
ብሥራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጦ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ መወለድ ያበሠራት ዕለት፣ ታኅሣሥ ፳፪ “ብሥራተ ገብርኤል” ታላቅ በዓል ነው፡፡ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅ አስማምታ በምትፈትልበት ሰዓት ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ “ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።
ድንግል ማርያምም “እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንዴት ይደረግልኛል?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ቅዱስ ገብርኤልም “ማርያም ሆይ አትፍሪ! ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና። እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዩዋለሽ። ይህ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” አላት፡፡
እርሷም “ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል፤ ወንድ ሳላውቅ?” አለቺው፡፡
መልአኩ ገብርኤልም “መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል፤ የልዑል ኃይልም ያድርብሻል” አላት፡፡
እርሷም የመልአኩን ቃል ተቀብላ “እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” አለቺው፡፡
በዚህ ጊዜ አካላዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፡፡ ቅድስት ማርያም እምነቷን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋለችና በትንቢተ ነቢያት መሠረት በድንግልና ፀነሰቺው፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱፣ ኢሳ. ፯÷፲፬ )
ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ስለ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራትና ስለ አምላክ ሰው መሆን ሲመሰክር “እርሱ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ቅዱስ ገብርኤል የሚባል መልአክ ወደ አንቺ ላከ፤ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ያድራል፡፡ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፤ ከአባቱ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሺው፤ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማሕፀንሽ ተወሰነ፤ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መላኮት በማሕፀንሽ አደረ›› (ቅዳሴ ማርያም ቁ. ፵፭) ብሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የብሥራት ቀን በማሰብ ታከብረዋለች፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፤ ቅዳሴ ማርያም

