ሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም( ሳማ ሰንበት)

ሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም
ሰንበትን የሰራት፣ በሰንበተ ክርስቲያን (እሑድ) መፍጠርን አሐዱ ብሎ የጀመረ፣ በሰንበተ ክርስቲያን ከሙታን ተለይቶ የተነሳ፣ በሰንበተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ልኮ ቤተክርስቲያንን የመሠረታት የሰንበት ጌታዋ (እግዚእ ለሰንበት) ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበተ ክርስቲያን ይህችን ዓለም ለማሳለፍ እንደሚመጣ አምናና ተዘጋጅታ የምትጠብቀው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን ለክርስቲያኖች ሁሉ የዘወትር ጉጉት የሆነውን የምጽአቱን ነገር ለማዘከር ከየዕለት አዋጇ ባሻገር በዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት በምልዐት በዓል አድርጋ ታነሳዋለች።


ይህ በዓል ከሚከበርባቸው አብያተክርስቲያናት አንዱ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ቤተክህነት የሚገኘው የሳማ ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት ገዳም ነው።


ገዳሙ ከግራኝ አህመድ በፊት በ1026ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በወቅቱ ደብረ ዘይት ይሰኝ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ጠፍ ደብር ሆኖ ከቆየ በኋላ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አያት በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን በድጋሚ ሲቀና ሳማ ተሰኘ።
የገዳሙን ታሪክ የሚያትቱ መዛግብት እንደሚናገሩት ገዳሙ በግራኝ አህመድ ዘመን ከጠፋ በኋላ የገዳሙ መሥራች የሆኑት አባ ገብረ ሕይወትና ሌሎች መነኮሳት ታቦተ ተክለሃይማኖትና ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ከጎንደር ወደ ሸዋ መጡ።


ገዳማውያኑ ገለልተኛ በዐት ሲፈልጉ አሁን ሳማ ሰንበት በሚገኝበት የምንጃር ሸንኮራ አካባቢ ከሚገኝ ጠቦ ከሚሰኝ ወንዝ ሸንተረሩ ላይ በዐት ፈልፍለው ጽሙና ያዙ።


በዚህ ወቅት ሙገሬ ዛላ በተሰኘው ጫካ አንድ ተዓምር ተከሰተ። ዛፍ ሊቆርጥ ወደ ጫካው የገባ አንድ ገበሬ ዛፍ ለመቁረጥ ሲሞክር እሳት እየነደደ አላስጠጋ ይለዋል በዚህ ወቅት ካህናት ተጠርተው የምሕላ ጸሎት ሲደረግ በሥፍራው ላይ ታቦተ እግዚአ ሰንበት ተገኘና አውጥተው ሁኔታውን ለንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አሳወቁ። ንጉሱም በጠቦ ወንዝ ሸንተረር ላይ ስለነበሩት መናንያን ሰምተው ስለነበረ ጽላቱ ለአባ ገብረ ሕይወት እንዲሰጥ በማዘዛቸው አባ ገብረሕይወት ተቀብለው ለረጅም ዘመን በዋሻቸው ዓመት እየቀደሱበት ቆዩ። በኋላ ላይም የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር አሑን ገዳሙ በሚገኝበት ደልዳላ መሬት ላይ ገዳሙን ገደሙ።

ገዳሙ ከዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ጋር ግንኙነት እንዳለውም ይነገራል። ገዳሙ ከሰንበተ ክርስቲያን ስም ጋር በተያያዘ የተመሠረተ ብቸኛው ቤተክርስቲያን ሲሆን በውስጡ በርካታ የብራና መጻሕፍት የሚገኙበት ነው። በየዓመቱም በእኩለ ጾም በበዓለ ደብረ ዘይት የሚከብር ሲሆን በአንድ ወቅት ገዳሙ ተቃጥሎ ነበር። ከቃጠሎው በኋላ በክብና በሰቀላ መልክ ሁለት ሆኖ ተሠርቶ በክብ መልክ በተሠራው ታቦተ ተክለሃይማኖት፡ በሠቀላው ደግሞ ታቦተ እግዚአ ለ ሰንበት ገባበት ። በምርቃቱ እለት የተገኙት የወቅቱ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ገዳሟን “ብሔረ ሕያዋን” ሲሉ ሰይመዋታል።