
ቤተክርስቲያናችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን
አፈ በረከት
አፈ መዐር (ማር)
አፈ ሶከር (ስኩዋር)
አፈ አፈው (ሽቱ)
ልሳነ ወርቅ
የዓለም ሁሉ መምህር
ርእሰ ሊቃውንት
ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ)
የሐዲስ ዳንኤል
ሊቀ ጳጳሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው)
መምህር፣ ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
ጥዑመ ቃል … እያለች ብዙ ታከብረዋለች ።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ነገዱ ከሶርያ፣ የተወለደው በ፫፻፵፯ ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ፣ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምህርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕፃንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመኑ አስኳላም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ፲፭ ዓመቱ ነበር:: በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኩዋን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው:: ቅዱሱ ገና በ1፲፮ ዓመቱ ሀብት፣ ንብረት፣ ውበት፣ ክብርና ዕውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በረሀ ገባ::
ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበረሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት:: ከዚህች ዕለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጓሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱሱ ኅሊናው ሳይታክት፣ ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት፣ መልእክታትና ትርጓሜያት ቢቆጠሩ ዐሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሠራ ዕድሜው ገና ለጋ፣ ማዕርጉም ዲቁና ነበር::
በኋላም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምህርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል አፈ ወርቅ ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው ቅዱሱ አፈ ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልአከ ሞትን ገስፆ ለዐሥር ዓመታት አቁሞታል::
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ድሃ፣ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: በዚህም ምክንያት የወቅቱ ንግሥት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ ሁለት ጊዜ አጋዘችው:: በተሰደደበት ሀገር ፍሬ አፍርቶ፣ አስተምሮና አሳምኖ በ፬፻፯ ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ፷ ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ::
አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ (ግብዣ አዘጋጀ)። በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ፣ አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ፲፪ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ:: ደንግጦ “ወዴት ናችሁ ጌቶቼ” ቢላቸው “ቁስጥንጥንያ፣ ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና” አሉት:: “እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንዲገለጥልኝ መርቁኝ” አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀዉት ጎዳናቸውን ቀጠሉ:: በማግስቱ በቤተ መንግሥት ውስጥ ሊቃውንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ጳጳሳቱ፣ ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን “ጥያቄ አለኝ” ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው::
‘ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ “ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ / የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?’ ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር::
“ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ኅብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር::
‘ “እርሷ ማን ናት? በማሕፀኗ ያለውስ ማን ነው?” እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ኅብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም:: አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ፣ ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኑን አወቀ ማለት ነው’ እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ፣ በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ “አፈ። ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!” ስትል ተናገረች:: ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ “እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . .” ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል::
ሊቁ ባረፈ በ፴፭ ዓመቱ በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን፣ በግንቦት ፲፪ ቀን ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኳል:: የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ረድኤት በረከቱ ያሳትፈን።

