
ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ፦ የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል ከቀጰዶቅያ አገር ነው የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍስጥዓዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ። ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሔደ። ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲአመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው። ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው።
ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም። ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው ጌታችን ግን ያጸናዋል ቊስሉንም ያድነዋል ሦስት ጊዜም እንደ ሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርነት አክሊል እንደሚቀበል ነገረው። ቃል ኪዳንም ሰጠው ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው።
ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ ሞልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር። ቅዱሱም ያንን ጽዋ በመስቀል መልክት አማትቦ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ። ከእርሱ ጋራ ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቊጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ። ቅዱሱንም “እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን” አሉት። በዚያን ጊዜ ጸለየ እንዳሉትም አደረጋቸው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቊጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ።
ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት። አቃጥለው አሳርረው ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ይድራስ ከተባለ ተራራላይ በተኑት። ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው። ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ። ቊጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።
ነገሥታቱም ደግመው ሙታኖችን ብታስነሳ አምላክህ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን በእርሱም እናምናለን” አሉት። ቅዱሱም ጸለየ ከመቃብር ጒድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ የገሀነምንም ወሬ ተናገሩ ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው ዐረፉ። ከሀድያን ነገሥታት ግን ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ ብለው ተከራከሩ። ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበለት። የዚያች መበለትም ቤቷ ምሰሶ ቅርጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ። ያቺም መበለት በተመሰለች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ “የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደእኔ መጣ” አለች። ቅዱሱም “እኔ አምላክ አይደለሁም የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ” አላት። እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው “የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ። ዕውር፣ ደንቆሮ፣ ዲዳ፣ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምህሃለሁ”። ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበው ያንጊዜም አየ። ቅዱስም “በሌላ ጊዜ እንዲሰማ እንዲናገርና እንዲሔድ እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ” አላት። በዚያን ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ ስለ እርሷም ጠየቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት። ንጉሡም ተቆጣ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አስገረፈው በመንኰራኵር አበራዩት ሙቶም በከተማ ውጭ ጣሉት ጌታም ከሞት አስነሣው ወደ ነገሥታቱም ተመለሰ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ ስለ ሕይወቱም አደነቀ።
ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት “ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ እኔ ስሠዋ እንዲአዩ” አለው። ንጉሡም ዕውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው። ለጸሎትም ተነሣ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ የዱድያኖስ ሚስቱ እለእስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እንደሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀምረ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች።
በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአያት ጊዜ ፈገግ አለ “ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው” አላት ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ “ወደ አጵሎን ሒድ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እዘዘው” አለው። ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው። በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለበት መጥቶ “እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም” ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ። ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው ጣዖታቱም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው ከወገኖቹ ጋራ ዐፈረ። ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ። እርሷም “አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖች አትጣላቸው አላልኩህምን” አለችው። ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅ ተቆጣ ወደ ክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ። ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች።
በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲአርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት። ያን ጊዜም የክብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ድል አድራጊ ቅዱስ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥታትን ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው። ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋራ ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው። በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ፣ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ።
ከዚህም በኋላ ወታደሮቹ የቅዱሳን የከበረች ራሱን ቈረጡት ደም፣ ውኃና ወተት ፈሰሰው፤ ጌታም ቅዱስ ሚካኤልን በብርሃን ልብስ ደሙን እንዲቀበለው አዘዘ። ጌታችንም የኃያሉ የቅዱስ ጊዮርጊስን ነፍስ በእጁ ተቀብሎ ሳማት፤ በሰማያዊ ልብስም አጐናጥፎ ከእርሱ ጋራ ወደ ሰማይ አሳረጋት። አየር በሙሉ ቅዱሳን መላእክትን ተሞላ። ለቸር አባቱና ለመንፈስ ቅዱስ ቊርባን አድርጎ እስኪያቀርበው ድረስ ቅዱሳን ሁሉ በየወገናቸው ያመሰግኑ ነበር። የብርሃን ልብስ አለበሰው። በዕንቈ ባሕርይ ያጌጠ ከጽሩ ወርቅ የተሠሩ መከራ በተቀበለባቸው ሰባት ዓመታት ልክ ከዕፀ ሕይወት አበቦች የተሠሩ አክሊሎች ያሉበትን ዘውድ አቀዳጀው ለዘላለም ከማኅበረ በኵር ጋራ ስሙን ጻፈው። ሰማያውያን መላእክትና ቅዱሳንንም ሁሉ በየወገናቸው በመንበሩ ላይ እንዲአስቀምጡት፤ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በዓል እንዲ ያደርጉለት አዘዛቸው።
ከዚህም በኋላ ከመብረቁ፣ ከነጐድጓድ፣ ከንውጽውጽታው ጽናት፣ ከዝናሙ ብዛት የተነሳ በምድር ላይ ትልቅ ድንጋፄ ሆነ። ምድርም ሦስት ጊዜ ተናወጸች ከዚያ ቆመው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሸሹ ወደ ከተማም ሔዱ ጭፍሮችም ይህንን በአዩ ጊዜ በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አመኑ። ነፍሱም ወደ ሰማይ በዐረገች ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሰገደች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምን ነፍስ ከሥጋዋ በተለየች ጊዜ አስቀድሞ ለሥሉስ ቅዱስ ትስገድ ከዚህ በኋላ ወደ ወዳጄ ወደ ጊዮርጊስ ይወሰዷት እና ለርሱ እጅ ትንሣ ብሎ አዘዘ፤ በዚህ ሁኔታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስክርነቱ ሚያዝያ በባተ በሃያ ሦስት ቀን በዕተ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ተፈጸመ። አገልጋዮቹም ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት ወደ ሀገሩ ልዳም ወስደው ቤተክርስቲያን ሰርተው በውስጡ አኖሩት፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የቅዱስ ጊዮርጊስም በረከቱ ረድኤቱ ሁላችንን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ፦ ገድለ ጊዮርጊስ እና የሚያዚያ 23 ስንክሳር።

