በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
ጌታ ሆይ በበዓለ ሀምሳ ቅዱስ መንፈስህን ልከህ ሐዋርያትን አጽንተህ አንጽተህ ሰባ ሁለት ቋንቋዎችን ገልጸህ ከዓለም የተሰበሰቡ በጸሎት የተጉ ሦስት ሺሕ ሰዎችን ለራስህ መረጥክበት፡፡ በብሉይ ኪዳኑ በዓለ ኀምሳ ቀድሞ ከደረሰው እሸቱን መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቡልህ እንደምትቀበልበት ሥርዓት ዛሬም የሐዲስ ኪዳኗን ቤተ ክርስቲያን ሦስት ሺሕ ምእመናን ለራስህ እሸት አድርገህ ተቀበልክ፡፡
እነዚያ ሰዎች በእውነት ምንኛ የታደሉ ናቸው፡፡ ከእነርሱ ቀጥሎ የሰማዕታትን አዝመራ ልታጭድ፤ የጻድቃንንም ሰብል በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያ አለ ባልከው ቦታ ልትሰበስብ፣ የሊቃውንትንም ነዶ በዐውደ ምሕረት አደባባይህ ልታከማች፣ የንጹሐን ምእመናንን ክምርም በዐውድማሕ ልትከምር መሆኑን ዛሬ በተቀበልካቸው ቀድመው በደረሱ እሸቶችህ አሳወቅኸን፡፡ ገና ሳይሰበክ ያመኑ፣ ገዳማት ሳይመሠረቱ በጸሎት የተጉ፣ ሐዋርያት ወደ እንኳን ወደ ዐለም ወደ እሥራኤል ቤት ሳይወጡ እነዚህ ከዓለም ሁሉ መጥተው ቀድመው የተሰበሰቡ ምንኛ የተመረጡ ናቸው፡፡ በሐዋርያት የወረደውን መንፈስህን አይተው ያደነቁ፣ አይሁድ ሐዋርያትን በጉሽ የወይን ጠጅ ሰክረዋል ሲሉ ሰምተው ያልደነገጡ፣ ቋንቋቻቸውን ሰምተው ጸጋህን የተረዱ፣ በዚች ቀን ተጠምቀው የመጀመሪያዋን ቅድስት ጉባኤ የመሠረቱት እነዚህ አማንያን በእውነት ምንኛ የተመረጡ ናቸው፡፡ በርግጥም ከሐዋርያት ስብከት በፊት የደረሱ እውነተኛ የመንፈስ ቅዱስ እሸቶች፡፡
ጌታ ሆይ እኔ ግን እንኳን ከሰው ከዓለም ቀድሜ ለፍሬ ለእሸትነት መሥዋዕት ልደርስ ከአዝመራውም የምገኝ አይመሰለኝም፡፡ ነገር ግን ቸርነትህን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በቃርሚያ ለቃሚ እንኳ ሰብሰብህ ለትንሽ ዐውድማህ እንድታበቃኝ እለምንሃለሁ፡፡ አዎን እኔ ለጽድቅ አዝመራ አጫጆች ለእጃቸው የማልጨበጥ፣ ለዐይናቸው የማልገባ ቃርሚያ እንኳን ከሆንኩ ትልቅ እድል ነው፤ ሩትን ልክህ እንደምትሰበስበን አውቃለሁና፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ ገበሬዎች ሐዋርያት በአንድ ቀን እንዳደረሷቸው ለእሸት መሥዋዕት ዛሬ እንደቀረቡልህ ሦስት ሺሕ ትጉኃን ምእመናን አድርገህ ተቀበለኝ አልልህም፤ ነገር ግን ገበሬዎች ባይሰበስቧቸውም እንደ ሩት ያሉ የተናቁ ግፉዓን ከሚለቅሟቸው ቃርሚያዎች አንዱ መሆንን ግን አትንፈገኝ፡፡
ጌታ ሆይ በዕለተ በዓለ ኀምሳ ትጓሃኑ ምእመናን እያዩት የወረደውን በእሳት ላንቃ አምሳል የሚወርድ ስጦታህን አልጠይቅህም፤ በእኔ ላይ የሰለጠነውን የዓለምን መንፈስ እንድታርቅልኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ በሰባ ሁለት ወይም በርከት ያሉ ቋንቋዎችን መናገርን እንድትሰጠኝም እኔ አልጠይቅህም፣ በምሰማቸው ቋንቋዎች መልካሙን መስማትና ማስተዋልን እንድትሰጠኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ በቋንቋ ዐለምን ለማገልግል አልጠይቅህም፣ በቋንቋ ምክንያት እንዳልጠፋና ሌሎችንም እንዳላጠፋ፤ የሌሎችን ቋንቋ እንዳልጠላ፣ ቋንቋዬን ጠሉ ብዬም ሰዎችን እንዳልጠላ ትረዳኝና ልቡናዬንም ትጠብቅልኝ ዘንድ ግን በእውነት እለምንሃለሁ፡፡ አቤቱ ባለብዙ ቋንቋዎችን አንድ ማድረገን ባልችል በቋንቋቸው ምክንያት መከፋፈልና መለያየትን ማምጣትን ግን ከእኔ ፈጽመህ አስወግድልኝ፡፡
አምላኬ ሆይ ዛሬ እንደ ሐዋርያትህ በመንፈስ ቅዱስ ልሞላ አልልህም፤ ለእኔ በውስጤ የሞላውን ቆሻሻ ካስወገድክልኝ በእጅጉ ይበቃኛል፡፡ የእሳት ላንቃዎች ይውረዱብኝ አልልህም፤ ከውስጤ እየጨሰ የሚወጣውን የንዴት፣ የብስጭትና የስድብ እሳት ካበረድክልኝ ይበቃኛል፡፡ በቅዱስ ያዕቆብ አድረህ “እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል” /ያዕ 3 ፤ 5 – 6/ ስትል የገለጽከውን የሚያቃጥለኝን ጎጅ እሳቴን ካጠፋህልኝ ነፍሴ ትልቅ ዕረፍት ታገኛለች። እንደ ሐዋርያት በመንፈስ ሆኖ ጥበብን መናገርንም ዛሬ አልተይቅህም፡፡ ሳላውቀው መንፈስ ቅዱስን ከመስደብ እንድትጠብቀኝ፤ ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ ኃጢአትን ሊያስተሠርዩ በተሾሙ ላይ አፌን ከመክፈት በእነርሱ ያደረ መንፈስ ቅዱስንም ከመስደብ እንድትጠብቀኝ ግን እለምሃለሁ፡፡
በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ልሰከር አልልህም፤ በነገር ከመስከር፣ በስሜት ከመናጥ አውጥተህ በመንፈስና በእውነት ከሚያመልኩህ እንድትደምረኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ ነቢይ ኤልሣዕ በሰማርያ ሆኖ በሶርያ የሚመከረውን ያውቅ እንደነበረ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታህ በዓለም ያለውን የተሰወረውን ሁሉ ልወቅ አልልህም፡፡ “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” / ዮሐ 16 ፤ 13/ ባልከው ቃል ኪዳን መሠረት በስምህ ከሚያጨበረብሩት ጠብቀህ ወደ እውነት ብቻ እንድትመራኝ ግን እለምነሃለሁ፡፡
ጌታ ሆይ ከጥፋት ጎዳና ከመልሰከኝ ለእኔ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ እንደ አይሁድ ካለ ሥጋዊ ቅንዓት አውጥተህ እንደ ዳዊት ወዳለ መንፈሳዊ ቅንዓት አድርሰኝ፡፡ ከሐዋርያትህ ጋር ቆሜ እንደ ሲሞን መሠርይ ባለ የስህተት መንገድ መንፈስህንና ጸጋህን ከመመኘትና በዚያም ከሚመጣ ርግማን ጠብቀኝ /ሐዋ 5፣/፡፡ ይልቁንም ቤተ መቅደስ ተጠርተው መገኘት ባይችሉም በቤታቸው ሳሉ ልባቸውን አይተህ ጸጋህን እንደ ሰጠሃቸው እንደ ኤልዳድንና እንደ ሞዳድ /ዘኍ 11 ፤ 26/ የመሆንን የትሕትና መንፈስ አድለኝ፡፡ ጌታ ሆይ እንደ ይሁዳ ኖሬ ኖሬ መጨረሻ ላይ ከመውጣት ጠብቀኝ፡፡ ይልቁንም እንደ ፈያታዊ ዘየማን ባለቀች የጭነቅ ሰዓት እንኳ ልቤን ለንስሐ አንቃልኝ ፡፡ ጌታዬ ሆይ ለአገልግሎትህና ለተልእኮ በወጣሁበት እንደ ዴማስ መንገድ ላይ ከመጥፋት አድነኝ፣ ይልቁንም እንደ ጳውሎስ ለጥፋት ከምፈጥንበት ጎዳና መልሰህ ከመንጋህ ደርበኝ እንጂ፡፡ በታላቅ ነቢይ ቀብተህ አክብረኸው ሳለ ለሥጋውና ለጠቅሙ ቀንቶ እንደናቅኸው እንደ ሳዖል ከመሆን ጠብቀኝ፤ ይልቁንም ሚስቱ ሜልኮል እስክትስቅበት ድረስ ራሱን ጥሎ ለክብርህ ብሎ በተራው ሕዝብ ፊት እንደ ዘፈነው እንደ ዳዊት የማስተዋልን መንፈስ አድለኝ፡፡
ጌታ ሆይ እኔ በመንፈስ ሆኜ መናገርን ዛሬ አልጠይቅህም፤ በመንፈስ ሆኜ ስለኃጢአቴ ማዘንን እንድትሰጠኝ ግን እለምንሃለሁ፡፡ ጌታ ሆይ እንደ ሕዝቅኤል እንደ ነቢያትም ሁሉ መንፈስህ መጥቶ ይዳስሰኝ፣ ቀጥ አድርጎም ያቁመኝ አልልህም /ሕዝ 3 ፤ 12/፡፡ የዳዊትን ቃል ተውሼ ግን አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ” እልሃለሁ /መዝ 50፤ 1-2/፡፡ እንደ እስጢፋኖስ አድርገህ መንፈስ ቅዱስን ሙላብኝም አልልህም፡፡ ነገር ግን በተነሳሂው በዳዊት ቃል “ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” እልሃለሁ መዝ 50 ፤ 11/።
ጌታ ሆይ ብዙ ነገር እየዘረዘርኩ ዛሬ ብዙ ስጦታ አልጠይቅህም፡፡ የምጠይቅህ አንድ ነገር ነው፤ በእውነት ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ፡፡ “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። 4 አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ” መዝ 51 ፤ 2 – 3/። “ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ” /መዝ 19፥12/ ። “አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ” /መዝ
25 ፤ 11/። “አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና / መዝ 39፥12/። “እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ” /መዝ 69፥29/። “አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ። የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና። አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና። አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ” /መዝ 86 ፤ 3 – 6/ ። “በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ” /መዝ 51 ፤ 7 – 12/። ጌታ ሆይ በሐዋርያትህ ላይ ባወረድከው፣ በቤተ ክርሰቲያንህ አድሮ በሚኖረው፣ እስከ ዕለተ ምጽአት ከወዳጆችህ በማይለየው በቅዱስ መንፈስህ አኔን አንጻኝ፤ አሜን፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሳችሁ፣ አደረሰን፡፡
ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
እግዚአብሔር ምስሌነ
@EMislene

