
ቅዱስ ያዕቆብ የይስሐቅ ልጅ ማለትም የአባታችን የአብርሃም የልጅ ልጅ ነው። የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ርብቃን አገባ፤ ርብቃም መካን ስለነበረች ልጅ አልነበራትም። አባታችን ይስሐቅ ስለ ይስሐቅ ሚስት እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም ተለመነው ርብቃም ፀነሰች። ትወልድ ዘንድ ዘመኗ በተፈፀመ ጊዜም። እነሆ በማሕፀኗ መንታ ነበሩ።
በፊትም የመጣው ቀይ ነበረ፤ ሁለተኛውም ጠጉር ለብሶ ነበር ስሙም ዔሳውተባለ። ከዚህም በኋላ ወንድሙ ወጣ በእጁም የዔሳው ተረከዝ ይዞ ነበር ስሙም ያዕቆብ ተባለ። አባታቸው ይስሐቅ ኤሳውን ይወድ ነበር፤ እናታቸው ርብቃ ግን ያዕቆብን አስበልጣ ትወደው ነበር።
አባታቸው ይስሐቅ በሸመገለ ጊዜ በጣም አርጅቶ ነበርና ለሚወደዉ ልጁ ሊባርከው አሰበ። ነገር ግን እናታቸው ርብቃ የዔሳውን ምርቃት ለያዕቆብ በመምከር የዔሳው በረከት ተወሰደበት። ዔሳውም በጣም ተናዶ ወንድሙን ያዕቆብን ለመግደል ወሰነ፤ በረከቱን ወስዷል እና ርብቃም ታላቁ ልጇ የዔሳው ቃል ደረሳት። ታናሹም ልጇን ያዕቆብን ጠርታ “እነሆ ዔሳው ወንድምህ ሊገድልህ ፈልጓል፤ ቃሌን ስማ ተነስና ወደ ካራን ምድር፣ ወደ ወንድሜ ላባ ሂድ፤ የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድለት ጥቂት ቀናት በዛው ተቀመጥ” ብላ አሳመነችው። ዘፍ ፳፯፥፵፬-፵፭ ያዕቆብም ” እሺ “ብሎ” መንገዱን ጀመረ።
ያዕቆብም ከቤርሳቤ ወደ ካራን ሄደ፤ ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፤ ፀሐይ ጠልቃ ነበርና ከዛ አደረ። በዛም ስፍራ ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ፤ ህልምንም አለመ። እነሆ መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፣ ራሱም ወደ ሰማይ ደረሰ፤ የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት፣ ይወርዱበት ነበረና እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር። እንዲህም አለ : “የአብርሐም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጥሃለው፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል። እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ፣ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ። የምድርም አህዛብ ሁሉ ባንተ በዘርህም ይባረካሉ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በመትሄድበት መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለው፣ የነገርኹህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነስቶ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር” አለ። ፈራ እንዲህም አለ “ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።” ያዕቆብም ማልዶ ተነሳ፤ ተንተርሶት የነበረውን ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው። በበላዩም ዘይት አፈሰሰበት፤ ያዕቆብም ይንን ስፍራ “ቤቴል” ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዞያች ቦታ ስም ሎዛ ነበር። ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስዕለት ተሳለ “እግዚአብሔር ከኔ ጋራ ቢሆን፣ የምሄድበትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ ፣ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ ቤት በጤና ብመለስ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል። ለሐውልት የተከልኩትም ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል። ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አንዱን እሰጥሃለው ብሎ ቃል ገባ።” ዘፍ ፳፰
እኛም እግዚአብሔር አምላክ ከቅዱሳን መላእክቱ ከኛ ጋር እንዲያድርና ጥሩ የሰላም እንቅልፍ እንዲያስተኛን፣ ቅዱሳንንና መላእክትን እንዲያሳየን፣ ከመጥፎ ህልም እንዲጠብቀን፣ እግዚአብሔር ከኛ ጋር እንዲሆን፣ ከመጥፎ አጋንንት እንዲጠብቀን፣ የያዕቆብ ሌሊት ይሁንልን! እንላለን። የያዕቆብ ሌሊት ይሁንልን።

