
አምላካችን እግዚአብሔር አዳምን ሊያድነው ፈቅዶ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› ብሎ ቃል የገባለትን በማሰብ ከትንሳኤ በኋላ ያለው ዕለተ ሐሙስ ‹የአዳም ሐሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ታድያ ይህ የአዳም ሐሙስ ዘንድሮ በ2016 ዓ.ም ለአዳም ተስፋው፡ ለሔዋንም መድኃኒቷ ከሆነችዋ ኢሳይያስ ከእሴይ በትር ውስጥ እንደምትገኝ ከነገረላት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ጋር በአንድ ቀን ውሏል።
ይሕ ሐሙስ አዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ዕለቱ ይከበራል፡፡ (ሉቃ. ፳፬ ፥፳፭-፵፱)
አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት በዕለተ ዓርብ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን አበው ሊቃውንት የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በማሰብ ዝክረ አዳም ሐሙስ እንዲከበር በወሰኑት መሠረት የሚከበረው የአዳም ሐሙስ አባታችን አዳም በተሰጠው የተስፋ ቃል የሁላችን ድኅነት ስለመፈጸሙ፣ አዳም ከነልጆቹ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለ መውጣቱ ይዘመራል።
ከገነት በኃጢአቱ ምክንያት የወጣው አዳም የተገባለትን የቃልኪዳን መፈጸም በጉጉት ይጠብቅና በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሲዖል ነጻ እስኪወጣ ተጨንቆ ለነበረው አዳም እመቤታችን ምልክት ነበረች። አዳምም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በተባለው መሰረት አምላኩ የሚወለድባትን የልጁን ልጅ መወለድ ዛሬ አገኘ።
አዳምና ሔዋን በንስሐ ተመላልሰው የተቀበሏትም ይኅችም ተስፋ፡ በሲኦል ውስጥ ለደረቀው አዳም መረስረስ እንዲሆንለት ለሰው ልጆች ዝናምን የምታሰጥ ደመና ናት።
አዳም እመቤታችን እስኪያገኝ ምን ያህል ናፈቀ? ምን ያህልስ ጓጓ? ነቢያት አምላካቸው እንደሚወለድ ይተነብዪት የነበረ ትንቢት የሚፈጸምባትን እናቱን እስከሚያገኟት ጓጉ። ለዓለሙ ሁሉ ደስታ እንደሆነ ቅዱስ ሉቃስ የጻፈለት አምላክ በማህጸኗ እንደሚያድር በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ሰማች። አዳም በሔዋን ምክንያት ያጣውን ገነት በእመቤታችን በኩል አገኛት። ተረግማና ደርቃ የነበረችው ምድር በልጇ በረከትን ለበሰች።
የእመቤታችን ለአዳም ተስፋ መሆን በጌታችን መወለድ ብቻ አላበቃምና ዛሬም፡ አዳም ተስፋ ሲያጣ ከእመቤታችን ይጠጋጋል። በእንተ ማርያም መሀረነ እያለ አምላኩን በእርሷ በኩል ይለምናል። የተሰጣትን ቃልኪዳን እያሰበ ምንም እንኳም ኃጥእ ብሆን ለእናትህ ስለገባህላት ቃልኪዳን ብለህ እያለ ይማጸናል። ከገነት ተራቁቶ በተሰደደ ጊዜ ልብስ ሆና እርቃኑን የሸፈነችለት እናቱን እያሰበም ዛሬም ድረስ በተስፋዋ ይኖራል።

