የሰላሙ ንጉሥ ልደት በጦርነት(ከቤተልሔም እስከ ላሊበላ)

አስቀድሞ በትንቢት “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ኢሳ ፱÷፮ የተባለለትን ቅዱስ ያሬድም በድጓው “ትዕምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ” “የሰላማችን ምልክት ወልድ ተወለደልን” ብሎ የተናገረለት የሰላሙ አለቃ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተከበረና ለመከበርም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።ምዕራባውያንን ጨምሮ የህንድና የሶሪያ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት በጎርጎርዮሳውያን ዘመን ቀመር መሠረት ባሳለፍነው ሣምንት ታህሣሥ ፲፯ በዓሉን አክብረዋል። በኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት የዘመን ቀመር ሥር የሚገኙት የኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊያን በታኅሣሥ ፳፱ በዓለ ልደትን ለማክበር በልዩ ጉጉት ውስጥ ሆነው እየጠበቁ ይገኛሉ።በዓለ ልደት ሲነሳ በክርስቶስ ኢየሱስ መወለድ ስላገኘነው ታላቅ ሠላም “ወሰላም ለምድር፤ ስምረቱ ለሰብእ” እያልን የምንዘምርበት ዕለት ቢሆንም ዘንድሮ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በዩክሬንና ሩሲያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሰላም እጦት ውስጥ ሆነው ለማክበር ተገደዋል። በዚህ ሳምንት ዘገባችንም የገና በዓል በድምቀት የሚከበርባቸው አካባቢዎች የዘንድሮን የበዓል አከባበር እንመለከታለን።

ላሊበላ – ኢትዮጵያ፡ ከአንድ አለት የተፈለፈሉ አሥራ አንድ አብያተክርስቲያናት የሚገኙባት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም የተሰኘችዋ ደብረ ሮሃ በዓለም ላይ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል አንዷ ናት። ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ አውጪዎች ለገና በዓል ከቅድስት ቤተልሔም ቀጥሎ በ፪ኛ ወይም በ፫ኛ ደረጃ የሚያስቀምጧት ላሊበላ ልብን በሚመሥጠው “የቤዛ ኩሉ” ዝማሬዋ ልቦናን ወደ ክርስቶስ የልደት ምሽት በመውሰዷ በብዙኀኑ ምእመናንና ቱሪስቶች ዘንድ በየዓመቱ ትናፈቃለች።ይህች የምስጋና ደሴት ግን ድኅረ ኮቪድ ሀገራችን ባስተናገደቻቸው አራት የጦርነት ዓመታት ምክንያት የደኅንነት ሥጋት ተጋርጦባታል። በዚህም ከሩቅና ቅርብ የሚመጡ የተሳላሚዎች መጠን በመቀነሱ አብያተ ክርስቲያናቱና በጎብኚዎች ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል። ማግሰኞ ለሚከበረው በዓለ ልደት እየተዘጋጀች የምትገኘው ላሊበላ ዘንድሮም በተስፋና ሥጋት ውስጥ ሆና እንግዶቿን እየጠበቀች ነው።በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም እየተካሄዱ ባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ባስከተሏቸው ጫናዎች ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያዊያን በዓለ ልደቱን በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ።

ገና በሩሲያና ዩክሬን፡ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ሕዝቦችን የያዙት ሩሲያና ዩክሬን በዓለ ልደትን ለዘመናት በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት በታኅሣሥ ፳፱ ያከብሩ የነበረ ቢሆንም ዩክሬን ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ምክንያት የሩሲያን ተፅዕኖ ከዩክሬን ለማጥፋት በሚል ስበብ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመንግስት ውሳኔ ከምዕራባውያን ጋር በታኅሣሥ ፲፯ ለማክበር ተገዳለች። ከሩሲያና ከሩሲያ ቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ከምድረ ገጿ እያጠፋች የምትገኘዋ ዩክሬን ለኦርቶዶክሳዊያን ሲኦል ሆና እየተሠራች እንደምትገኝ በርካቶች ይናገራሉ።ዩክሬን የዘንድሮ የገና በዓልን እንደ ከዚህ ቀደም በሚያማምሩ ርችቶች ሳይሆን በእስካሁኑ ጦርነት ታይቶ በማይታወቅ የባለስቲክ ሚሳኤል ናዳ ነበር ያከበረችው። ለአንድ ሰው ሞትና ለአስራ አምስት ሰዎች መቁሰል ምክንያት የሆነው ይህ ጥቃት ከፍተኛ የኀይል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ በማድረጉ ዩክሬናውያን በዓሉን በጨለማ ለማሳለፍ ተገደዋል።

ልደት በመካከለኛው ምሥራቅ፡የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ በሶሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአዲሱ ወታደራዊ መንግስት ስር ሆነው የልደት በዓልን ታኅሣሥ ዐሥራ ሰባት አክብረዋል።የልደት በዓል አከባበሩ በደማስቆ መንበረ ፓትርያርክ በሰላም የተካሄደ ቢሆንም እንደ አሌፖና አልዋ ባሉ አካባቢዎች ክርስቲያኖች የተፈናቀሉበት የልደት በዓል መታሰቢያዎች የተቃጠሉበትና ግጭቶች የተነሱበት ሆኖ አልፏል።

በዓለ ልደት በሊባኖስና ኢራቅ፡ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የኪልቂያ መንበር መቀመጫ በሆነችው ሊባኖስ የገና በዓልን ከእስራኤል ጋር ባለው ጦርነት ሥጋት ውስጥ ሆና በቀዘቀዘ የሀዘን ድባብ ውስጥ አክብራለች።በኢራቋ ነነዌ ደግሞ በዓሉን በሥጋት ውስጥ ሆነው ቢጀምሩትም ኢስላማዊው የሺሃይት ብርጌድ ባደረገው ጥበቃ ያለምንም ችግር በዓሉን አከናውነዋል። ይሄንን ተከትሎ በርካታ የኢራቅ ክርስቲያኖች ለብርጌዱ ያላቸውን አክብሮት ሲገልፁ ተስተውለዋል።

ባለ ፪ በዓሏ ቤተልሔም፡ከእስራኤል ጋር አመትን የተሻገረ ግጭት ውስጥ በምትገኘው ፍልስጤም የዌስት ባንክ አስተዳደር ስር ያለችውና የክርስቶስ ኢየሱስ የልደት ቦታ የሆነችው ቤተልሔም በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ የገናን በዓል ሁለት ጊዜ ታከብራለች። ታኅሣሥ  ፲፯ እና ፳፱። እነዚህ ቀናት በክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን በእስልምና ተከታዮች ዘንድ የሚናፈቅና በየዓመቱ በሚልየን የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚገኙበት የነበረ ቢሆንም ቤተልሔም ዘንድሮ ያን ተናፋቂ በዓል ለማክበር አልታደለችም። በከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር ክርስቲያኖች ሥርዓተ አምልኳቸውን በአብያተክርስቲያናታቸው አክብረው እንዲመለሱ ከመንግስት ባለሥልጣናት በተላለፈላቸው መመሪያ መሠረት የታኅሣሥ ፲፯ቱን በዓል ዝም ባለ ድባብ ያከበሩ ሲሆን የታኅሣሥ ፳፱ኙም ተመሳሳይ እንደሚሆን ይጠበቃል።በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው በዓለ ልደትን የሚያከብሩ የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪያቸውን እያሰሙ ሲሆን ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመትና ተያይዞ ለሚከበረው የልደት በዓል ለመላው ዓለም መልእክታቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ናቸው። ዓለም በዚህ ትብታብ የመከራ አዙሪት መውጣት የምትችለው በይስሙላ የሰላም ስብሰባ አለመሆኑን ጠቅሰው “ስለዚህ በዚህ የልደተ ክርስቶስ መታሰቢያና የ2025 ዓ.ም. መቀበያ ላይ ቆመን ይቅር መባባል፣ ለጋራ ቤታችን መሥራትና በሰዎች አለመግባባት የታወከችውን ዓለም በሰዎች ቁርጥ ውሳኔ እንድትረጋጋ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል ።” ሲሉ ጥሪያቸውን በመላው ዓለም ላሉ ሁሉ አቅርበዋል።እኛም የቅዱስ አባታችንን ጥሪ፣ ጥሪ አድርገን የልደቱ ባለቤት መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእርሱ የሚገኘውን ሰላም እንዲሰጠን እየተመኘን የዛሬውን በዚህ ቋጨን።መልካም ገና፣ መልካም ሰሞነ አስተርዕዮ!