ጾመ ሐዋርያት


ሐዋርያት ወንጌለ መንግሥት እንዲስፋፋና በሕዝብም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ አገልግሎታቸው የሠመረ እንዲሆን መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ በበዓለ ሃምሳ ማግሥት ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ በሰጣቸው ሥልጣን ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማውጣት እንዲሁም የተለያዩ ገቢረ ተአምራትን ይፈጽሙ ዘንድ ጸሎትና ጾም ያስፈልጋቸው ነበርና፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን ጋኔን ያለበትን ልጅ ካዳነው በኋላ ሐዋርያቱ ስለምን እነርሱ ጋኔን ከሰው ማውጣት እንዳልቻሉ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መልሶላቸዋል፤ ‹‹…ይህ ዓይነቱ ግን ያለጾምና ጸሎት አይወጣም፡፡›› (ማቴ.፲፯፥፳፩)

ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ገቢረ ተአምራትን ሲፈጽም፣ ሲጾምና ሲጸልይ አብረውት ሆነው አይጾሙም ነበር፤ በዚያን ጊዜም የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙርት ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹እኛና ፈሪሳውያን ብዙ እንጾማለን፤ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጾሙም›› ብለው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጾማሉ፡፡ (ማቴ.፱፥፲፬-፲፭)


ሙሽራ የተባለውም ጌታችን ኢየሱስ በምድር ላይ ነገረ ድኅነትን ፈጽሞ እስኪያርግና መንፈስ ቅዱስ ሚዜዎቻቹም በተባሉት ሐዋርያት ላይ እስኪያድር ድረስ አልጾሙም፤ ከዚህ በኋላ ግን ጾማቸውን እንደሚጀምሩ ጌታችን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ያለ ጾምና ያለ ጸሎት አገልግሎት ሊሰምር አይችልም፤ ጠላታችን ዲያብሎስንም ማሸነፍ አይቻለንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ ‹‹መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?›› ብሎ እንደተናገረው ሐዋርያት በዓለም ዙሪያ በ፸፪ ቋንቋ ማስተማር የቻሉትና ተልእኮአቸው የሠመረላቸው አስቀድመው በመጸለያቸውና መጾማቸው ነው፡፡


ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸው ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊውንም የሚያስቡ ናቸው›› በማለት እንደተናገረው ለከርሣቸው የሚኖሩ ክብራቸውን ያጡ ሰዎች በርካቶች ናቸው፤ ሰው እግዚኢብሔር አምላኩን የሚተወው ራሱን ለሥጋ ምግቦች አዘጋጅቶ ለሆዱ ብቻ ሲኖር ነው፡፡ ለጾም ያደሉ ቅዱሳን ግን ፊታቸው የሚያበራ፣ በጥላቸው ድውይ የፈወሱ፣ ሙት ያነሡ፣ በመቅደሱ ገብተው ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆኑትን ሰዎች በመፈወስ ያዳኑ ናቸው፤ (ፊል.፫፥፲፱)


ሐዋርያት በጾምና በጸሎታቸው ወንጌለ መንግሥት እንዲፋጠን ከአምላካቸው እግዚአብሔር የተሰጣቸውን መመሪያ ይዘው ተጉዘዋል፡፡ እኛም በጾምና በጸሎት ተግተን ጌታችን ኢየሱስ በመሠረተልን የድኅነት መንገድ ተጉዘን ወደ እግዚአብሔር ክብር ራሳችንን በንስሓ መለወጥ እንችላለን፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በየዓመቱ የሐዋርያትን ጾም በማወጅ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲጾሙ ታደርጋለች፤ በዚህ ዓመትም ጾሙ ከግንቦት 28 ቀን እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በመሆኑ ሁላችን ልንጾመው ይገባል፡፡


ነፍስን የሚያለመልምና በቅድስና ሕይወት የሚያኖር፣ በወንዝ ዳር እንደተተከለችና ሁል ጊዜ ፍሬዋን እንደምትሰጥ ዛፍ ነፍሳችን እንድታፈራ የሚያደርግ ጾም በመሆኑ ሁላችን ልንጾም ይገባል፡፡