ፍቅርን መስጠት

ክርስቲያናዊ ፍቅር ከልብ የተተከለ የመውደድ ኃይል አለው፡፡ የክርስቲያኖች የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና፡፡ ”ነገር ግን በእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው። (፩ኛጴጥ፭÷፰) ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ በማለት ከዘረዘራቸው መካከል የመጀመሪያው ፍቅር ነው። (ገላ፭÷፳፪) በዘመናችን ግን ይህ የመንፈስ ፍሬ ከሰው ልጆች ልቡና እየጠፋ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ -መዛሙርቱ በደብረ ዘይት ስለ ዓለም ፍጻሜ በጠየቁት ጊዜ ምልክቱን ሲነግራቸው ከሰው ልጅ ዘንድ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ገልጾላቸዋል፡፡ ”ከዐመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” በማለት (ማቴ ፳፬÷፲፪) የፍቅር ሸማ ከሰው ልጆች ልቡና ውስጥ ተገፍፎ እንደሚወድቅ ተነግሮናል።

“ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻው ቀርቧል፤ እንግዲህ እንደ ባለአዕምሮ ዐስቡ፤ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” ይላል። (፩ኛ ጴጥ ፬÷፯) ወጥ ማጣፈጫው ጨውና ቅመም እንደሆነ ሁሉ የሰው ማጣፈጫውም ሃይማኖትና ፍቅር ነው፡፡የፍቅር ምንጩ ክርስቶስ ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ለተራቡ ሥጋውን አብልቶ ደሙን አጠጥቶናልና“ ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን፤ የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው (ሉቃስ ፩፥፶፫) ዘለዓለማዊ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር በቃላት ከመነገርና በልቡና ከመታሰብ በላይ የሆነውን ጥልቅ ፍቅሩን የገለጠው በመስቀል ነው፡፡ በአዳም በደል ምክንያት “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን” (ኢሳ፶፫÷፮)፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን እንዳንቀር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደል ሳይኖርበት የእኛን በደል ተሸክሞ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገልጾልናል፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም ይህንኑ ሲመሰክር “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት። (ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው)” ብሏል (ቅዳሴ ማርያም)፡፡
እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል ገልጦልናል፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅሩን ካሳየን በኋላ “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” (ዮሐ. ፲፭፥፲፪) በማለት እርሱ እንዲሁ እንደወደደን እኛም እንዲሁ እንዋደድ ዘንድ አዞናል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ  “ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል?” (፩ኛ ዮሐ ፬÷፰-፲፪) በማለት ያስተማረን።  ስለዚህ ነገ ነፍሳችን ልብሰ ጸጋዋን ተገፋ ከክርስቶስ ፊት እራቆቷን እንዳትቆም ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የፍቅር ሸማኔ ሆነን ልብሰ ጸጋ ልንሠራላት ይገባል፡፡ ድሩን ሃይማኖት ማጉን ፍቅር አድርገን የክብር ልብስ የሠራንላት እንደሆነ ሞገስ ታገኛለች፡፡

ሰው ለፍቅር ዘወትር የጋለ ብረት ምጣድ ሆኖ ከተገኘ ዕድሉ የቀዘቀዘና የፈዘዘ አይሆንበትም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሽዋ ጸናጽል ሆኜኛለሁ….” (፩ኛ ቆሮ ፲፫÷፩-፰) ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን፣ ተስፋንና ፍቅርን ከዘረዘረ በኋላ የሚበልጠው ፍቅር ነው ይላል፡፡ ክርስቲያኖች የሚኖረን ፍቅር እንደ ፀሐይ እንጂ እንደ ጨረቃ መሆን የለበትም፡፡ ፀሐይ ሁል ጊዜ ሙሉ ነች የእኛ ፍቅር ወጥ መሆን አለበት እንጂ ጥቅም ስለምናገኝ ብቻ ሰዎችን የምናፈቅር ከሆነ ጨረቃ ሁነናል ማለት ነው፡፡ “በቃልና በኑሮ በፍቅርም፣በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን”  (፩ኛ ጤሞ ፬÷፲፩-፲፪) ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን በፍቅር የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ ፍቅር ለሌሎች በመስጠት ክፉ የሚያስቡትን በፍቅር ማሸነፍ ይገባል፡፡