በዓለ ደብረ ቁስቋምእንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምዓመታዊ በዓል (ኅዳር ፮) አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!!

እመቤታችን ቅድሰት ደድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ አረጋዊ ዮሴፍንና ሰሎሜን አስከትላ ወደ ግብጽ ተሰዳ ደብረ ቁስቋም ላይ ያረፉበትን ኅዳር ፮ ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
                                                     
የእመቤታችን ስደት ወደ ግብጽ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለቅዱስ ዮሴፍ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊደግለው ይፈልገዋልና ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፡፡ ተመለስም ብዬ እስክነግርህ ድረስ በዚያ ኑር” ስለተባለ በዚያኑ ዕለት ሌሊት ስደት ጀምረዋል፡፡ በዚያውም “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የሚለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። ሆሴ.፲፩፥፩ ነቢዩ ኢሳይያስም “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል ብሎ ነበረ። ኢሳ.፲፱፥፩ ደመና እመቤታችን ስትሆን እግዚአብሔር የተባለው ደግሞ በተለየ አካሉ ሰው የሆነ ፡እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንደ ነቢዩ ቃለ ትንቢት ቀሊል ደመና እመቤታችን በጀርባዋ አዝላ የቀኑ ሐሩር የሌሊቱ ቁር እያቃጠላት ወደ ምድረ ግብጽ ተሰደደች፡፡
    የእመቤታችን ስደት ወደ ኢትዮጵያ  የእመቤታችን ስደት ወደ ኢትዮጵያም ነበረ፡፡ ነቢዩ ዕንባቆም “እግዚአብሔር ከቴማን፣ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል፡፡ ክብሩ ሰማያት ከድኖአል፡፡ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል፡፡ ጸዳሉም እንደ ብርሃን ነው፡፡ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፡፡ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል፡፡” ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱሱ ከፋራን ተራራ ይወጣል እንደተባለ የፋራን ተራራ የተባለች እመቤታችን ናት፡፡ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይከፍት ወደ ማኅፀኗ ገብቶ ሳይከፍት ወጥቶአልና፡፡ በመቀጠልም “ፍለጋውም ከዘላለም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ”። ዕንባ.፫፥፫-፯ ያለው እመቤታችን ጌታን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ በተሰደደች ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ ጠባቂዋ ዮሴፍ እመቤታችንና ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ኖሩ፡፡ (ወላዲተ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ፤ ገጽ ፻፬)፡፡
  በጠቅላላው እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ብዙ መከራ ተቀብላለች፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ “ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን ከርሱ ጋር ከሀገር ወደ ሀገር ስትሸሺ ካንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ከዐይኖችሽ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር ዕንባ አሳስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ረሃቡንና ጥሙን ችግሩንና ሀዘኑን ከርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ቁጥር ፻፷፯

የቁስቋም ተራራ ደብረ ቁስቋም በደቡብ ግብፅ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ደብረ ቁስቋም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍንና ቅድስት ሰሎሜን ይዛ ከስደት ሲመለሱ ያረፉበት ቦታ ነው፡፡(ማቴ.፪፥፲፱-፳)
    በየዓመቱ ኅዳር ፮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእነርሱን ስደትና ወደ ሀገራቸው እስራኤል መመለሳቸውን በማስታወስ ታከብራለች፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ፡ ሄሮድስ ጌታችን ኢየሱስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ዮሴፍ በሕልሙ “ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ” ባለው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፭)