አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ

ትውልድ ሀገራቸው ጽላልሽ (ዞረ) ነው። አባታቸው ሮማንዮስ እናታቸው ማርታ ይባላሉ። አባታቸው ሮማንዮስ ቄስ ነው። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ናቸው።
በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ በጽላልሽ ረሀብ ፀንቶ ነበር። እሳቸው ግንቦት ፳፫ ቀን በመንፈቀ ሌሊት በልብሰ ብርሃን ተጠቅልለው ተወለዱ። ቤታቸው በበረከት ተመላ። ለሀገሬው ዝናብ ዘንቦለት ህዝቡ ከፃድቁ እናትና አባት የተመፀወቱትን ከፍለው ዘሩ። አቡነ ታዴዎስ በተወለዱ በ፵ ቀናቸው ሐምሌ ፪ ቀን ሲጠመቁ የተዘራው እህል አንድ ሳይቀር አፍርቶ ተገኝቷል።ዕድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ ለሊቀ ካህናቱ ለሕይወትብነ ሰጥተዋቸው ሲማሩ አደጉ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዳሞት (ወላይታ) ተሻግረው መተሎሚን አስተምረው “በእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ጸሎት መተሎሚን በሃይማኖት ወልጄዋለሁ። በምግባር አሳድጌዋለሁና እኅትህን ይዘህ በቶሎ ና!” ብለው ላኩባቸው።
እኅታቸው ትቤጽዮን ትባላለች። የመተሎሚን ወንድም ዝግናን አግብታ አባ ኤልሳዕን ወልዳለች። ከባሏ ተጣልታ ነበርና እሷን ከባሏ አስታርቀው እሳቸው አቡነ ተክለሃይማኖትን እያገለገሉ ፱ ዓመት ኖረዋል። በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲሄዱ እሳቸውም ወደ ጽላልሽ ተመልሰው ስለነበር አፄ ይኩኖ አምላክ “እንድትመክረኝ፣ እንድትገስፀኝ ከቤቴ ተቀመጥ!” ብለው ከቤተመንግሥት አስቀመጣቸው።
ሰይጣን ለፀብ ለምቀኝነት አያርፍምና ጠላ ቤቷን ክፉ የሚገድል ሽታ አሸተታትና ሞተች። አባ ታዴዎስ ወንዝ ገብተው ሲጸልዩ ሙቷ ተነሥታለች። ከዚህ በኋላ “ውዳሴ ከንቱ ይሆንብኛል” ብለው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተመለሱ። አቡነ ተክለሃይማኖት “ወደ ጽጋጋ (ጅጅጋ) ሂድ አሏቸው።” “ለምን? ቢሉ? አባ አኖሬዎስ ሄደው ሲያስተምሩ ያገሬው ሰዎች ደብድበው አስረዋቸው ነበርና እሳቸውን ለማስፈታት ነበር። የአካባቢው ንጉስ መዩጥ ይባላል። በነፋስ ሰረገላ ተጭነው ሄደው ከፊቱ ወርደው ሲቆሙ ደንግጦ “ከሰማይ መላእክት ነህ ወይስ ከሰው ወገን?” ቢላቸው። እኔ ከሰው ወገን ነኝ አሉት። ክርስትናንም አስተማሩት ጋኔን ከእሳት ላይ ጥሎት ሲሰቃይ የሚኖር ልጅ ነበረው አድነውለታል። ይህን አይቶ አምኖ ሕዝቡም እንዲያምኑና ክርስትናን እንዲቀበሉ አዋጅ ነገረ።
እንደ ሐዋርያው ታዴዎስ ፳፭ ግመል በመርፌ ቀዳዳ በተአምራት አሳልፈው በማሳየታቸው አፍጃል የሚባል የአንድ ባለጠጋ ልጅ በምትሐት እንደሚያደርጉት አድርጎ በመናገሩ ከግመሎቹ አንዲቱ ረግጣው ሞተ፤ ይህን ሙሳ የሚባል ልጅም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን ‘አልዓዛርን ከሙታን በአስነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም “ልጄ ና ተነስ!” ብለህ ይህንን መቋሚያዬን ወስደህ ከመቃብሩ ላይ አኑር! ‘  ብለው በአፍጃል ሰጥተዉት እንዳሉት ቢያደርግ አፈፍ ብሎ ተነስቷል። ይህን አይተው ሕዝቡ ሁሉ አምነዋል። ከዚህ በኋላ ሙሳን “ሙሴ” ብለው ሊቀ ካህናት አድርገው ፲፪ አብያተ ክርስቲያናት አሳንፀው አኖሬዎስን ይዘው ተመልሰዋል። አቡነ ተክለሃይማኖትም ከንጉሡ ተማክረው ሊቀካህናት ዘጽላልሽ ብለው ሾመዋቸዋል። ንጉስ ዓምደ ጽዮን ፍቅረ ዝሙት አድሮበት የአባቱን ቅምጥ ቢያገባት ሄደው ገሰፁት። በዚህ የተናደደች የንጉሱ ሚስት የኋሊት አሳስራ ከጥልቅ ገደል አሰጣለቻቸው። በዚህ ጊዜ የመቶ ሃያ ዓመት አረጋዊ ነበሩ። የታዘዘ መልአክ ገብረ እግዚአብሔርና ውቢት የተባሉ ደጋግ ሰዎችን አስነስቶ ስጋቸውን ወስደው ከበዓታቸው ቀብረው የተሰጣቸውንም ቃል ኪዳን በዳግማዊ አፄ ዳዊት ዘመን በሕዝቡ ፊት መስክረዋል። ንጉሥ ዳዊትም ዜና ገድላቸውን አጽፈዋል፤ ስጋቸውንም ወደ ከተማቸው በክብር አፍልሰው በተቀደሰ ስፍራ አኑረውታል።ከረድኤታቸው ያሳትፈን።