የበረከት ዳናዎች – መንፈሳዊ ጉዞዎች እንዴትና ለምን

ታላቁ የበረከት ጾም፣ ጾመ እግዚእ ሦስተኛ ሳምንቱን ጨርሶ ወደ አራተኛው ሳምንት እየተንደረደረ ይገኛል፡፡ በዚህ በዓቢይ ጾም በምእመናን ዘንድ ከሚስተዋሉ መንፈሳዊ ተግባራት አንዱ ደግሞ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ዓቢይ ጾም ደረስኩ ከማለቱ የአድባራትና ገዳማት ግድግዳዎች በመንፈሳዊ ጉዞ ማስታወቂያዎች ይመላሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዙሪያ አድባራና ገዳማት እስከ ግብጽና ኢየሩሳሌም ድረስ መዳረሻቸውን ያደረጉ ማኅበራትና ሰንበት ት/ቤቶች ምእመናንን በልዩ ልዩ መንገድ ይጣራሉ፡፡ በተለይ በጾሙ ወቅት ላይ የሚያርፈው የመጋቢት ፭ቱ የቅዱስ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ በዓልና በጾሙ እኩሌታ የሚከበረው የእግዚአ ለሰንበት በዓላት በርካታ ምእመንን ወደ ምድረ ከብድ፣ ዝቋላና ሳማ ሰንበት ያነጉዳል፡፡ እኛም ይህንን አስታከን በዛሬው ቤተክርስቲን ሳምንታዊ መሰናዶ ስለ መንፈሳዊ ጉዞዎች ማንሳት ወደናል፡፡

መንፈሳዊ ጉዞዎች ስማቸው እንደሚያመለክተው ለመንፈሳዊ ዓላማ ሲባል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የሚደረግ ጉዞን ይወክላል፡፡ ጉዞው በተጓዦቹ ፈቃድ የሚደረግ በመሆኑ ከስደትና ግዞት የሚለይ ሲሆን ዓላማው መንፈሳዊ በረከትና ትምህርት መሆኑ ደግሞ ለተዝናኖትና ለዘገባ ከሚደረጉ ጉብኝቶች ይነጠላል፡፡ ይህ ትርጓሜ ቅዱሳን ገዳማትን ለመሳለም ምእመናን የሚያካሂዱትን ጉዞ እንዲሁም አገልጋዮች የሚጓዙትን ሐዋርያዊ ጉዞዎች ያካትታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ መንፈሳዊ የጉዞ ታሪኮች ሲገኙ በተለይም እስራኤላውያን ወደ ምድረ ርስት ያደረጉት ጉዞ እንዲሁም ወደ ተለያዩ ሀገራት የተበተኑ እስራኤላውያን ለአይሁድ ፋሲካ፣ ለዳስ በዓልና ለበዓለ ኃምሳ የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያውያኑ የንግሥተ ሳባና የህንደኬ ጃንደረባ የቅዱስ ባኮስ ጉዞም ከመንፈሳዊ ጉዞዎች መካከል የሚካተት ነው፡፡
በዘመነ ሐዲስ ኪዳን የሐዋርያቱ አገልግሎት በውስን አካባቢ በመሆኑ እንዲሁም ቀጥሎ የነበረው ዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች በግድ የሚሰደዱበት እንጂ እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱበት፣ በአካል ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ባለመሆኑ በጉልህ ጉዞዎች ባይገኝም ወደ መንፈሳዊ ቦታዎች የሚካሄድ ጉዞ የክርስቲያን ሕይወት ተምሳሌት ሆኖ ይጠቀስ ነበር፡፡

መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያቱ እንዲሁም ሐዋርያነ አበው በትምህርቶቻቸው ላይ ክርስትና ወደ ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ አድርገው ማስተማራቸው መንፈሳዊ ጉዞን ከብሉይ ኪዳን በተለየ መልኩ በአካላዊ ቦታዎች ብቻ ያልተገደበ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን በዕለት ተዕለት ሥርዓተ አምልኮዋ ምእመናንን ከቤተልሔም ወደ ማዕከለ ቀራንዮ በመውሰድ ዳግመኛም “አልዕሉ አልባቢክሙ /ልቦናችሁን ከፍ ክፍ አድረጉ” እያለች በሰማያዊው ምሥጢር በኩል ወደ ሠማያዊው ሥርዓት እንዲገቡ ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡

በቀደመቺው ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ጉዞዎች የሚካሄዱት ጌታችን በነበረባቸው የቤተልሔም፣ ኢየሩሳሌም፣ ቀራንዮና መሰል አካባቢዎች ላይ ነበር፡፡ በ፪ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ያሉ እንደ ኦሪገን ያሉ ሊቃውንት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዙ ታሪክ ይዘግባል፡፡ በ፬ኛው ክፍለዘመን ክርስትና በተጎናጸፈው ነጻነትና ከፍታ ምክንያት በተለይም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስና በእናቱ ቅድስት እሌኒ አማካኝነት እየሩሳሌም በመታደሷና አብያተ ክርስቲያናት በመታነጻቸው መንፈሳዊ ገዞ ከቀድሞ በተሻለ መጠን ተበራክቷል፡፡

እንደ ኢየሩሳሌሙ ሊቀጳጳስ ቄርሎስ፣ እንደ ቅዱስ ጀሮም እንደእነ ቅድስት ሜላኒያ ያሉ ታላላቅ ቅዱሳንም በዚህ ወቅት ወደ ኢየሩሳሌም ማቅናት ችለዋል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ያለውን መንገድ የሚያሳየው ለዘመናችን ከደረሱ ጥንታዊና ወደ ኢየሩሳሌም የሚያቀና ፍኖትን የሚያሳይ ካርታ ቦርዲክስ በወቅቱ ዜና ሰማዕታት በብዛት ይነገር ስለነበር የሰማዕታቱን በረከት ለመካፈል በሮም ወደሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች ማለትም ወደ እስክንድሪያ፣ የአሁኗ ጣልያን፣ ቅርጥግና (ቱኒዚያ)፣ ሶሪያና የመሳሰሉት ይጓዙ ነበር፡፡ በዚሁ በ፬ኛው ክፍለ ዘመን በበረሃው ከዋክብት ቅዱስ እንጦስና ቅዱስ ጳውሎስ (አባ ጳውሊ) አማካኝነት የተስፋፋው ምንኩስናም ቢሆን ለመንፈሳዊ ጉዞ የራሱን አሻራ አሳልፏል፡፡

በኢትዮጵያ የነበሩ በርካታ ቅዱሳን አባቶችና ክርስቲያኖች በግብጽ ምድር አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌምና ግብጽ ይጓዙ የነበረ ሲሆን በፖለቲካ ችግር ወደ ግብጽ መሄድ በማይቻልባቸው ወቅቶች በሃገር ውስጥ በረከቱ ሳይቀርባቸው እንዲሳተፉ ለማድረግ ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ አምሳለ ኢየሩሳሌምን በሮሃ መገንባቱ ይታወቃል፡፡ በአሁን ወቅት ርእሰ አድባራት አክሱም ጽዮን ማርያምን፣ ቅዱስ ላሊበላን፣ ግሸን ማርያምን፣ ደብረ ሊባኖስንና የመሳሰሉትን በመጎብኘት በረከትን ለመካፈል ከቅዱሳኑ ረድኤት ለማግኘት፣ ያሳለፉትን መንገድ አብሮ ለመጓዝ በርካታ ምእመናን ወደ ቦታው ይጓዛሉ፡፡

ምንም እንኳን መንፈሳዊ ጉዞዎች ለብዙዎች በረከትና ሕይወት ቢሆኑም ከጉዞ አዘጋጆች የዕውቀት እጥረት፣ ግዴለሽነትና ከተጓዦች የመንፈሳዊ ጉዞ ዓላማን መዘንጋት አንፃር በርካታ ስህተቶች ሲፈፀሙ ይስተዋላሉ። ወደ ገዳማት በሚደረጉ ጉዞዎች መናንያኑን ከማወክ፣ ያልተፈቀደ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጀምሮ በመንፈሳዊ ጉዞ ስም ስካር፣ የአልኮል መጠጦች ሸመታ፣ ልዩ ልዩ ግብይቶችን መፈፀምና መንፈሳዊ ባልሆነ ሁኔታና ቦታ ማደርና የመሳሰሉት ችግሮች ሲፈፀሙ ይስተዋላል።

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለመንፈሳዊ ጉዞዎች ባነሳበት ድርሳኑ “ልብህ ሳይዘጋጅ ወደ ጎልጎታም ሆነ ወደ ደብረ ዘይት ብትወጣ ክርስቶስን አታገኘውም። ነገር ግን ልብህን ብታዘጋጅ ግን በቀጰዶቅያም ሆነህ ክርስቶስን ልታገኘው ትችላለህ” ብሎ እንደሚነገር በቅዱሳን ገዳማትና ቦታዎች የሚካሄዱ ጉዞዎች አስቀድሞ በጎ ፈቃድና መንፈሳዊ ዝግጅት ከሌለባቸው ከቱሪስት ጉብኝት የሚለዩና በረከት የሚያስገኙ አይሆኑም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውጪ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ግላዊ ትርፍ ለማካበትና ምእመናንን ለመቀሰጥ መንፈሳዊ ጉዞዎችን እያዘጋጁ መሆኑ የጉዞዎቹ ሌላ ችግር እየሆነ ይገኛል። በመሆኑም ምእመናን ወደ መንፈሳዊ ቦታዎች ከመሄዳቸው በፊት ስለጉዞ አዘጋጁ ማንነትና ምንነት፣ ጉዞው ስለሚያካትታቸው ተግባራትና በሚሄዱበት ገዳማትና መካናት ያሉ መመሪያዎችን ማወቅ ይገባል። ከምንም በላይ ግን ጉዞውን የሚሄዱት ከቅዱሱ መካን ለመባረክ በመሆኑ በዙሪያቸው ባሉ ሌሎች ተጓዦች በጎ ያልሆኑ ልማዶች እንዳይሰናከሉ ሊጠበቁ ይገባል።

በጾሙ ውስጥ ወደ ቅዱሳን መካናት ለምትጓዙ ሁሉ ሰናይ ጉዞን እየተመኘን ጽሑፋችንን ከመቋጨታችን በፊት በጾሙ ወራት ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከሀገር ውስጥ ወደ ሳማ እግዚኡ ለሰንበት (ሳማ ሰንበት)ና ከሀገር ውጭ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ጉዞዎች እንዲሁም በ፱ኛው ዙር ፍኖተ ሕይወት ወደ መቄዶንያ ለመጓዝ መጋቢት 28 ማቀዱንም ለመጠቆም ወደድን።

ጾሙን በመንፈሳዊ ተግባራት በርትተን ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ለጀመርነው ጉዞ የመንገድ ስንቅ የምንሰንቅበት ያድርግልን። መልካም ጾም! መልካም ጉዞ!