
ኢያቄምና ሐና ቃል ኪዳናቸውን ለመፈጸም ዘመዶቻቸውን ባልንጀሮቻቸውን ከነልጆቻቸው በመጥራት፣ ሕፃን ልጃቸውን እመቤታችንን ልዩና ንጹሕ ልብስን አልብሰው በመንፈሳዊ ዝማሬ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ መብራትን በእጆቻቸው ይዘው እያበሩ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ወሰዷት። ያን ጊዜም ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ በካህናቱ ታጅቦ የምስጋና ዝማሬን ከልኡካኑ ጋር እያሰማ እነርሱን ለመገናኘት ከመቅደስ ወጣ።በዚያም ሊቀ ካህናቱ ብቻ ወደሚገባበት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚያስወጡ ፲፭ ደረጃዎች ሲኖሩ በየደረጃዎቹም መዝሙረ ዳዊት ተደጋግሞ ሲደረስባቸው ከሚጸለዩት የዳዊት መዝሙራት መካከል መዝ ፻፲፰(፻፲፱)፣ ፻፴፪ (፻፴፫) የሚገኙ ሲኾኑ እነዚኽንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አጥኚዎች “Psalms of Ascent” (የመውጣት መዝሙራት) ይሏቸዋል::
እናትና አባቷም ሊቀ ካህናቱን ካለበት ቅዱስ ቦታ ወደነርሱ እስኪመጣ ለመቆየት ልጃቸው ማርያምን ከአንደኛው ደረጃ ላይ ቢያኖሯትም እርሷ ግን በድንቅ አምላካዊ ሥራ መንፈሳዊ ኀይልን ተመልታ የሦስት ዓመቷ እመቤታችን ያለምንም ረዳት ብቻዋን ደረጃዎቹን በመውጣት በእጅጉን ወደተቀደሰው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ወዳለበት ስፍራ ኼደች ርሱም በእጅጉ ተደንቆ ባረካት።
ያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለሊቀ ካህናቱ የሰው ዘርን በመላ ወደ ገነት የሚያስገባ፣ ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት የእግዚአብሔር ልጅን የምትወልደው እርሷ እንደኾነች ገለጸለት። ቦታዋም በጣም የተቀደሰውና እርሱ መሥዋዕት ለማቅረብ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገባበ፣ ከእርሱ በቀር ማንም ሰው የማይገባበት፣ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ መኾኑን ገልጾለታል ፡፡ እርሱም ይኽንን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራን በማድነቅ፣ ይኽቺን የመሰለች ልጅ ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምንስ እናጠጣታለን? ምን እናነጥፍላታለን? ብሎ ሲጨነቅ ለእስራኤል ደመና ጋርዶ መናን አውርዶ የመገበ፣ ለኤልያስም በመልአኩ እጅ በመሶበ ወርቅ ኅብስት የመገበ፣ ለእዝራ ሱቱኤልም በመልአኩ በቅዱስ ዑራኤል እጅ መልኩ እሳት የሚመስል ጽዋዐ ልቡና ያጠጣው ልዑል እግዚአብሔር ለእናትነት ወደ መረጣት ወደ እናቱ መልአኩ ፋኑኤልን ላከላት። (ዘፀ ፲፮፥፴፩፣ ፩ ነገ ፲፱፥፮፣ ዕዝ. ሱቱ. ፲፫፥፴፰-፵፩)
ከዚያም “ወሶቤሃ ወረደ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት ወጸለላ በአክናፊሁ ወተለዐለ ላዕለ መጠነ ቆመ ብእሲ ወወሀባ ወመጠዋ ወዐርገ ውስተ ሰማይ” ይላል።” / “በዚያን ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊን በብርሃን ጽዋዕ፣ ስቴ ሕይወትን ይዞ ረብቦ በመውረድ አንድ ክንፉን አንጥፎ፣ አንዱን ክንፉን አጎናጽፎ፣ ከመሬት የሰው ቁመት ያኽል ከፍ አድርጓት፣ ኅብስቱን መግቧት፣ ጽዋውን አጠጥቷት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ስላዩትና ስለተደረገው ነገር ኹሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አማናዊት የአምላክ መቅደስ፣ የአካላዊ ቃል ታቦት እመቤታችንን ምሳሌዋ ወደሚኾነው ቤተ መቅደስ ታኅሣሥ ፫ በሦስት ዓመቷ አስገብተዋታል። ከዚያም ኢያቄምና ሐና ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡የቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ መቅደስ ሕይወት በእጅጉ አስደናቂ ሲኾን የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ትውፊት (Holy Tradition) እንደሚያስረዳን ቤተ መቅደስ በኖረችባቸው ፲፪ ዓመታት የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለቤተ መቅደስ የሚያስፈልገውን ነገር በእጆቿ እየሠራች በፍጹም ንጽሕና እና ቅድስና ኾና እግዚአብሔርን በማመስገን መላእክት እያገለገሏት ኖራለች፡፡ ይኽነን በቤተ መቅደስ የነበራትን ቆይታ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በጥልቀት ጽፈዋል። እነሆ የሊቃውንቱ ቃል፦አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማኅሌተ ጽጌ
“ማርያም የሐናን ወተት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ብቸኝነት ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚመላለስ ደመናን የሚረግጥ የእሳት አበባ ፋኑኤል ከጓደኞቹ መላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በንጽሕና የማደግሽ ተአምር ደስ ያሰኘኛል።”
“በዐረብና በተርሴስ ወርቅ እንዳጌጠች ታቦት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ያጌጥሽ ማርያም ቀንሞስ፣ ቀናንሞስ የሚባሉ ሽቱዎች ኢያቄምና ሐና ለጳጦስ ምሳሌ የኾንሽ አንቺን ከአስገኙሽ ዘንድ በሦስት ዓመት በቤተ መቅደስ የመኖር ተአምርን አሳየሽ።”
ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ። ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን ነው እንጂ። ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ። ድንግል ሆይ ከአንቺ አስቀድሞ ከአንቺም በኋላ እንዳሉ ሴቶች መተዳደፍን የምታውቂ አይደለም፤ በንጽሕና በቅድስና ያጌጥሽ ነሽ እንጂ። ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም፤ የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፤ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ።”
በ፭፻፭ (505) ዓ.ም. የተወለደው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን: “ከንጹሓን ይልቅ ንጽሕት የኾንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ ዕንጨት እንደተሠራ፣ በወርቅ እንደተጌጠና ዋጋው ብዙ በኾነ በሚያበራ ዕንቊ እንደተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ። እንዲኽ ኾነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ፤ መላእክት ዘወትር ምግብሽን ያመጡ ነበር፤ መላእክት እየጐበኙሽ እንዲኽ ዐሥራ ኹለት ዓመት ኖርሽ፤ መጠጥሽም የሕይወት መጠጥ ነበር፤ ምግብሽም የሰማይ ኅብስት ነበር።” “መላእክት እመቤታችንን እኅታችን ይሏታል። በክንፋቸው ይጋርዷታል፤ በማር ወለላ የተመሰለ የእግዚአብሔር ቃል ከከንፈሮቿ ይፈስሳል፤ ጒንጮቿ እንደ ሮማን ቅርፍት ናቸው። ልዑል ወደዳት፣ ዳዊት በመዝሙሩ አመሰገናት፣ በቤተ መቅደስ ተቀበሏት።” ቅዱስ ያሬድ (መጽሐፈ ድጓ) ጌታ የመረጠሽ ማርያም ሆይ ለምኚልን። ዕፀ ጳጦስ ተብላ የተጠራችውን እመቤታችን ዘካርያስ በቤተ መቅደስ ተቀበላት። ኹላቸውም ቅዱሳን ዐዲሲቱ እንቦሳ ይሏታል።በዓሉን የረድኤት የበረከት ያድርግልን!
፩. ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣
፪. ነገረ ማርያም በሊቃውንት ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ። ኢንኅድግ ማኅበረነ እግዚአብሔር ምስሌነ!

