
ጥምቀት ሌሎችን ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለመሳተፍ፣ የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን የመጀመሪያው መግቢያ በር ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ጥምቀትን መሠረተ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከውኀው ከወጣ በኋላ አብ “ዝንቱ ወልድየ” ብሎ የባሕርይ ልጅነቱን መስክሯል። መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጧል። ማቴ ፫÷፲፮-፲፯ በትምህርቱ መጨረሻ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ!” በማለት ጥምቀትን አዟል። ማቴ ፳፰ ÷ ፲፱
ከመጠመቅ በፊት የሚያስፈልጉ ነገሮች
፩. ትምህርት፣
፪. እምነት ያስፈልጋል። ተጠማቂው በዕድሜ ከፍ ያለ ከሆነ የክርስትናን ትምህርት የተማረ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመነ መሆን አለበት። ጌታችን “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ብሎአልና። ማር ፲፮ ÷ ፲፮.
እምነት መሠረት ነው ሌሎች ተግባራት ግን ሕንጻዎች ናቸው። እምነቱን ለመግለጽ የማይችል ሕጻን ከሆነ ግን በወላጆችና በክርስትና አባቱ ወይም እናቷ ኃላፊነት ይጠመቃል። ካደገ በኋላ በኃላፊነታቸው ይመክሩታል ያስተምሩታል።
ለጥምቀት የተወሰነ ዕድሜ፡-ለጥምቀት የተወሰነ ዕድሜ ለወንዶች ፵ ቀን እና ለሴቶች ፹ ቀን ነው። ኩፋሌ ፬÷፱-፲፫ ሕፃኑ ሞት የሚያሰጋው ሆኖ ከተገኘ ግን ከአርባና ከሰማንያ ቀንም በፊት በሞግዚት ታዝሎ ሄዶ ይጠመቃል። ለመጠመቅ ቀኑ የደረሰውን ሰው ለነገ ብሎ ቀጠሮ መስጠትና በልዩ ልዩ ምክንያት ማሳደር አይገባም።
የጥምቀት ሥርዓት፡- ፩. ጥምቀት የሚደረገው በሥላሴ ስም ነው። የሥላሴን ስም ሳይጠሩ የተጠመቁት ጥምቀት ውኃ ተነክሮ እንደመውጣት የሚቆጠር እንጂ የሚሰጠው ዋጋ ወይም ጥቅም የለውም። ማቴ ፳፰ ÷ ፲፱
፪. ጥምቀት የሚፈጸመው በፈሳሽ ወይም በጥልቅ ውኃ ነው። የሚከናወነውም የሥላሴን ስም እየጠሩ “አጠምቀከ በስመ አብ፤ አጠምቀከ በስመ ወልድ፤ አጠምቀከ በስመ መንፈስ ቅዱስ” እያሉ ሦስት ጊዜ ብቅ፣ ጥልቅ እያደረጉ በማጥመቅ ነው። የማጥመቁ ሂደት ጥልቅ ውኃ በማይገኝበት ጊዜ ግን ውኃ በመቅዳት ወይም በእጅ በማፈስ ያጠምቁታል።
፫. አጥማቂው ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ነው፤ ስልጣነ ክህነት የሌለው ሊያጠምቅ አይችልም።
በማጥመቅ ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዓት የሚከተለው ነው።
ንኡሰ ክርስቲያን ማጥመቂያው የትንሣኤ ዕለት የሆነ እንደሆነ በሰሙነ ሕማማት፣ በሱባኤው ውስጥ ሰውነታቸውን ይታጠባሉ፤ ዐርብ ይጾሙና እሑድ ይጠመቃሉ።
ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ቄሱ ሲያጠምቁ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው፣ እጃቸውን ዘርግተው ይጸልዩለታል።
ቀጥሎ ልጅነት በሚያሰጠው መንፈስ ቅዱስን በሚያሳድረው በሜሮኑ ይጸለይበታል።
ከተጸለየበት በኋላ ለሌላ ቄስ ይሰጥና በተጠማቂዎች ቀኝ ያቆሙታል።
ወደ መጠመቂያው ከመግባታቸው አስቀድሞ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳመኑ ይናገራሉ። ማለትም “በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ታምናለህን?” እያለ እያንዳንዳቸውን ይጠይቃቸዋል። “አዎን አምናለሁ” እያሉ እያንዳንዳቸው ይመልሳሉ።
ከዚህ በኋላ ቅብዓ ቅዱስ ይቀቧቸዋል፤ ያጠምቋቸዋል፣ ልጅነትን ያሳድሩባቸዋል።
መናገር የሚችሉ ከሆነ ራሳቸው እምነታቸውን በመመስከር ጸሎተ ሃይማኖትን ያነባሉ። መናገር የማይቻላቸው ከሆኑ የክርስትና አባትና እናት ስለ እነሱ ሃይማኖታቸውን ይመሰክራሉ፤ ጸሎተ ሃይማኖት ያነባሉ።
የተጠማቂዎች ቅደም ተከተል ተራ፡-በመጀመሪያ የ ፵ና የ፹ ቀን ምፃናት ይጠመቃሉ፤ በኋላ ንኡሰ ክርስቲያን ወንዶች ይጠመቃሉ፤ በመጨረሻ ንኡሰ ክርስቲያን ሴቶች ይጠመቃሉ።
ተጠማቂዎች ከተጠመቁ በኋላ ካሕኑ ሜሮን ይቀቧቸዋል። ከዚያ በኋላ ቅዱስ ሥጋውን እና ደሙን ያቀብሏቸዋል። የክርስትና አባት እና እናትም አብረው ጾመው ቅዱስ ሥጋው እና ደሙ ይቀበላሉ።
በዕለቱ ክርስትና የተነሱ ከሌሎች ቆራቢዎች በፊት ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ። የምትጠመቀውን ሴት ንኡሰ ክርስቲያን ቅብዓ ቅዱሱንና ሜሮኑን ኤጲስ ቆጶሱ ከአንገቷ በላይ ከቀባ በኋላ ሌላውን ሰውነቷን የምትቀባው ዲያቆናዊት ሴት ናት።
በጥምቀት የሚገኝ ክብር፡- ከእግዚአብሔር መንፈሳዊ ልደት መወለድ ልጅነት ማግኘት፣ ከኃጢአት መንጻት ነው።
ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት (ጸሎተ ሃይማኖት) የእግዚአብሔር ፀጋ ለሰው ልጅ የሚሰጠው በጥምቀት ከሥላሴ ሲወለድ መሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት ተነግሯል። ዋቢ መጽሐፍ:- ሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያን በሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ

