
ምጽዋት ማለት ስጦታ፣ችሮታ፣ ልግስና ማለት ነው፡፡ ሰዎች በሰዎች ላይ የሚያዩትን ችግር በማገናዘብ የተቸገሩትን መርዳት ከፍጹም ፈቃድና ርኅራኄ የሚያደርጉት ስጦታ ምጽዋት ይባላል፡፡ በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፮ ቊ ፻፳፭-፻፳፯ እንደተገለጠው ምጽዋት ምሕረት ነው፡፡እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ ከተቀባዮች ጋር ሆኖ የሚቀበል በመስጠትና በመቀበል በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር፣ ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምጽዋትን የተረጎሙት እንዲህ በማለት ነው “ምጽዋት ማለት የዕለት ምግብና የዓመት ልብስ ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት ነው። ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ምጽዋት ነው። (ጎሐ ጽባሕ ገጽ ፳፬)፡ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሔር መስጠቱ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም “ለደሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” ይላል። (ምሳ፲፱÷፲፯) ምጽዋት ብልሆች ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው፡፡ ደካሞችን በጉልበት፣ ያልተማሩትን በዕውቀት የሞያ እርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሞያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡ ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ፣ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡ ”ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ድሀ፣ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ” (ዘዳ ፲፭÷፲፩) “ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው፤ እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ ካንተ ጋር ይኑር” (ዘሌ፳፭÷፴፭)
ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡ “……እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፣ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን? (ኢሳ፶፯÷፯) መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ”ሁለት ልብስ ያለው ሰው ለሌላው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ“ ይላል (ሉቃ፫÷፲፩)፡፡ ክርስቲያኖች የሚመጸውቱት ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ነው (ሉቃ፳፩÷፩-፬) ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው፣ ምጽዋት ትልቅ የክርስትና ቁልፍ በመሆኗ ነው፡፡
ብዙዎቻችን የኃጢአት ሥር በተባለው በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ ምጽዋት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መስጠት ነው፡፡ ምጽዋት ብድሩ ከልዑል እግዚአብሔር ይገኛል፣ በሚል እምነት ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ ከግብዝነትና ከከንቱ ውዳሴ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሯል፡፡ የድሆችን ጩኸት ሰምቶ በችግራቸው በመድረስ ምላሽ የሚሰጥ እሱ በተቸገረ ጊዜ በጎ ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል፡፡ ምጽዋት የክፉ ጊዜ ዋስትና ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ”ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የዐቅቦ፣ ወያሐይዎ፣ ወያበፅዖ ዲበ ምድር። / ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል” ብሎ ጽፏል። (መዝ፵÷፩-፪) ጠቢቡ ሰሎሞንም “ፈኑ ኅብስተከ ውስተ ገጸ ማይ እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ። / እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን (ቀን) በኋላ ታገኘዋለህና” (መክ ፲፩÷፩) ብሏል። “እንዴት ሰው ዐይኑ እያየ እንጀራውን በውኃ ላይ ጥሎ ከብዙ ቀን በኋላ ያገኘዋል?” ልንል እንችላለን። “እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው!” ማለት ምጽዋትህን ለተቸገሩት፣ ለድሆች ስጥ ማለት ነው፡፡ “ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ” ማለት የምጽዋቱን ዋጋ በገነት፣ በመንግሥተ ሰማያት ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ፤ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል ምግብህን በከርሠ ርኁባን ፣ መጠጥህን በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው (ዘዳ፲፭፥፯)
ምጽዋት የሚመጸውቱ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይመጸውቱ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ ብዙ በረከትንም ያጣሉ፡፡ በመጨረሻ የፍርድ ጊዜም ወቀሳ፣ ተግሣጽ፣ ፍዳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሰው ከሚረገምባቸው የጥፋት ሥራዎች አንዱ ለድሆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡ “እስመ ኢተዘከረ ይግበር ምጽዋተ፣ ሰደደ ብእሴ ነዳየ ወምስኪነ። / ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም፤ ችግረኛና ምስኪን አሳዷልና“ይላል። (መዝ፻፰÷፲፭)
“ምጽዋት በመስጠት ሰው ፈጣሪውን በሥራ ይመስለዋል፡፡ ለሰው ማዘን፣ መራራት፣ ገንዘብ መስጠት፣ ከአምላክ ባሕርይ የሚገኝ ነውና። / ወበምጽዋት ይትሜሰሎ ሰብእ ለፈጣሪሁ፤ እስመ ውሂበ ምፅዋት ወተሣህሎ እምነ ጠባይዕ አምላካዊ”።
“ምጽዋት መስጠት ለአምላክ ማበደር ነው፡፡ከአምላክ ጋር የሚነግዷት ንግድ ናት፡፡ / ወምጽዋትሰ ልቃሕ አምላካዊት ወይእቲ ካዕበ ተናግዶ አምላካዊት ማእምንት ርብሕት“። “ዳግመኛም ቍርባን ና፤ በከርሠ ነዳያን የምትቀርብ ናት። / ወይእቲ ካዕበ ቍርባን ውክፍት በኀበ መቅደስ ነባቢት“ እንዳሉ። (፫ቱ፻)
ራሱን መርዳት የሚችል ሰው የሰውን ገንዘብ አይቀበል፤ ወጥቶ ወርዶ ራሱን ይርዳ።
ቅዱሳን ሐዋርያትም “ገንዘብ እያለው ምጽዋት የሚቀበል ወዮለት” ብለዋል፡፡
“ምጽዋት ከክፉ ታድናለች፤ ኃጢአትን ታስተሠርያለች፡፡ ውኃ እሳትን እንዲያጠፋ ምጽዋትም ኃጢአትን ታጠፋለች። / ለእሳት ዘትነድድ ያጠፍኣ ማይ፤ ወከማሁ ምጽዋትኒ ታኀድግ ኃጢአተ” እንዳለደ። ሲራክ ፫÷፳፰
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ “ወእመ ትብሎ አንሰ ወሀብኩከ ብዙኀ ጊዜ፤ እብለከ ኢትበልዕኑ አንተ በኵሉ ጊዜ። ብዙ ጊዜ ሰጠሁህ፤ ይበቃሃል አትበል፤ አንተ ጠዋት ማታ ትበላ የለምን? እንደራስህ አታየውምን?” ይላል፡፡
ምጽዋት የሚሰጠው ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ከእግዚአብሔር መልካም ነገር ለማግኘት ነው፡፡ ”ስጡ ይሰጣችኋል“ተብሏልና (ማቴ.፲፥፰፣ ፪ኛቆሮ. ፱፥፯—፲፪) በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር። የጌታን ትእዛዝ፣ ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውታል። (የሐዋ.ሥራ ፳÷፴፮) ዕዝ ፱÷፭) ምጽዋትን በፍቅር መመጽወት ይገባል፡፡ አበው “ከፍትፍቱ ፊቱ“ እንዲሉ፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው“ (ያዕ፬÷፲፯) ይህን በጎ ምግባር ሠርተን እንድንጠቀም የእጃችንን እስራት አምላካችን ይፍታ፤ በእርግጥ የእግዚአብሔር ስጦታውን በቃላት ተናግረን አንጨርሰውም (፪ኛቆሮ፱÷፲፭)

