
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌ ካስተማራቸው እና ወደ ዓለም ከላካቸው ከመጀመሪያዎቹ የወንጌል ገበሬዎች ሐዋርያት በኋላ የተነሡ አባቶች ነበሩ፡፡ እነዚህም አባቶች ከጌታ ሐዋርያት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸውና የእነርሱ ደቀ መዛሙርት ስለነበሩ፣ በትምህርተ ሃይማኖትና በምግባርም መሳዮቻቸው ስለሆኑ ሐዋርያውያን አበው ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነርሱም ከቅዱሳን ሐዋርያት በቃልም በሥራም የተማሩ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ፣ በመንበራቸው የተተኩ ደቀ መዛሙርታቸው ናቸው፡፡ በማንኛውም የሥራ መስክ መንፈሳዊ አደራቸውን ከቅዱሳን ሐዋርያት ተቀብለው ቤተ ክርስቲያንን የመሩ፣ ርቱዐነ ሃይማኖት የሐዋርያት ሁለተኛ ዙር ሐዋርያት ናቸው፡፡ ዘመናቸውም ከ70 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 160 ዓ.ም. ድረስ የዘለቀ ነው:: በእርግጥ “ሐዋርያውያን አበው” የሚለው ቃል በዚያን ጊዜ አይታወቅም ነበር፡፡ ስያሜውን በስፋት መጠቀም የተጀመረው ከዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ነው፡፡
ከነዚህም አበው ብዙዎቹ ብዙ መጻሕፍትን ጽፈዋል፣ ተርጉመዋል፣ በጽሑፎቻቸውም ክርስቲያኖች በደረሱባቸው ስደቶች ምክንያት ተስፋ እንዳይቆርጡ አጽናንተዋቸዋል፡፡ እንዲሁም በየጊዜው በተነሡት መናፍቃን ትምህርት እንዳይታለሉ በማለት ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በሥርዓት ለመምራት የሚያስችሏቸውን ጽሑፎች በቅዱስ መጽሐፍ ቃል ላይ ተመሥርተው ጽፈዋል፡፡ መጽሐፈ ዲድስቅልያ፣ መልእክተ በርናባስ፣ መልእክታተ ቀሌምንጦስና ራእየ ሔርማ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም “ቀደምት የክርስትና ጸሐትት” (Early Christian Writers) ይባላሉ። (GEOFFREY PARRINDER, A CONCISE ENCYCLOPEDIA OF CHRISTIANITY, P.26; GEORGE W. GRUBE, THE COMPLETE BOOK OF ORTHODOXY, P. 37)
እነዚህ አበው ከቤተ አይሁድ ብቻ ሳይሆን ከቤተ አሕዛብም የተገኙ ናቸው፡፡ በሐዋርያት ጊዜ እነርሱን እየረዱ ኖረዋል፡፡ ባስተማሯቸውም ትምህርት ጸንተው በማጽናታቸው በዐላውያን ነገሥታት ሰይፍ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ ሐዋርያውያን አበው ከሚባሉት መካከል ቀሌምንጦስ ዘሮም፣ ፖሊካርፐስ፣ ሄርማስ፣ ፓፒያስና አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ አባቶች ለቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነትን እስከ መቀበል ደርሰው ከሠሩትና ካስተማሩት ይልቅ ከሞቱ በኋላም ሕያው በሆነው ስማቸውና ትምህርታቸው እየሠሩ ያለው ሥራ ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ትምህርታቸው መናፍቃንን እያሳፈረ አጋንንትን እያስደነበረ ነውና፡፡ ሊቃውንቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉት በአነርሱ አስትንፋስ (ትምህርት) ነውና፡፡
እነርሱን መሆን ባይቻልም ቤተ ክርስቲያንም የእነዚህን ቅዱሳን አበው ብሔረ ሙላዳቸውን፣ ጥንተ ነገዳቸውን፣ የገድላቸውን ጽንአትና የሥነ ጽሑፋቸውን ብስለት መዝግባ አስቀምጣልናለች።
አብዛኛዎቹ የሐዋርያውያን አበው ድርሳናት የክርስቶስ ምጽአት ላይ ያተከሩ ሲሆን ከዚህም የተነሣ በመጀመሪያው እና ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የነበሩት አበው ክርስቶስ በቶሎ ይመጣል የሚል ጠንካራ አመለካከት (Eschatological attitude) ስለነበራቸው ብዙ ድርሳን የማዘጋጀት ዓላማ አልነበራቸውም፡፡ በጻፏቸው ጥቂት ድርሳኖችም ላይ ነገረ ምጽአታዊ ትምህርቶች በስፋት ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡
እነዚህ ሐዋርያውያን አበው በተለያየ አገር የኖሩ ይሁኑ እንጂ በመልእክቶቻቸው ያንጸባረቁት አስተምህሮት ግን ተመሳሳይ እና ከአንድ ምንጭ የተቀዳ ነው:: ይህም ነገር የቤተ ክርስቲያንን ኩላዊትነት (Catholicity) የሚያሳይ ቀዳማዊ ማስረጃ ነው፡፡
ምንጭ:
፩. አባቶችህን እወቅ (ዲ/ን አቤል ካሳሁን) ፳፻፲፪ ዓ.ም.
፪. ነገረ ቅዱሳን (አሉላ ጥላሁን እና ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ) 2014 ዓ.ም

