ሐዋርያውያን አበው (ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም፣ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፣ቅዱስ ፖሊካርፐስ)

ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም፡ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የተተካው ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም ከሊነስና አንክሌተስ ቀጥሎ ሦስተኛው የሮም ሊቀ ጳጳስ እንደነበር ቅዱስ ሄሬኔዎስ ይናገራል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማንያ ወአሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚመደበው መጽሐፈ ቀለሜንጦስ ቅዱስ ቀለሜንጦስ ለሮም የላከው መልእክቱ ነበር። በመጽሐፉም ከሥነ-ፍጥረት ጀምሮ ነገረ-ሃይማኖትና ቀኖና ቤተክርስቲያን ይገኙበታል። ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥብቅና በመቆም ሐዋርያዊ ሥራውን እየሠራ ሳለ በጠራብሎሱ መሪ ከሮም ተወስዶ፣ ወታደሮች በባህር መካከል ጥለው ገድለውታል። በዓለ ዕረፍቱን ቤትክርስቲያን ኅዳር ፳፱ ታከብረዋለች።

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፡ ጌታችን ለሐዋርያት ሕፃኑ ቅዱስ አግናጥዮስን በመካከል ይዞ ስለ ትሕትና አስተምሯቸዋል። በኋላኛው ዘመንም በሐዋርያት በአንጾኪያ ጵጵስናን ተሾመ።  በትራጃን የንግስና ዘመን ትራጃን ምሥራቃውያንን ድል በመንሳቱ የጣኦት መሥዋዕትን ሊሰዋ ወደ አንጾኪያ ከተማ መጣ። ክርስቲያኖች ለጣዖት እንዲሰዉ ቢያስነግርም ቅዱስ አግናጥዮስ ምዕመናን ለጣዖት እንዳይሰግዱ መስዋዕትንም እንዳያቀርቡ ያስተምራቸው ነበር። በዚኽ የተበሳጨው ትራጃን ወደ ሮም እንዲወስዱት እና ለተራቡ አናብስት እንዲሰጥ አዝዟል። ስለሚደርስበት መከራና ስለክርስቶስ ፍቅር እንዲህ እያለ ይጸልይ ነበር: “ጌታ ሆይ በፍቅርህ ብዛት ታከብረኝ ዘንድ ፣ እንደ ሐዋርያህ ጳውሎስ በብረት ሰንሰለቶች እንድታሰር ስለ ፈቀድኽልኝ አመሰግንሃለሁ”። በሮም የነበሩ ክርስቲያኖች ቅዱስ አግናጥዮስን ለማትረፍ ሲሞክሩ ከሚያገኘው መከራ እንዳያስቀሩት መልእክትን ላከላቸው። “በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር ከመሄድ የተሻh ሌላ ዕድል የለኝም። ስለዚህ እለምናችኋለሁ! ለ እኔ የተዘጋጀ መሠዊያ አለና። ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኜ እቀርብ ዘንድ አሰቃዩኝ፤ ከዚህ ዓለም ወደ እግዚአብሔር የምትጠልቅ ፀሐይ መሆን አንዴት ዓይነት ክብር ነው። እርሱ ባለበት እወጣለሁና፣ እኔ ለእግዚአብሔር የመገበሪያ ስንዴ ነኝ። የክርስቶስ ንጹሕ የመሥዋዕት ኅብስት እሆን ዘንድ በአናብስቱ ጥርስ ክፈጥ ይገባኛል”። ቅዱስ አግናጥዮስ በሮም በፍላቪያን አንፊ ቴያትር ፩፻፰ ዓ.ም. በተራቡ አናብስት ተበልቶ ሰማዕት ሆኗል። በዓለ ዕረፍቱም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ይታሰባል።

ቅዱስ ፖሊካርፐስ፡ በሐውርያው ቅዱስ ዮሐንስ የተሾመው ቅዱስ ፖሊካርፐስ ትውልዱም እድገቱም ጵጵስና በተሾመበት በዚህች በሰርምኔስ ከተማ ነበር። የቅዱስ ዮሐንስ ደቀመዝሙር የነበረው የሰርምኔሱ ሊቀ ጳጳስ ቡኩሎስ አስተምሮ ዲቁና ሾመው። ኋላም ቡኩሎስን በመተካት የሰርምኔስ ሊቀ ጳጳስ ሆነ። መናፍቃንን ይቃወማቸው፣ አብዝቶም ለኑፋቄያቸው መልስ ይስጥ ነበር። በተለይ በዘመኑ የነበሩት ከሀድያን መርቅያንና ቀሪንጦስን ስለ ክህደታቸው ለምዕመናን በማስተማር የእረኝነቱን ሥራ ይሠራ ነበር። በሮማውያን ወታደሮች ተይዞ፣ ስለ ክርስቶስ ክፉ እንዲናገር ቢያስገድዱትም ለቀናች ሃይማኖቱ ይጋደል ዘንድ ቤዛ ለሆነው አምላኩ መስክሮ፣ በሚነድ እሳት ተጨምሮ ሰማዕትነትን ተቀብሏል።

በቅዱሳን ሐዋርያት እግር ሥር የተተኩ በጽሑፎቻቸው፣ በሥራቸውና በተጋድሏቸው የሚታወቁት ሐዋርያውያን አበው(የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ በርናባስ፣ የኤዶም ሊቀ ጳጳስ ሴማዊው ሄኔሬስና ቅዱስ ዲዮናስዮስ) በጊዜው ለነበሩት ክርስቲያኖች በቃል፣ በጽሑፍና በተግባር እያስተማሩ በሃይማኖት አጽንተዋቸኋል። ሐዋርያዊት ተብላ የምትጠራውን ቅድስት እምነት በመረከብ ተላውያነ ሐዋርያነት(Apostolic succession) እንደነበረች በማስቀጠል፣ ከሐዋርያት ባልተለየ እምነታቸው አስረድተዋል። የእኒኽ የቅዱሳንን አባቶቻችን ረድኤትና በረከት በሁላችን ይደርብን!!!