ቤተክርስቲያን ምንድን ነው? /የቃሉ ትርጉም/

ብዙዎች ቤተክርስቲያን ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው የአድባራትና የገዳማት ህንፃ ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያን ማን ናት ተብሎ ለሚጠየቀው ጥያቄ እያንዳንዱ ክርስቲያን ምዕመንን ብሎ የሚመልስም አይጠፋም።  በእርግጥም ከቤተክርስቲያን ትርጓሜ ስፋት አንፃር እነዚህ ሁለቱም መልሶች ትክክል ናቸው። ነገር ግን ለህንፃውም ሆነ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያንነት መሠረቱ ግን በክርስቶስ ራስነት ውስጥ ያለው የአማንያን ሕብረት፣ መሰባሰብ፣ ወገን ወይም ጉባኤን ነው።ቤተ ክርስቲያን የሚለው የግእዝ ቃል የሚነግረንም ይሄ ነው። በሀገራችን የሚኖሩ አይሁድን ቤተ አይሁድ፣ ቤተ እስራኤል እንደምንለው ቤተ ክርስቲያንም የክርስቲያን ህብረት፣ የክርስቲያን ጉባኤ፣ የክርስቲያን ወገን (ዘር) ማለት ነው።መጽሐፍ ቅዱስ በተፃፈባቸው ጥንታውያን የዕብራይስጥና የግሪክ (ጽርዕ) ቋንቋዎችም የቤተክርስቲያን አቻ ትርጉሞች የሚያሳዩት ይሄንኑ ነው።

በዕብራይስጥ ቋንቋ ሁለት ቃላት ቤተክርስቲያን የሚለውን ቃል የሚተኩ ሲሆን አንደኛው “עֵדָה” (አይ’ዳው) ሲሆን መሰባሰብ፣ ጉባኤ፣ ቤተሰብ ወይም ሕብረት ማለት ነው። ሁለተኛውም የዕብራይስጡ ቃል “קָהַל” (ቃ’ዋል) ተመሳሳይ ትርጓሜ አለው። የግሪኩ ἐκκλησία (አቅሌሲያ)ም በተመሳሳይ መሰብሰብን፣ ጉባኤንና ህብረትን አመላካች ነው።κυριακός (ኩሪ’ያኮስ) የሚለው የግሪክ ቃል ደግሞ በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ከአቅሌሲያ ጋር በትይዩ ያገለግል የነበረ ቃል ሲሆን የጌታ ቤት፣ የክርስቲያኖች ቤት የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ዛሬ ላይ ለምንጠቀመው የግእዙ ቤተ ክርስቲያን ወይም ለእንግሊዘኛው CHURCH መነሻ ቃል እንደሆነ ይታመናል።

ከላይ ለማየት እንደምንችለው የዕብራይስጡም፣ የግሪኩም፣ የግእዙም ሆነ የእንግሊዝኛው ስም በብዛት ትኩረት የሚያደርጉት ከሦስቱ የቤተክርስቲያን ትርጓሜዎች (ከህንፃው፣ ከእያንዳንዱ ምዕመንና ሕብረቱ) ላይ ነው። የዚህ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱን ማለትም የእያንዳንዱ ክርስቲያን ቤተክርስቲያንነትና የህንፃው ቤተክርስቲያንነት የሚመነጨው በክርስቶስ ራስነት በተሰበሰቡ የምዕመናን ህብረት በመሆኑ ነው። አንድ ምዕመን በጥምቀት በሚገኝ ልጅነት ከቤተክርስቲያን ሕብረት ጋር እስካልተዋሃደና የሕብረቱ አካል እስካልሆነ ድረስ ቤተክርስቲያን መሆን አይችልም በተመሳሳይም አንድ ህንፃ ቤተክርስቲያን ለመባል የክርስቲያኖች ሕብረት የሚሰባሰብበትና በአንድነት ቅዱስ ምሥጢራትን የሚፈጽሙበት ሊሆን ይገባል።

/እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ በቀጣዩ ሳምንት የቤተክርስቲያንን ምንነት ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሊቃውንት አንፃር እንዳስሳለን/ ይቆየን።