📖መጻሕፍትን ሾለ ማንበብ – በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

📖መጻሕፍትን ሾለ ማንበብ – በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን መጻሕፍት ለሰው ልጆች የተሰጡት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ እንዲርቅ ስላደረግነውና እግዚአብሔርን መስማት የምንችልበት መንፈሳዊ ጆሮ (እዝነ ልቡና) በማጣታችን ምክንያት ነው (ማቴ.፣ ድር. 1፡1)፡፡

ቃሉን በልቡናችን መጻፍ ስላቃተን በጽላትና በወረቀት ተጽፎ የተሰጠን ነው (ዝኒ ከማሁ)፡፡

አንድ ሰው በአጠገቡ ለሌለ ወዳጁ ደብዳቤ እንደሚጽፍለት ኹሉ፥ እግዚአብሔርም ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ከእርሱ ለራቀው ለሰው ልጅ የላካቸው ደብዳቤዎች ናቸው – ቅዱሳት መጻሕፍት (ዘፍ.፣ ድር.2፡4)፡፡

ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር ወደ አዳም መጥቶ ካነጋገረው፣ ቃኤልን ከገሠጸው፣ ከኖኅ ጋር ከተነጋገረው፣ የአብርሃምን ደግነት ከተቀበለበት አንጻር ኹለተኛ አማራጭ ናቸው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚህ ምድር ሲመጣ የሰው ልጆችን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ እንደ መጀመሪያው አፍ ለአፍ እንዲያናግራቸው ነበር (ማቴ.፣ ድር.1)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በመጣ ጊዜ የነገራቸውን እንደሚያስታውሳቸው እንጂ የተጻፈ ነገር አለመስጠቱም ይህን የሚያስረዳ ነው (ዮሐ.14፡26)፡፡

ዳግመኛም ነቢያቱ “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እኾናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይኾኑኛል” ብለው ትንቢት የተናገሩትም ለዚህ ነው (ኤር.31፡33)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም “ሥጋ በኾነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ” ያለውም ይህን እንደሚያስረዳ ሊቁ ያብራራል (2ኛ ቆሮ.3፡3)፡፡

ስለዚህ መጻሕፍት የተሰጡት በኹለት መሠረታዊ ምክንያቶች እንደ ኾኑ ሊቁ ያብራራል፡-

☞ የመጀመሪያው በጊዜ ሒደት አንዳንዶች ከመሠረታዊው ትምህርተ ክርስትና ፈቀቅ እያሉ ስለ ኼዱ ነው፡፡

☞ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ማለትም በምግባራቸው ንጽህናቸውነን እያቆሸሹ ስለ ኼዱ ነው፡፡

በመኾኑም መጻሕፍት ሲሰጡ እነዚህ በሃይማኖትም በምግባርም ከእውነት ወደ ሐሰት፣ ከጣባቢቱ ወደ ሰፊይቱ መንገድ ፈቀቅ ያሉትን ለመመለስና ሌሎችም ወደዚያ እንዳይሔዱ ለማስታወስ የተሰጡ ናቸው (ሉቃ.1፡1-4)፡፡

ከላይ ከተመለከትነው መረዳት እንደሚቻለው መጻሕፍትን ማንበብ የሕይወት (የድኅነት) ጉዳይ እንጂ የአማራጭ ጉዳይ እንዳልኾነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለሊቀ ጳጳሱ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ መጻሕፍትን ስለ ማንበብ፡- “እስክመጣ ድረስ በማንበብ ተጠንቀቅ፤ በማንበብ ተወስነህ ኑር” ካለው በኋላ ምክንያቱን ሲነግረውም፡- “ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ” ያለውም ለዚህ ነው (1ኛ ጢሞ.4፡16)፡፡ ጳጳስ ቢኾንም፣ ሕመምተኛ ቢኾንም ከእናቱና ከሴት አያቱ እንደ ለመደው ማንበብ ነበረበትና !

ሊቁም፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥንቃቄና በብልሐት የምናነብ ከኾነ እውነተኛውን ሃይማኖትን እንደምንማር መንፈሳዊ ሕይወትንም መምራት እንደሚቻለን አሰተምሯል (ዮሐ.፣ ድር.30)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በተቀመጠበት ላይ ዲያብሎስ ወደዚያ መቅረብ ካልተቻለው፥ ቃሉ በእኛ ዘንድ ሲኖርም አጋንንት ወደ እኛ አይቀርቡም፡፡

ክፉ ሰሚዕ ብሎም ርእይ አጋንንትን ወደ እኛ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ኹሉ፥ ደግ ሰሚዕ ብሎም ርእይም ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንድናገኝ ያደርጋል (ዮሐ.፣ ድር. 32)፡፡

ስለዚህ ከዚህ ከለመለመ የአበባ መስክ እንደ ንብ መቅሰም ፍሬውንም በየጊዜው መብላት እጅግ ያስፈልጋል (ሐውል.፣ ድር. 1)፡፡ ከምግበ ሥጋ ረሃብ ይልቅ ቃለ እግዚአብሔርን መራብ ይከፋልና፤

ቅዱሳት መጻሕፍት ማለት የመድኀኒት ሳጥኖች ናቸው፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ለሚያጋጥመው ማንኛውም ዓይነት መከራና ኀዘን ወደ እነርሱ ኼዶ መድኀኒትን ለራሱ ሊወስድ ይገባል (ቆላ.፣ ድር.9)፡፡

ጠላታችን ዲያብሎስ ረቂቅ ነው፡፡ እርሱን ድል የምናደርግበት መሣሪያም ረቂቅ ሊኾን ይገባል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ረቂቃን መንፈሳዊ ትጥቆች ናቸው፡፡ እነዚህን አለመታጠቅ ማለት ወደ ጦር ሜዳ ያለ ትጥቅ እንደ መኼድ ነው (ቆላ.፣ ድር.9)፡፡ ማደግ የምንችለው እነዚህን በአግባቡ ስንታጠቅ ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት መብራቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መብራቶች የማይጠቀም ሰው በምንፍቅናና በምግባር ጨለማ ይጓዛል፡፡ ቢደክምም እንኳን ድካሙ ረብ የለሽ ድካም ይኾንበታል (ሮሜ.፣ መቅድም)፡፡

ለክርስቲያኖች ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማንበብ እጅግ ውርድት ነው፡፡ አሕዛብ ስለ ፈረስ ግልቢያ ቢጠይቁአቸው የተጨዋቾቹን ስም፣ ጨዋታው የሚካኼድበት ከተማ፣ የተጨዋቾቹ ብቃት፣ ከተጫዋቾቹም አልፈው ስለ ፈረሶቻቸው ሳይቀር ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በቤ.ክ. የሚካኼደውን ነገር የማያውቁ ክርስቲያኖች ግን አሉ (ዮሐ.፣ ድር. 32)፡፡

እንደ ሊቁ አነጋገር ለስሕተት ትምህርት መግነን፣ ለአሕዛባዊ ሕይወትም መበራከት ተጠያቂዎቹ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች እውነትን ይዘው እውነት እንድታበራ ማድረግ ሲገባቸው ተውጠውና በቸልታ ስለሚኖሩ ከላይ የጠቀስናቸው እንዲበዙ አድርጓቸዋል፡፡

አሕዛብ አንድ የሚወዱት ተጫዋች ሲዘለፍ ዝም አይሉም፡፡ ስለ ተነቀፈው ዘፋኝ ወይም ተጫዋች ይከራከራሉ፡፡ ነቃፊውን ያሳምኑ ዘንድም ረዘም ያለ ክርክርን ያደርጋሉ፡፡ ክርስቲያኖች ግን በክርስትና ላይ እንደዚህ ያለ ነቀፋ ሲደርስ ወይ አብረው ይስቃሉ፤ ወይም አንገታቸውን ደፍተው ዝም ይላሉ፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀሰቅስ ነው (ዮሐ.፣ ድር. 17)፡፡

መጻሕፍትን አለማንበብ ክሕደት የተባለ ልጅ እንዲወለድ፣ የተበላሸ ሕይወት እንዲኖር፣ እንደዚሁም ነገሮች ኹሉ ምስቅልቅላቸው እንዲወጡ ያደርጋል (ሀብታምና ድኻ፣ ድር. 3)፡፡

ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ የድኅነት – የዘለዓለም ሕይወት ጉዳይ መኾኑን በመገንዘብ ዕለት ዕለት ማንበብና መዳናችንንም መፈጸም ይገባናል !

✞ ይህን እንድናደርግ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ያድለን፥ አሜን !
(ጥንቅር ገብረ እግዚአብሔር ኪደ)

🏡በማኅበራዊ መገናኛዎቻችን ቤተሰብ ይሁኑ!
የዩቲዩብ ቻናል፡
http://youtube.com/@EMislene
የቴሌግራም ቻናል፡
https://t.me/EMislene
የፌስቡክ ገጽ፡
https://www.facebook.com/EMislene/
የኢንስታግራም ገጽ፡
https://www.instagram.comS/egziabher_meslene28/
የቲክቶክ ገጽ፡
https://www.tiktok.com/@egziabhermeslene28
ድሕረ ገጽ፡
www.debregelila.org