
እንኳን ለኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ በአጤ (ዐፄ) ሱሱንዮስ አንገቷን ተሰይፋ ሰማዕት ለሆነችና ታላቁን ገዳም ራማ ኪዳነ ምሕረትን ላቀናች ለታላቋ ለጻድቅ ወሰማዕት ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ለዕረፍቷ በዓል በሰላም አደረሰን (የካቲት 29) ።
በጎንደር ክፍለ አገር ደራ ፎገራ አንበሳሜ ወረዳ ልዩ ስሙ አቡነ ሐራ ገዳም አጠገብ ኮክታ ማርያም ተብሎ በሚጠራው ቦታ ውስጥ ተወለደች፡፡ዛሬም ይህ አካባቢ እመ ምዑዝ መንደር ይባላል፡፡የአባቷ ስም ቅዱስ ላባ የእናትዋ ስም ቅድስት ወንጌላዊት ይባላል፡፡ እነዚህም ወላጆቿ እጅግ ደጋግ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለተራበ፣ ለተጠማ የሚያዝኑና የሚራሩ እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ በጎ ምግባር ያላቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን በረከት ሁሉ በሥራ ላይ የሚያውሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ ስላልወለዱ ወደፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ ቸር አምላክ ስለሆነ እንደ ቅድስት ሐና እመ ሳሙኤል ጸሎታቸውን ሰምቶ የተመረጠች ደግ ሴት ልጅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በሚያዚያ 4 ቀን ተፀንሳ ታኀሣሥ29 ቀን ከእነሱ ተወለደች፡፡ ስመ ጥምቀቷ ማርያም ጸዳላ የዓለም ስሟ ሙዑዚት ሲሆን ሙዑዚት ማለት ጣፋጭ ማለት ነው፡፡ (ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ደግሞ የቆብ ስሟ ነው።)
በተወለደችም ጊዜ በእግርዋ ቆማ “በማኀየዊ ቸርነትህ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኸኝ ለአብ ምስጋና ለወልድ ምስጋና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል” ብላ አመሰገነች ከእግዚአብሔር የተላከ መነኵሴም ወደ እርሷ በመሄድ የዳዊትን መዝሙር፣ መጻሕፍትንና የቤተክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ አስተምሯታል፡፡
ቅድስት እናታችን አምላኳን አስከ መጨረሻው በድንግልና ማገልገል ብትፈልግም ዕድሜዋ ከፍ ሲል ቤተሰቦቿ ዘርዐ ክርስቶስ ከሚባል አገረ ገዥ ጋር በቤተክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል አጋቧት ፡፡ እርሷ ግን በጫጉላ ቤት ሳሉ በእኩለ ሌሊት ባሏን “ወንድሜ ሆይ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ድንግልናችንን እንጠብቅ” አለችው፡፡ እርሱም “እሺ” ብሏት ይህንን ተመካክረው በጸሎት ሲተጉ አደሩ፡፡ ለእግዚአብሔር እየተገዙ በጾም በጸሎት በንጽሕናና በድንግልና ኖሩ በሌሊትም ወደ፡ባሕር ውስጥ እየገቡ ጸሎት ያደርጉ ጀመር፡፡ በመጨረሻም እርሷ በጳጳሱ በአባ ማርቆስ እጅ ስትመለኵስ ባሏም ድንግልናውን እንደጠበቀ በሰማዕትነት አንገቱን ተሰይፎ አርፏል፡፡ እርሷ በነበረችበት ዘመን ንጉሥ ሱስንዮስ “ሁለት ባሕርይ” የሚለውን የረከሰ የሮማውያንን ሃይማኖት ሕዝቡ ሁሉ እንዲያምን በማወጁ ምክንያት በአገራችን ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት ግጭት ስለተነሣና ከ8ሺህ በላይ ክርስቲያኖች በግፍ ተጨፍጭፈው ሲያልቁ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከእነ አቡነ ስምዖንና ከሌሎችም ቅዱሳንና ቅዱሳት ጋር ተሰልፋ ሰማዕትነትን ተቀብላ ለሃይማኖትዋ ምስክር ሆናለች፡፡ ባለቤቷ ዘርዐ ክርስቶስም በሰማዕትነት ዐርፎ ሰባት አክሊላት ወርደውለታል፡፡
እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሱስንዮስ በአደባባይ ሲያስገርፋቸው ሥጋቸው እየተቆራረጠ መሬት ላይ የወደቀውን የሰማዕታቱን ሥጋቸውን ሰብስባ “ይህን ለንጉሡ እጅ መንሻ ስጡልኝ” ብላ ላከችለት፡፡ “ይህ የየሃይማኖት ፍሬ ነው፡፡ እኛስ አስከአሁን በሃይማኖታችን አለን፣ አንተ ብትገለን መከራም ብታደርስብን ሃይማኖታችንን አልካድንም፡፡ ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ከሞት አስነሣን ይህን የሥጋዬን ቁራጭና የእህቶቼን የደናግላንን ሥጋ ብላው ፣ ደማችንን ጠጣ ሃይማኖትህ የከፋ፣ ሰነፍ፣ የረከስህ ነህ” ብላ ልካለታለች፡፡ መልእክተኞቹም ለንጉሡ ወስደው ሰጥተውታል፡፡
ሱስንዮስ አዋጁን እንዳወጀ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖንም ካህናትንና ክርስቲያን ልጆቻቸውን አነሳስተው እያስተማሩና እያጠነከሩ እያለ በጦር ተወግተው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ስምዖን በሰማዕትነት ከማረፋቸው በፊት ግን እነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ፣ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስን፣ ቅድስት አካለ ክርስቶስን፣ ቅድስት እመ፡ወተትን … ወዘተ አነሳስተው ንጉሡን መክረውታል፣ ገሥጸውታል፣ ንጉሡ ግን ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን የሃይማኖቷን ጽናት ስላየ ሥጋዋ እየተቆረሰ መሬት ላይ እስኪወድቅ ድረስ በብረት በትር አጥብቆ ያስገርፋት ጀመር፡፡
በመጨረሻም ምድር እየሰወረቻት ለመግረፍ የማይመቻቸው ቢሆን ከሌሉቹ ሰማዕታት ጋር አንገቷን በሰይፍ አስቆርጦታል፡፡ በዚህም ጊዜ ፍጹም ጨለማ ሆኖ ምድርም ተነዋወጠች፡፡ ስምንት ሺህ ዐሥር ቅዱሳንም በሰማዕትነት ዐረፉ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን አንገቷን በሰይፍ ቢቆርጧትም ነገር ግን ቅዱስ ሚካኤል ገነትንና ሲኦልን አሳይቶ 14ቀን በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከተቀመጠች በኋላ እንደገና እንደተኛ ወይም ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ከሞት አስነሥቶ ወደ ቦታዋ መለሳት፡፡
እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤልም ከሞት ካስነሣት በኋላ መናኝ ሆና በየገዳሙና በየአድባራቱ እየሄደች ዓለምን ስትዞር ያቀናቻቸው ብዙ ገዳማት አሉ፡፡ ለምሳሌ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ በሆኑት በአባ ጉባ ተመሥርታ በግራኝ ወረራ ጠፍታ የነበረችውን ራማ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምን አቅንታ የወንድና ሴቶች መነኰሳት በጋራ አብረው ይኖሩ የነበረ ቢሆንም የበጎ ሥራ ጠላት የሆነው ሰይጣን በማኀበረ መነኰሳቱ መካከል ሊፈጥር ያለውን ክፉ ፈተና ለእናታችን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተገልጾላት በገዳሟ ውስጥ የወንዶችና የሴቶች መነኰሳት መኖሪያ የተለያየ እንዲሆን አድርጋለች፡፡
ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌምም በመሄድ ላይ ሳለች በመንገድ ሰውን የሚበሉ ፍጡሮች ወደሚኖሩበት አካባቢ ስትደርስ 60 የሚሆኑ አገልጋዮቿን ለመብላት ይዘው ሳር ቅጠል እንዲበሉ በማድረግ ዓይናቸውን በጉጠት በማውጣት ለወራት በጨለማ ቤት ውስጥ ዘጉባቸው ሰይጣንንም ያመልኩ ነበርና ከ4 ወራት በኋላም በዓል አድርገው ለመብላት ከእሳት ውስጥ ጨመሩአቸው፡፡ እነርሱ ግን ምንም አልሆኑም፡፡ ያን ጊዜም “እናንተ ሰዎች ምንድን ናችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡ ቅድስት እናታችን ፍቅርተ ክርስቶስም ክርስቲያን መሆናቸውንና እነርሱ የሥላሴ ሕንጻ የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንደሌለባቸው ብትመክራቸው “ምን እንበላለን?” አሏት፡፡ እርሷም ከራማ ኪዳነ ምሕረት ስትነሳ የእህል ዘርን ለአገልጋዮቿ አስይዛ ስለነበር ከዚያ ስንዴ ወስዳ ዘራችው፡፡ስንዴውም በአንድ ቀን ተዘርቶ በቅሎ፣ ታጭዶ፣ ደርቆ፣ ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡
ቅድስት እናታችንም ቀምሳ ስታቀምሳቸው እንደማር እንደ ወተት የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም እንደዚህ እያደረጉ እየሠሩ እንዲበሉ አስተምራ አስጠምቃቸው ስድስት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርታላቸዋለች፡፡ወንጌልን፣ ስንክሳርን፣ ሃይማኖተ አበውን፣ ግንዘትን፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ አርጋኖንን ሁሉ በእጅዋ ጽፋ አስቀመጠችላቸው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጣላት በልጅዋ ምክንያት ስለ ደረሰባት ሀዘኖች አውርታላታለች፡፡ የፈለገችውንም እንድታደርግበት በእጅዋ ያለውን መስቀል ለቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሰጥታታለች፡፡ በዚህም መስቀል ባሕር ከፍላ ደቀ መዛሙርቶቿን አሻግራለች፡፡
እናታችን የአባታችን የአባ ኤዎስጣቴዎስን ገድል በማንበብና በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እርዳታ ባሕሩን በአጽፏ ተሻግራ ወደ አገረ ናግራን ሄዳለች፡፡ እንዲሁም በበትረ መስቀል እንደ ዘርዐ ቡሩክ ከባሕር ውስጥ የሰጠሙ የደቀ መዛሙርቶቿን መጻሕፍት ምንም ሳይሆኑ ማውጣት ችላለች፡፡ በሁሉም አገር እየዞረች ቅዱሳት መካናትን ትሳለም ነበር፡፡ ደብረ ደሞ ሄዳ “ሴቶች መውጣት አይችሉም” ቢሏት በሀዘን ስታለቅስ ቅዱስ ሚካኤል በሥውር ወስዶ አድርሷታል፣ አቡነ አረጋዊም ተገልጸውላት ባርከዋታል በዚያም ሥጋ ወደሙን ተቀብላለች፡፡
እናታችን ወደ ኢየሩሳሌምም ሄዳ ቅዱሳት መካናትን እየተሳለመች ለ7 ዓመታት ቆይታለች ቅዱስ ሚካኤልም በዓምደ ብርሃን እየመራት ተመልሳ ወደ አገራችን መጥታ በድጋሚ ከሱስንዮስ ጋር ተሟግታለች፡፡ ሙታንንም እያስነሳች እንዲመሰክሩላት ብታደርግም እርሱ ግን ከጥፋቱና ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም ነበር፡፡ የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ መልእክቷንም በንስር አሞራ አድርጋ እየላከች ትመክረው ነበር ፡፡
በአንድ ወቅትም በአገራችን እህል መታጣት ሆነና ቅድስት እናታችን ዝክር የምታደርግበት እህል አጣች፡፡ደናግል ልጆቿንም ጠርታ ትንሽ ዱቄት እንዲያመጡላት ነግራቸው በእርሱ ጸሎት አድርጋበት “ወደ ቦታው መልሱት” አለቻቸው፡፡ በማግስቱም እንሥራው ጋኑ ሁሉ በዱቄት ተሞልቶ አግኝተውታል፡፡ የካቲት ኪዳነ ምሕረትንም በዓል በደስታ አክብረዋል፡፡ መልአኩም ከቅድስት አገር ኢየሩሳሌም መልሶ ወደ ኢትዮጵያ ካመጣት በኋላ ዛሬ ገዳሟ ካለበት ቦታ ስትደርስ ከቦታዋ ላይ ዓምደ ብርሃን ተተክሎ በቀስተ ደመና ተከቦ አይታ “ይህች ቦታ ምንታምር” ብላ ጠራቻት፡፡
በቦታውም ላይ በመድኃኔዓለም ትእዛዝ የቅድስት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀን ታህሣሥ14 ቀን በዕለተ ዓርብ ጧት በሰንሰል (በስሚዛ) እንጨት ጀምራ ማታ እንደተፈጸመ በ3ኛው ቀን እሁድ ታህሣሥ16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር በድርገት (በቁርባን) ጊዜ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አእላፋት መላእክት ጋር ወርዶ መቅደሱን ሲባርክ መቅደሱ በ4ቱ ማዕዘን ለጌታ ሰገደ። ለጌታ እንደ ሰገደ ዛሬም ድረስ ይታያል ጌታችንም “ይህ መቅደስሽ ሳይፈርስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ይቆይልሻል፡፡ በዚህ ቦታ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ኃጢአቱ ይሰረይለታል፡፡ በምድርም ስምሽን የጠራ፣ መታሰቢያሽን ያደረገ፣ የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ የተረጐመ ሁሉ ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቡና ያልታሰበውን ለነዚህ ሁሉ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ፡፡ ከሩቅም ከቅርብም ከቀኝም ከግራም መጥቶ መቅደስሽን ለተሳለመ ሁሉ እስከ 12ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ፡፡ላልምረው ቦታችን አላስረግጠውም፡፡ በረከቴም በእሱ ላይ በልጆቹም በንብረቱ ላይ ለዘለዓለሙ ይኖራል፡፡ ስለጾምሽ፣ ስለጸሎትሽ፣ ስለተጋድሎሽ፣ ስለ ስግደትሽ ሰባት አክሊል ሰጠሁሽ” አላት፡፡
ፃድቋ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ብዙ ገድል በሠራችበት ብዙ መነኰሳይያትን በአቋቋመችበት ገዳሟ በእመ ምዑዝ ኪዳነ ምሕረት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድነት ገዳም የካቲት29 ቀን ዐረፈች። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ከሰማዕታት ጋር መጥቶ ነፍሷን ተቀብሎ ወደ ገነት ወስዶ አኖራት፡፡ ባረፈች ጊዜ በሥጋዋ ላይ ታላቅ የብርሃን ዓምድ ተተክሎ የታየ ሲሆን እንደ ፀሓይም ከጠዋት እስከ ማታ ያበራ ነበር፡፡ በመካነ መቃብሩዋም ላይ እስከ አርባ ቀን ድረስ ብርሃን ተተክሉ ታይቷል፡፡
ምንጭ፦ገድለ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ። ከእናታችን ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን። በጸሎቷም ይማረን!።

