
የንስጥሮስ ክህደት በኤፌሶን ጉባኤ በ፬፻፴፩ ዓ.ም. ከተወገዘ በኋላ የክህደቱ ተከታዮች ፈጽመው ባይጠፉም፣ ንስጥሮሳውያን በብዛት ተሰራጭተው የሚገኙት በፋርስና በባቢሎን ቢሆንም በኤፊሶንና በቁስጥንጥንያም በመጠኑም ይገኙ ስለነበር እነርሱን የሚቃወሙ ደግሞ በብዛት ከእስክንድርያ ሌላ በቁስጥንጥንያም ይገኙ ነበር፡፡ የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ የሚቃወም አውጣኪ (Eutyches) የሚባል በቁስጥንጥንያ የአንድ ትልቅ ገዳም አበምኔት የነበረና “ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ሁለት አካል” የሚለውን የንስጥሮስን ትምህርት አጥብቆ በመቃወም እርሱ በተቃራኒው ወደባሰ ክህደት አመራ፡፡ በቁስጥንጥንያ አውጣኪ “ክርስቶስ አንድ አካል አንድ ባህርይ” አለው ብቻ ያስተምር ነበር፡፡ አባባሉ የቄርሎስን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ቢመስልም አውጣኪ ግን አንድ ባህርይ ሲል የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ብቻ ማለቱ ነበር፡፡ በአውጣኪ አባባል “ሁለቱ ባሕርያት ማለት የሥጋና የመለኮት ባሕርያት በተዋሐዱ ጊዜ የመለኮት ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ውጦታል አጥፍቶታል፡፡ ሥጋና መለኮት በተዋሐዱ ጊዜ በክርስቶስ ላይ የሚታየው የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው፡፡” ግን ልክ አይደለም። የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ የአውጣኪን ኑፋቄ ትምህርት እንደሰማ ወዲያውኑ ደብዳቤ ጽፎ ስሕተቱን በማስረዳት ከዚህ ስህተት በአስቸኳይ እንዲታረምና ይህንን ትምህርት እንዳያሰራጭ አስጠነቀቀው፡፡ አውጣኪም ትምህርቱን ማሰራጨት ባለማቆሙ የተነሳ ፓትርያርክ ፍላብያኖስ በስሩ የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳት ሰብስቦ በ፬፻፵፰ ዓ.ም. አወገዘው፡፡ አውጣኪ “የቄርሎስን ሃይማኖት ስለ መሰከርኩ እንጂ አንዳች ስሕተት ሳይኖርብኝ ያለ አግባብ ተወገዝኩ” ብሎ ለንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ቴዎድስዮስ አመለከተ፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱ ዓለም አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት እንዲሰባሰቡ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤው በኤፌሶን በ፬፻፵፱ ዓ/ም እዲደረግ በጉባኤው ላይ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢ እንዲሆን ተመረጠ። አውጣኪም ለጉባኤው ተጠርቶ እንዲያስረዳ ተጠየ። እሱም “እምነቴ ልክ እንደቄርሎስ ነው” በማለት የኤፌሶኑ ጉባኤ የወሰነውን የቄርሎስን ዐሳብ በውሸት አቀረበ። ጉባኤው ይህን ሰምቶ ከውግዘቱ ፈታው። የጉባኤውም ውሳኔ በንጉሠ ነገሥቱ በቴዎዶስዮስ ዳግማዊ ጸደቀ፡፡ ይህም ጸድቆ የቆየው ይህ ንጉሠ ነገሥት እስከ ሞተ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ፪ኛው የኤፊሶን ጉባኤ ከአለፈ ከአንድ ዓመት በኋላ በሐምሌ ወር ፬፻፶ ዓ.ም. ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ በድንገት ከፈረስ ወድቆ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ቴዎዶስዮስ ወራሽ ስላልነበረው ለአልጋው ቅርብ የነበረች ታላቅ እኅቱ ብርክልያ (Pulcheria) ነበረች፡፡ ብርክልያ ግን በድንግልና መንኵሳ ነበር፡፡ ሆኖም ብርክልያ ለሥልጣን ስለጓጓች ምንኵስናዋን አፍርሳ የሮም መንግስት የጦር አዛዥ ጄኔራል የነበረውን መርቅያን (Marcianus) አግብታ በነሐሴ ፬፻፶ ዓ.ም. እሱ ንጉሰ ነገስት እሷ ንግስት ሆነው የሮምን መንግስት ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ይህ የብርክልያ ምንኵስናን ማፍረስ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በተለይም በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። የሮሙ ፖፕ ግን ከአዲሶቹ የሮም መንግስት ነገስተ-ነገስታት ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት ጋብቻቸውን በማወደስ አጽድቆላቸዋል። በዚህም የተነሳ ከንጉሳዊው ቤተሰብ ጋር ወዳጅነት መሠረተ፡፡ብዙም ሳይቆይ ፖፕ ልዮን በአሳሰበው መሠረት ንጉስ መርቂያን ጥቅምት ፰ ቀን በ፬፻፶፩ ዓ.ም. ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲደረግ ለጳጳሳቱ ሁሉ ጥሪ አስተላለፈ፤ ጉባኤውም ኬልቄዶን እንዲደረግ ተወሰነ። በጉባኤውም ላይ ከ፮፻ በላይ የሚሆኑ ጳጳሳት ተገኙበት። በጉባኤውም ላይ የፖፕ ሊዮን ጦማር እንዲነበብ ተደረገ። በውስጡ አንድ አካል ሁለት ባህሪይ የሚል ክህደት ስለተገኘበት ዲዮስቆሮስ “አልቀበለውም” አለ።በጉባኤው የነበሩ ጳጳሳት ነገስታቱን ስለፈሩ ዝም አሉ፡፡ ዲዮስቆሮስና እርሱን ተከትለው የወጡት ጳጳሳት ጉባኤውን አውግዘው ሄዱ፤ ጉባኤውም እነርሱን አወገዛቸው። ንግስት ብርክልያም “ጉባኤውን የማትቀበለው እኛን በመናቅህ አይደል?” ብላ አስደበደበቺው፣ ጽህሙንም አስነጨችው፣ እርሱንም በግዞት አስላከችው። እርሱም የወለቀውን ጥርሱን የተነጨውን ጽህሙን ለእስክንድርያ “እንኩ የሃይማኖት ፍሬ” በማለት ላከላቸው፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ከሮሙ ቤተክርስቲያን ጋር ተለያይታ ቀረች። ጉናኤውንም “ጉባኤ ከለባት” አሉት፤ የውሾች ጉባኤ ማለት ነው፤ ጳጳሳቱ የነገስታቱን ፈቃድ ለመፈጸም ታድመዋልና፡፡ እንደ እኅቶቿ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔና ቀኖና አልተቀበለችውም፤ አትቀበለውም፡፡ ምንጭ፡- የቤተክርሰትያን ታሪክ በዓለም መድረክ

