱም በግራር ዛፍ ላይ በሮችን አውጥቶ የሥንዴውን ነዶ አበራ የሰባ ሰባት የእንቅብ መስፈሪያም ሆነ። ሁለተኛም የወይን ሀረግ በአለት ላይ ተከለ ወዲያውም በቀለች አበበችና አፈራች በእርሷም መሥዋዕትን አሳረገ። አንዲት ቀንም ሲጽፍ መሸና ፀሐይ ሊጠልቅ በተቃረበ ጊዜ በቦታውም እንዲቆም በማዘዝ ጽሕፈቱንም እስኪጨርስ አቆመው። ምራቁንም ትፍ ባለበት ዘንድ ጠበል ፈልቆ እስከ ዛሬ ለበሽተኞች ፈውስ ሆኖ ይኖራል።
ታዲያ በአንዲት ዕለት ሰዎች ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው “ቀሲስ ይስሐቅ እኮ ከበላ በኋላ የቁርባን ቅዳሴ ቀደሰ” ብለው ነገሩት አባ ጰንጠሌዎንም ወደርሱ ሄዶ “ልጄ ይስሐቅ ሆይ ምሥጢር ስለ አለኝ ከአጠገባችን ሰዎችን አስገልል” አለው ይስሐቅም “ሰዎችን ተውና ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ይገለሉ” አለ። ወዲያውኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ሸሹ። አባ ጰንጠሌዎንም “ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ” አለ ስለዚህም ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ገሪማ ተባለ።
መልካም ተጋድሎንና የቀና አካሔዱን በፈፀመ ጊዜ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት “ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያው ለሚያደርግ፣ ገድሉንም ለሚጽፍና ለሚያጽፍ፣ ለሚያነበውና ለሚተረጉመው ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው ዳግመኛም “የተራበውን ላበላ፣ የተጠማውንም ላጠጣ እኔ የሕይወት እንጀራን እመግበዋለሁ የድኅነት ጽዋንም አጠጣዋለሁ” አለው። በቤተ ክርስቲያንህም በማኅሌት ያመሰገነውንና የጸለየውን እኔ የመላእክትን ምስጋና አሰማዋለሁ የተራቆተውንም ለሚያለብስ የብልህ እጅ ያልሠራው የብርሃን ግምጃን አለብሰዋለሁ ነፍሱም ከሥጋው በምትለይ ጊዜ የጨለማ መላእክት አይቀርቡትም። የብርሃን መላእክትም በዙሪያው አቆማቸዋለሁ። በስምህም ቤተ ክርስቲያን ለሠራ በሰማያት አርባ ሰባት የብርሃን ቦታዎችን እኔ እሰጠዋለሁ፣ ለቤተ ክርስቲያንህ መባ የሚሰጠውንም እኔ በመንግሥቴ እቀበለዋለሁ፣ ቦታህን የሚያከብረውንም እኔ በመንግሥቴ አከብረዋለሁ፣ ጠላቶች አጋንንትን ረግጦ የሚገዛበትንም እሰጠዋለሁ”። ብሎ ቃልኪዳን ገብቶለታል።
አባ ገሪማም “ይህን ታላቅ ሀብት በቸርነትህ ብዛት የሰጠኸኝ አቤቱ ስምህ ይክበር ይመስገን ግን ጌታዬ ሆይ መታሰቢያዬን ላደረገ፣ ገድሌንም ለጻፈ እስከ ስንት ትውልድ ትምርልኛለህ” አለ። መድኃኒታችንም “እስከ ዐሥራ ሁለት ትውልድ እምርረዋለሁ” ብሎታል። አባ ገሪማም መድኃኒታችንን “ልጆች ባይኖሩትስ ምን ታደርግለታለህ” ባለው ጊዜ መድኃኒታችንም “ዐሥራ ሁለት ዕጽፍ ክብር እሰጠዋለሁ” ብሎ መልሶለታል።
ዳግመኛም “የሞት ጥላ እንደማያገኝህ ታላቅ የምሥራች እነግርሃለሁ” አለውና ሰላምታ ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ቅዱስ አባ ገሪማም በልቡ ደስ ተሰኝቶ ሰኔ 17 ቀንም በብርሃን ሠረገላ ተነጥቆ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም አባ ገሪማ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


