
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ አርእስተ ሊቃውንት ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ (ባስልዮስ የሚሉ አሉ)፣ እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባልና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው ፭ ወንድ እና ፩ ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ ( ቅድስት ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን ፭ቱም ወንዶች ጳጳሳት መሆናቸው ነው:: የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው ። ቅዱስ ባስልዮስ ገዳማዊ ጻድቅ፣ ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ፣ የብዙ ምእመናን አባት፣ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት፣
ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ፬ኛው መቶ ክ/ዘ ያስገነባ እርሱ ነው:: እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል:: ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዛሬ ይህኛውን ታስባለች::
በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውዬውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ:: እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን “ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ” አለው:: ያ ከንቱ ሰው “እሺ” አለ:: መተተኛው ቀጠለ “በል! ሌሊት ፮ ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል” ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ፣ ነጥቆ ወደ ጥልቁ የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- “አንተ የፈለግኸው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ” አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው:: በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: ልጃቸው “ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ” አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ:: እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተዉት አልወደዱምና ጾሙ፣ ጸለዩ፣ ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::
አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ ” ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ፣ ቆርበህ፣ ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ፣ አማትበህስ ታውቃለህ?” አለችው:: እርሱም “በጭራሽ አላውቅም” አላት:: “ለምን?” ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት:: ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በኅሊናዋ አንድ ዐሳብ መጣላት:: “ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል” አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች:: እርሱም “ልጄ ሆይ! አይዞሽ! በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሽን አምጪው” አላት:: ሔዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው “መዳን ትፈልጋለህ?” አለው:: ሰውየው መልሶ “ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር” አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን “ሒጂና ጸልዪ! ከ፵ ቀን በኋላ ትመጫለሽ” ብሎ አሰናበታት:: በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ፬ አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት “ከ፫ ቀን በኋላ እመጣለሁ” ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ፫ኛው ቀን መጥቶ “እንዴት ነህ?” አለው:: “አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ” አለው:: “አይዞህ!” ብሎት ወጣ::
በ፮ኛው ቀን መጥቶ “አሁንስ?” አለው:: “አባ! ስቃዩ ቀረልኝ፤ ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል” አለው:: “በርታ” ብሎት ሔደ:: በ፱ኛው ቀን ተመልሶ “ደግሞ አሁንሳ?” አለው:: “አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው” አለው:: እንዲህ በ፫ ፣ በ፫ ቀናት እየተመላለሰ ለ፲፫ ጊዜ ጠየቀው:: በ፴፱ኛው ቀን መጥቶ “ዛሬ ምን አየህ” ቢለው “አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ” አለው::
ቅዱስ ባስልዮስ በ፵ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናንን ሰብስቦ፣ ያንን ሰው ከመሃል አቁሞ፣ “እግዚኦ በሉ” አላቸው:: ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ፵ ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ፤ የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር ፮ ቀን ዐርፏል::አምላከ ቅዱሳን ከረድኤት በረከቱ ያሳትፈን።

