ንጋት (ትረካ)

መፈገግ ከንጋት በኋላ ላለች ቀን ባህሪዋ ነው ምን ብትዳምን የምትረጨው ብርሃን የምታጋባው ሙቀት ባይኖራት እንኳን ጨርሶ አትጨልምም ያ ነው ማታ ከሚለው ስያሜ የሚለያት በእርግጥ ውስጧ የተሸከመቻቸው የሐሳብ ክምሮች በኗሪው ልቦና ውስጥ ወይ ብርሃን ወይ ጨለማ ያደርጋት ይሆን እንጂ ለንጋት ብርሃን የማጣት ባህሪ ማን ሰጥቷል ? ልብ ግን የፀሐይ መውጣት ሳያሞቃት የዝናቡ ውሽንፍር ቁብም ሳይሰጣት እንዳች ነገር እንደደፈነው ጆሮ ጥቂት ብቻ ኦያደመጠች እንዲሁ ሳታገናዝብ መኖር ትችል እንደሆን የሚጠይቅ ካለ የሰማ የሰፈር ሰው ሁሉ ምሳሌ ስጥ ቢባል እጁን ወደ እኔ ይቀስራል በእርግጥ እውነት ነው። እኔጋር ቀን አዘቅዝቃች የማሰላሰል እና ነገርን የማጤን ለዛ ካጣሁ ጊዜያት ከመቆጠር ዘለዋል “እንግዲ በተዋት ጊዜ ይተዋት” እያሉ የሚያዝኑልኝ ሰዎች ሁሉ የትላንት እኔነቴን እያስታወሱ አይናቸውን አይኔ ላይ ቀስረው ምራቅ ይመ’ጣሉ ።


አዎ ብቻ መሆንን ወድጄ እራሴን ከአብሮነት ገትቼ እራሴ ላይ ቆልፌያለሁ ስላጣኋቸው ነገሮች ሳስብ አለኝ የምለው መስመር እንኳን ሳስቶ ሊበጠስ የደረሰ ክር ይመስለኛል በቃ ለእኔ መቋጨት ያልቻለኩት የማቆም ጫፍ ቆሜ ለመፈጥፈጥ የፊሽካ ድምጽ የምጠብቅ አይነት ሰው ነኝ ለምን አትበሉኝ ምክንያቹን ልክ አይደለሽም ለሚለኝ ውስጠቴ እንኳን በቂ አይደሉም ለራሴ በቂ ያሆንኩና ያለኝ የተነጠቀብኝ ሰው እንደሆንኩ ብቻ ነው ሚሰማኝ በማለዳ ክፍሌ የምትገባዋ ፀሐይ ለመንጋቱ ምልክት ናት ከዚያ በዘለለ ሙቀቷ ሰርጾኝ አያውቅም እንደውም ታደክመኛለች ሌላ የማይገፋ ቀን ይዛብኝ ትመጣለች ሰውነቴ በግድ ወዲህ ወዲያ ይበል እንጂ በትርጉም የሚሰራው ስራ አልነበረውም ክፍሌ ራሴ ለራሴ እያለቀስኩ የቀበርኩባት መቃብሬ ሆናለች። ለነብሳቸው ያደሩ ቤተሰቦቼ ቢሰለቹም እንዳልሞት በግድ ይመግቡኛል። ሌላ በኑሮዬ የማስታውሳቸው ነገሮች ደሞ የጠያቂ ድምጾች ናቸው ” ያቺ ልጅ እንዴት ናት እንደው ምንም ለውጥ የላት” የሁሉም ሰው ወሬ መጀመሪያ ናት። ” አለች ምንም ለውጥ የላት እንደተለጎመች ይንን ሆንኩ እንዲህም ተደረኩ አትል ግራ የገባው ነገር ነው እኛም እኮ ተጨነቅን ” ይላሉ ለመጣ ሁሉ ።ለምጄዋለሁ አልጋዬ ላይ ያስቀረኝን ድባቴ ወድጄ ተገዛሁለት እሱም ወደሽ ከተደፋሽ እያለ ይረግጠኛል ።


ሌሊቱ ከድቅድቅ ጨለማ ጋር ቢሆንም ምን እንዳስፈነጠረኝ የማላውቀው ስሜት ከዘመናት አልጋዬ አስነስቶ መስኮት ላይ ገተረኝ ከአንዳድ የሰማይ ከዋክብት በቀር የሚታይ ነገር የለም ጸጥ ረጭ ያለ ጨለማ የቆምኳቸው ሰዓታት ቢበዙም የድካም ስሜት ግን የለኝም ጨለማ ወስጥ የዛለ ስጋዬን መቆሜ ውስጥ ደሞ የድሮ ትጋት እና ጽኑ ስሜቴ ውልብ አለኝ እንዲህ ስለትላንቱ ማሰቤ በራሱ ለራሴ አስገረመኝ ።የቆምኳቸው ቀናት እና ቦታዎች በአእምዬ ውስጥ በተርታ ተስሎ እንደቀረበ አውደ ርዕይ ይታወሱኝ ጀመር ሰዓታቱ ፣ ማኅሌቱ …..ሁሉ ልቤ ላይ ቀረ ግን ከጨለማ ጋር ነው ። ወዴትም ከማይወስድ ድቅድቅ ጋር የውስጤን ሀሳብ ገታውት ጨለማው እንዳሸነፈኝ አይነት ማስተባበል ነግሬ ጸጥ አደረግኩት ዝምታ። ጨለማ ብቻ። …ከውስጤ ዝምታ ግን የምታባንነኝ በክፍሌ ግርግዳ ተሰቅላ ሰኮንድ የምትቆጥር መስመር ነች ጥቂትነቷ ሳያግዳት ጊዜ የምትለካ ሁኔታ የምትለውጥ ጥቂት ባለ ሙሉ መስመር።


ሳብሰለስል ከቆየሁት ሀሳብ ያነቃኝ ደግሞ ግርማው የሚያስፈራው ጨለማ በወጋገን ላለመሸነፍ የሚያደርገው ትግል ነበር ለካ ከጥቂት ሰኮንድ ቆጣሪ የምትወጣ ድምጽ ብቻ ሳይሆን እይታም ምልከታም ጊዜን ይለውጣል የማይገፋ የሚመስል ጨለማን በብርሃን ይተካል አሁን ነጋ ብርሃን ብቻ ነው ያለው፤ ሙሉ ብርሃን ያልጠቆረ ያልዳመነ ሙሉ ንጋት።


ውጪ ውጪ አለኝ በቃ ይህንን ብርሃን ከተከለለ ክፍል ውጪ ሆኜ ላጣጥመው ፈለኩ ግን ፈራሁ ደሞ አንድ ልቤ አይኔን በሰዓቱ እየላከ እያለፈኝ ያለውን ዘመን ያስታውሰኛል እየገፋ ያበረታኛል። እየፈራሁ ከመታጠቢያው ክፍል ገባሁ ልብሴን አላወለኩም ቧንቧው ማውረድ የሚችለውን ያህል ራሴ ላይ ከፈትኩት አንዳች ነገር ከላዬ ተንዶ የወረደ መሰለኝ ቁምሳጥኑ ፊት ካለው ሙሉ መስታወት ፊት ቆሜ ራሴን ቃኘሁት እንዲህ ራሴን ከተመለከትኩ ረጅም ጊዜ ….ጊዜው በዛች በቀስቃሽ ሰኮንድ ቆጣሪ ከተለካ ደሞ ዘመን በሉት። በረዥም ቁመቴ ላይ ነጭ ረዥም ቀሚስ ለቀቅኩበት ረዥም ነጭ ነጠላ አጣፍቼ በአዘቦቱ ማክሰኞ ትንሳኤ እደሆነለት ሰው ከመቃብር ክፍሌ ወጣሁ ተሰብስቦ ቡና ሲጠጣ የነበረው ቤተሰብ ሁሉ በድንጋጤ ይሁን በመረበሽ ስሜት ከውጭ እንደመጣ እንግዳ ቆመው ተቀበሉኝ ” ወዴት ነው ማለቴ የትነሽ እንዴት ተነሳሽ ” የጥያቄ መአት መልስ አልሰጠሁም መውጣት ብቻ ነበር የፈለኩት ” ልከተልሽ ” አለች እህቴ ስስት በለበሰ ድምጿ ” አይ እመለሳለሁ ብቻዬን ይሻላል ” ማለቴ ብቻ ትዝ ይለኛል እንኳን ለቤተሰቤ ለራሴም ከአንደበቴ ቃል መውጣቱ አስደንቆኛል።

የቤቱንም የጊቢውን በር ተራ በተራ ከፍቼ ወጣሁ ልክ የመጀመሪያውን ልቦናዬ ክርችም በብርሃን ተሸንፎ እንደተከፈተ። ከቤታችን ሩቅ ወዳልሆነው የእመቤታችን ቤተክርስቲያን ያላዘዝኩት እግሬ እየመራ ወሰደኝ አጸዷ እንደድሮው አይደለም ዛፎቿ የሉም ግን ሰላሙ አለ ያ የሚያረጋጋ መንፈስ አለ ከሁሉ በላይ በዓይኔ የፈልኩት ያ የሚያየኝ ያህል የሚሰማኝን ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕልን ነበር አለ ከነመቀጫ ድንጋዩ። ተቀመጥኩ ዓይኔን ከዓይኗ ተክዬ አወራኋት ግን እያፈርኩ ግን እየፈራው ያስቀየምኳት ባዳ የሆንኩባት እናቴን ከዘመናት በኋላ ፊቷ ቁጭ ብዬ አየኋት ለካስ ናፍቃኝ ነበር መንፈሴ ተዋሃዳት።


ከዚህ ሁሉ መመሰጥ ውስጥ ግን ያነቃኝ የአንዲት እናት እልልታ ነበር ሁለት እጃቸውን ካለልክ ዘርግተው በታላቅ ድምጽ እልልልልሰ እያሉ ወደ ሥዕሏ ይመጣሉ ስለሚያያቸው ሰው ስለሚሰማቸው አካል ግድ የላቸው በመንታ የሚወርደው እንባቸውን ሳያብሱ እናቴ ክብር ይግባሽ ይላሉ ይህችን ብቻ እየደጋገሙ ከአጠገቤ ከሥዕሏ ፊት ተደፉ “ምን ተደርጎላቸው ነው ይለኛል ውስጠቴ ፊታቸው ላይ ያለ ደስታ ያፈለቀው እንባ ከተደፉበት መሬት ላይ ይንጠባጠባል ቀናሁ ማልቀስ አማረኝ እንደ እሳቸው ሞልቶልኝ እንዲህ እንባና ውዳሴን ማቅረብ አሰኘኝ እጃቸው አሁንም እንደተዘረጋ ነው። ከእኔ በስተቀኝ እጃቸውን በነጠላ ሸፍነው ፊታቸው ላይ ያገለደሙ ሁለት ሴቶች ይሾካሸካሉ አይናቸውን ሴትዬይቱ ላይ ተክለው ያወራሉ ” እኚህ ባለፈው ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሴትዮ አይደሉ እንዴ ” አንዷ ትጠይቃለች ” እኮ ገርመውኝ እኮ ነው ብታይ እንዴት እንደሚያሳዝኑ ምንም እኮ አልተረፈላቸውም አመድ ነው የሆነው ደሞ ልጃቸው ቢቃጠልም ይተርፋል ብለን ነበር ሆስፒታል ገብቶ ተስፋ ሰጥቷቸው በሁለተኛው ቀን ሞተ በስተእርጅና የወለዱት አንድ ልጃቸው ነበር” ያብራራችው ነገር እና የሴትዮዋ ሁኔታ አልገጥም አለኝ የምሰማው ድራማ እንጂ እውነት የተፈጸመ ታሪክ ነው ብሎ ማመን ከበደኝ የእሳቸው ጸሎት ሌላ የእነሱ ወቀሳ ሌላ። ” ታዲያ ይሄ ሁሉ ጉድ ወርዶባቸው የምን እልልታ ነው ?” ” እንጃላቸው የሰፈሩ ሰው ግን አእምሮአቸው ሳይነካ አይቀርም ይላል አንቺዬ ነገሩ የሆነ ለት አለቀሱ ከእዛ በኋላ ብቻቸውን ቢቀሩም ተመስገን ብቻ ነው የሚሉት ታድያ ይሄ በጤና ነው ” ግራ አጋቡኝ የማየው ከምሰማው አልዋሃድ አለኝ ጆሮዬን ወደሳቸው መለስኩ አሁንም በጉልበታቸው ወድቀው እጃቸውን እንደዘረጉ ናቸው ” እናቴ ሆይ ሁሉን ሞላሽልኝ የወሰድሽውም ቢሆን እኮ ያንቺ ነው እዚሁ ሥዕልሽ ፊት ተደፍቼ አልቅሼብሽ አይደል ልጄን የሰጠሽኝ ይህንን ያህል እኔ ጋር ከኖረ ይበቃል እንደፍቃድሽ በራሴ ያገኘሁት ምን አለ ሁሉ ባንቺ ነው የእኔ እናት ክበሪልኝ የአምላክ እናት ተመስገኚልኝ ምን እልሻለሁ” ይላሉ እየፈገጉ ።

እንዳሉት ጤናቸው አልታወከም እንዳሟቸውም አይደሉም ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ እንደተባለ እንጂ አሁን ያጣዋቸው ነገሮች ትርጉም አልሰጥ አሉኝ ለዘመናት ቤት ዘግቼ የደበትኩባቸው ኩነቶች አሁን እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም አፈርኩም ደግሞም ይህንን ለእኔ ስላዘጋጀ ሐሴት አደረኩኝ። አሁን የለበስኩት ያምርብኛል ትርጉም ይሰጣል ቆምኩ ዓይኔን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጌ ለዘመናት ከራቀኝ ፈገግታ ጋር ተመስገን አልኩ…..ሁሉን ውብ ማድረግ ታውቃለህና በምክንያት ትሰራለህና ሁሉ ካንተ ነውና ልዩ አድርገህ ፈጥረኸናልና አሁንም ተመስገን ።


ጸሐፊ – ሜላት ክብረት