አካልና ጥላ : መግቢያ

“እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።”
ቆላ 2፥17

ሐዋርያው ቅዱስ ጳወሎስ በታናሿ እስያ ለሚገኙ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ላይ መገረዝ በጥምቀት እንደተተካ በተናገረበት አንቀፁ፡ ስለ በዓላትም ያነሳና የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች፣ ሥርዓቶች በሙሉ ሊመጣ ያለው የክርስቶስ ጥላ እንደሆኑ ያነሳል።

በእርግጥም የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ እንደውሃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ ካለምንም በድንገት ብቅ ያለ አይደለም። መምህራችን ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት ያስተማሯቸው ትምህርቶች አስቀድሞ  ለከበሩ አባቶች ለእነ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከተገለጠው እውነት ጋር የሚስማሙ እንጂ እንግዳ ትምህርቶች አልነበሩም። በዚህም ምክንያት ከእነሱ ጋር ሊከራከሩ የወደዱ አይሁዶችን ከመጽሐፋቸው በመጥቀስ ዝም ያሰኟቸው ነበር። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው “ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።” ማቴ 22፥29 ብሎ የተናገረው ለዚሁ ነው።

በመሆኑም ኦርቶዶክሳዊው የነገረ ሃይማኖት መረዳት አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚጓዝ ሳይሆን የብሉይ ኪዳን ጽሁፎችን ከሐዲስ ኪዳኑ ጋር እያስማሙ በኅሊና አበው የመጓዝ ጥበብ ነው።

የብሉይ ኪዳን አስፈላጊነት ብዙዎች እንደሚያነሱት የሥነ ፍጥረት ትረካን ለመረዳት፣ የቀደሙ አበውን ለማወቅ፣ የእግዚአብሔርን ጠብቆት ለመረዳት ብቻ አይደለም በእርግጥ ገፀ ንባቡ የሚነግረን ይሄን ቢሆንም በውስጡ እጅግ ድንቅ የሆነ የነገረ ድኅነት ሃሳቦችን ይዞ ይነሳል።

በሥነፍጥረት በአዳም አፈጣጠር ውስጥ ካለው የዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ሥጋ መሆን ጀምሮ፣ በአቤል ደም፣ በኖህ መርከብ፣ በይስሐቅ መሰዋት፣ በሙሴ መነሳት ወዘተ ሥጋዌውን በብዙ ምሳሌያት ይናገራል። በምሳሌ ብቻም ግን አይደለም በዘመናት ባናገራቸው ነብያት በኩል አይተው የጻፉት በሚመስል ልክ ይመጣ ያለውን መሲህ ክርስቶስን ይተርኩታል። ወንጌላውያኑም የክርስቶስ ኢየሱስን ሥጋዌ በዘገቡባቸው ሥፍራዎች ላይ በነቢይም / በመጽሐፍም እንደተናገረው ሲሉ የሚያነሱት ይሄንን ነው። ይሄ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መገናዘብ ግን በግላዊ መረዳት የሚደረስበት አይደለም። ይልቁንም ከቀደሙ የቤተክርስቲያን አባቶች ጋር በሚስማማ አንድ ልብ እንጂ።

እርሱም ሐዋርያው እንደሚለው ሁሉን አንድ            የሚያደርግ የክርስቶስ ልብ ነው (1ኛ ቆሮ 2:16) በመሆኑም ይህ የክርስቶስ ልብ (ሃሳብ) ደግሞ በብቸኝነት የሚገኘው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነውና ከቀደሙት አባቶች ጋር በትርጓሜና በጸሎት መተባበርን ይጠይቃል። ምክንያቱም አርዮስን ጨምሮ ብዙዎች የብሉይ ኪዳንን ገፀ ንባብ በገዛ ፍላጎታቸው ልክ በመተርጓማቸው ከክርስቶስ አንድነት እንዲለዩ ሆነዋል።

በመሆኑም በዚህ አምዳችን በየሳምንቱ አርብ እነዚህን የብሉይ ኪዳን ሀሳቦች እንዴት ሊመጣ ላለው አካል ክርስቶስ ጥላ እንደሆኑ እንመለከታለን። የአምዱ አላማ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብቻ ባለመሆኑ በውስጡ ነገረ ሃይማኖት፣ ነገረ ክርስቶስ፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ድህነት፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ነገረ አበውና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ይዳሰሱበታል።

አምዱ ዘወትር አርብ የመሆኑ ምሥጢር በዕለተ አርብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ወደተናገራቸው ቃላት ይወስደናል። በዚህች ዕለት ከተናገራቸው ቃላት መካከል በዮሐንስ ወንጌል የተዘገበው የመጨረሻው ቃል “ተፈፀመ”  ነው። የቤተክርስቲያን መተርጉማን ይሄን ሲተረጉሙ ከሚያነሷቸው ትርጓሜዎች አንዱ “ከፅንሰቱ እስከ ስቅለቱ ድረስ በኦሪትና በነብያት የተነገሩት ሁሉ ተፈጽመዋልና ተፈፀመ አለ” የሚል ነው።  በመሆኑም ብሉይ ኪዳናዊው ድንግዝግዝ ጥላ ወለል ብሎ በተገለጠበት በዕለተ አርብ በማዕከለ ዘመን ላይ ቆመን ወደፊትና ወደ ኋላ እንጓዛለን።

ቀጣይ ሳምንት 👉 “ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁም ? 1ቆሮ 11:15 “

ይቆየን