
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም::ስለዚህም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አባት ሊቀ ሊቃውንት፣ ርእሰ ሊቃውንት፣ የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን) ሐኪም (Doctor of the Church)፣ ሐዋርያዊ ብላ ታከብረዋለች::
ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ (በ300 አካባቢ) እስክንድርያ ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር:: ሕፃን እያለ ለጨዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም “ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ!” ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕፃናቱ ዕጣ ተጣጣሉ:: ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር:: በአጋጣሚ ሕፃናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕፃኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት:: ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ጳጳሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው:: ምንም ሕፃን ቢሆንም ከሊቅነቱ፣ ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::
ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው:: ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ፣ እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው:: ከዚህበኋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) ፳ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ፵፰ ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በረሃ ሲያግዙት በስደት ከ፲፭ ዓመታት በላይ አሳልፏል::
አርዮሳዊ መናፍቅ ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም የሚያሳድድ ሆነ። ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር:: በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በረሃ አግዞ፣ መናፍቅ ጳጳስ በግብጽ ሾሞ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል፣ ቅዱሱን ለስድርት ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ ተናገረው::
ሁለት አማራጮችን አቅርቦ “ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን፤ ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምእመናን) መልሰኝ” አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::
ቀዛፊ፣ መቅዘፊያ፣ ምግብና ውኃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ:: ቅ. ሚካኤልና ቅ.ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፉ፣ ሌሎች መላእክት እየመገቡት እስክንድርያ(ግብጽ) አድርሰዉት ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል።
በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው:: ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ፣ ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በ፫፻፸ዎቹ ዓ/ም አካባቢ አርፏል::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

