
የስሟ ትርጓሜ ሰላም ፍቅር ማለት ነው። ለንጉሥ ሉክያኖስ ልጁ ነች እርሱም አባቷ ያማረ አዳራሽን ሠራላት መስኮቶቹንም ስምንት አደረገ ቅጽሩንም በዙሪያው ዐሥራ ሁለት አደረገ ማዕድንም ሠራላት። የወርቅና የብር የሆኑ ሣህኖችና ጽዋዎችንም አዘጋጀላት የሚያስተምራትም አንድ ሽማግሌ ሰው አደረገላት።
ከዚህም በኋላ በዚያች አዳራሽ ውስጥ አኖራት የሚያገለግሏትም ሦስት አገልጋዮችን በእርሷ ዘንድ አድርጎ ደጃፎችን በላይዋ ዘጋ መምህርዋም በውጭ ሆኖ ያስተምራታል።
ዕድሜዋም ሰባት ዓመት ሆናትና ያን ጊዜ ራእይን አየች በማዕዷ ላይ ርግብ ስትቀመጥ በአፍዋም የወይራ ቅጠል አለ ። በማዕዱም ላይ አኖረችው ሁለተኛም ንስር መጣ ከእርሱ ጋር አክሊል አለ በማዕዷ ላይም አኖረው። ደግሞ ቊራ መጣ ከእርሱ ጋራ ከይሲ አለ በማዕዷ ላይም አኖረው። ደነገጠችም ለመምህርዋም ነገረችው እርሱም እንዲህ ብሎ ተረጐመላት “ርግብ የሕግ ምልክት ናት የዘይቱም ቅጠል የክርስትና ጥምቀት ናት፣ ንስርም ድል አድራጊነት ነው አክሊልም ለሰማዕታት የሚሰጥ ክብራቸው ነው። ቊራ የንጉሥ ምሳሌ ነው ከይሲውም መከራ ነው አንቺም የክብር ባለቤት በሆነ ክርስቶስ ስለ ስሙ ትጋደዪ ዘንድ አለሽ” አላት።
ከዚህም በኋላ ይጐበኛት ዘንድ አባቷ ወደርሷ መጣና “ልጄ ሆይ ከመንግሥት ታላላቆች ለአንዱ ላጋባሽ እኔ እሻለሁ” አላት እርሷ ግን ከልቡናዬ እስተምመክር ሦስት ቀኖችን አባቴ ሆይ ታገሠኝ” ብላ መለሰችለት። አባቷም በሔደ ጊዜ በጣዖታቱ መሠዊያ ፊት ተነሥታ ቆመችና ስለጋብቻ የሚሆነውን ይገልጡላት ዘንድ ለመነቻቸው እነርሱም ምንም ምን ከቶ አልመለሱላትም።
ከዚህም በኋላ ዐይኖቿን ወደ ሰማይ አቅንታ “የክርስቲያን አምላክ ሆይ ወደምትፈቅደው ምራኝ” ብላ ጸለየች ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንዲህ አላት። “እነሆ ነገ ከጳውሎስ ደቀ መዛመርት አንዱ ወደዚች አገር ይመጣል እርሱም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቅሻል። በማግሥቱም ያ ሐዋርያ መጥቶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃት። በሦስተኛውም ቀን እንደቀጠረቻቸው አባቷና እናቷ መጡ እርሷም እንዲህ አለቻቸው “እኔ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ”።
አባቷም ሰምቶ በእርሷ ላይ ተቆጣ ወደ ከተማው መካከልም አውጥተው በጐዳና ላይ እንዲጥሏትና በፈረሶች እግር እንዲአስረግጧት አዘዘ። ወታደሮችም ንጉሥ አባቷ እንዳዘዘ አደረጉባት ግን ምንም ምን ክፉ ነገር ከቶ አልደረሰባትም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አባቷና እናቷ በአዩ ጊዜ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ መንግሥታቸውንም ትተው ለርሷ ወደተሠራው አዳራሽ ሔደው በውስጡ ተቀመጡ።
በጐረቤታቸው ያለ ንጉሥም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ርሳቸው መጥቶ ወደ መንግሥታቸው እንዲመለሱ ተናገራቸው። እነርሱም አልፈለጉም እርሱም መንግሥታቸውን ያዘ ቅድስት ኄራኒንም ይዞ አሠቃያት ከዚያም አንበሶችን፣ እባቦችን በላይዋ ሰደደ ምንም አልቀረቧትም ። ሁለተኛም በመጋዝ መገዛት በአንገቷም ውስጥ ታላቅ ደንጊያ አሥሮ ከባሕር ጣላት የክብር ባለቤት ጌታችንም ከዚህ ሁሉ አድኖ ያለ ጥፋት በጤና አሥነሣት።
ከዚህም በኋላ እርሷን ያጠመቀ ሐዋርያን አባቷ ጠርቶ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ ቊጥራቸውም ሦስት መቶ ሆነ ከዘመዶቹና ከሀገር ሰዎችም ብዙዎች ተጠመቁ።
ከዚህም በኋላ ከሀዲው ንጉሥ ኑማርያኖስ የቅድስት ኄራኒን ዜናዋን ሰማ ወደርሱም አስቀርቦ ቀላኒካ ወደሚባል አገር ወሰዳት። በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያት በበሬ አምሳል በተሠራ የነሐስ በርሜል ውስጥ ዘጋባት የክብር ባለቤት ጌታችንም ያንን በሬ ሰብሮ ቅድስት ኄራኒን ያለ ጥፋት በጤና አወጣት።
ከዚህም በኋላ ኑማርያኖስ ሙቶ በርሱ ፈንታ ሳፎር ነገሠ እርሱም የቅድስት ኄራኒን ዜና በሰማ ጊዜ ወደ ርሱ አስቀርቦ በእጁ ውስጥ በአለ በታላቅ ጦር ወጋትና ነፍሷን አሳለፈች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሞተ አስነሣት። ንጉሥ ሳፎርም በአየ ጊዜ እጅግ አደነቀ ሰገደላትም በጌታችን ኢየሱስም አመነ ። ከእርሱም ጋራ ከሀገር ሰዎች ብዙ ወገኖች አመኑ ቁጥራቸውም ሠላሳ አንድ ሺህ ሆነ።
ከዚህም በኋላ በዚያች አዳራሽ ውስጥ አባቷና እናቷ ዐረፉ እርሷን ግን አምላካዊት ኃይል ተሸከመቻት ወደ ኤፌሶን አገርም አድርሳት በዚያ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገች።
በፋርስ ነገሥታት በመቄዶንያ፣ በቀላኒካና በቊስጥንጥንያ ነገሥታት ፊት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከመሰከረች በኋላ ወደ ወደደችው ክርስቶስ ሔደች። የድልና የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያዊቷ ሰማዕት በቅድስት ኄራኒ በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ የነሐሴ 21 ስንክሳር።

