
ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው:: ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት “ካልዕ (ሁለተኛው) ሊቀ ሰማዕታት” ሲሉ ይገልጹታል::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በ፪ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ (አስሌጥ) ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር “አሮስ” የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደምግባት የሠመረላት፣ እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር:: አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል “እንስሳ ተያዘልን” ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: ሁለት ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ተይዘው ነበር። እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ፣ ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ፣ ወገባቸው እንደ ሰው፣ ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስለው:: እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና: አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው:: “ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት” አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ ሁለቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት:: ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር (ፒሉፓተር) ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም “መፍቀሬ አብ – የአብ ወዳጅ” ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን : ልጁንና ሁለቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተጠመቀ::
አበው ካህናት እሱን “ኖኅ”፣ ሚስቱን “ታቦት” : ልጁን ደግሞ “መርቆሬዎስ” ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም “ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ / የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ” እንደ ማለት ነው:: ከዚያም ደስ እያላቸው፣ ክርስቶስን እያመለኩ፣ ነዳያንን እያሰቡ፣ ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ “ካላመጣሃቸው” አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ:: ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን ሁለቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል “እንቢ” በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::
በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን “ላግባሽ” ስላላት የ፭ ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው:: እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በኋላ ግን በሕፃኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ:: በዚያም ቤተ ክርስቲያን አንጾ፣ ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጎ፣ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::
ቅዱስ መርቆሬዎስ በጦርነትም እጅግ ኃያል፣ በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ፣ የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምእመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ:: ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: በማግስቱም “ምን ይሻላል?” ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ “እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻዬን እቋቋማቸዋለሁ” ቢል ሳቁበት:: እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ (አብሮት ያደገ ነው) ተጭኖ በርበሮችን “ጠብ ይቅርባችሁ፤ በሰላም ሒዱ” ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ አልነበረም::
ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ “ድሉ የጣዖቶቼ የነ አጵሎን ነው” በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ:: በ፫ኛው ቀንም “ለጣዖት ሠዋ” የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው:: “ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል:: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ:: (ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ እና ሀብትህ ለጥፋት ይሁንህ)” ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው:: ያም አልበቃ:: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት: “አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም:
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም:: አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም::” ያሉት::
ከዚያም ቅዱስ መርቆሬዎስን ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ፣ በግርፋት፣ በእሳት፣ በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::እርሱ ካረፈ በኋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኳል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ፳፻ ዓ/ም እንደ ተወለደ፣ በ፳፻፳ ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ፳፻፳፭ ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

